በኢትዮጵያ የኮሮና ተጠቂዎች በ3 ቀናት ውስጥ ብቻ በ105 ሰዎች አሻቀበ

በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ እንዳለባቸው በምርመራ የተረጋገጡ ሰዎች ባለፉት ሶስት ቀናት ውስጥ ብቻ በ105 ሰዎች ጨምሯል። የጤና ሚኒስትር ዛሬ ባወጣው መግለጫ ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ በተደረገ ምርመራ 61 ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል። በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ የመጀመሪያ ተጠቂ መገኘቱ ይፋ ከተደረገበት ከመጋቢት 4፤ 2012 ወዲህ የዛሬው በአንድ ቀን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው የተመዘገበበት ሆኗል። 

የሀገሪቱ መዲና አዲስ አበባ አሁንም ከፍተኛው የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ያሉበት ቦታ እንደሆነች ቀጥላለች። ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ ቫይረሱ በምርመራ ከተገኘባቸው ውስጥ 48ቱ በአዲስ አበባ ያሉ መሆናቸውን የጤና ሚኒስትር መግለጫ አስታውቋል። ከእነዚህ ውስጥ 43ቱ የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክም ሆነ በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት የሌላቸው መሆናቸው መጠቆሙ ሁኔታውን አሳሳቢ አድርጎታል። 

የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ከትናንት በስቲያ በሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ በተዘጋጀ መድረክ ላይ በሰጡት ማብራሪያ በተወሰኑ የአዲስ አበባ አከባቢዎች ያለው ሁኔታ የወረርሽኝ ጥናት ባለሙያዎች “ደረጃ አራት” ብለው የሚጠሩት ምዕራፍ ላይ እየደረሰ መሆኑን ተናግረው ነበር። በሀገር አቀፍም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የስርጭት ሁኔታዎች በአራት ደረጃዎች እንደሚከፈሉ ያስታወሱት ሚኒስትሯ ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ሁኔታ በዚሁ ክፍፍል ላይ ተመስርተው አስረድተዋል። 

“እንደ ሀገር ያለውን ሁኔታ ስናየው በሶስተኛው ደረጃ ወይም ‘በክለስተር ያሉ ኬዞች’ በየቦታው የሚገኙበት ሁኔታዎች ላይ ነው በአብዛኛው ያለነው። በተወሰኑ የአዲስ አበባ አካባቢዎች በተለይ ይበልጥ ወደ አራተኛው [ደረጃ] ያደላ፤ በማህብረሰብ ውስጥ ያለ ስርጭት እየታየ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው” ብለው ነበር ዶ/ር ሊያ። 

በዓለም ጤና ድርጅት ምደባ መሰረት “ሶስተኛ ደረጃ” ተብሎ በሚጠራው ወቅት ከዚህ ቀደም በኮሮና ቫይረስ ከተጠቁ ሰዎች ጋር ግንኙነት በሌላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ዘንድ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ይከሰታል። ሁኔታው ወደ አራተኛ ደረጃ ተሸጋገረ የሚባለው ደግሞ የቫይረሱ ስርጭት አድማሱን ሲያሰፋ እና የተጠቂዎች ቁጥር መጨመር በሀገሪቱ የጤና ስርዓት ላይ ከፍተኛ ጫና ሲያሳድር ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)