አምስት የሶማሌ ክልል ምክር ቤት አባላት ታስረዋል ተባለ

በተስፋለም ወልደየስ

የሶማሌ ክልል ምክር ቤት ያለመከሰስ መብታቸውን ካነሳባቸው የምክር ቤቱ አባላት ውስጥ አምስቱ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ቤተሰቦቻቸው እና ባልደረቦቻቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። አምስቱ የምክር ቤት አባላት ላለፉት አራት ቀናት ጅግጅጋ በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ በእስር ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል። 

ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ላይ አስቸኳይ ስብሰባውን አካሂዶ የነበረው የሶማሌ ክልል ምክር ቤት “ሁከት በመፍጠር፣ በሥርዐት አልበኝነት እንዲሁም በሌሎች ወንጀሎች ተጠርጥረዋል” ያላቸውን የ12 አባላቱን ያለመከሰስ መብት አንስቷል። ከእነዚህ የምክር ቤት አባላት መካከል ዶ/ር ኒምአን ሃመሬ፣ ዩሱፍ ኢልሚ፣ ነዲር ዩሱፍ፣ ሻፊ አሺር እና አብዱራዛቅ አብዱላሂ ሐሙስ ግንቦት 13 ምሽት መታሰራቸውን ባልደረቦቻቸው ተናግረዋል። 

ዶ/ር ኒምአን፣ ዩሱፍ እና እና ነዲር በሐሙሱ የምክር ቤት ስብሰባ ተጨማሪ አጀንዳዎች እንዲያዙ ጥያቄዎችን ሲያቀርቡ የነበሩ መሆናቸውን ስብሰባውን የተከታተሉ አባላት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። አስቸኳይ ስብሰባውን ይመሩ በነበሩት በምክትል አፈ-ጉባኤ ወ/ሮ ፍርደውሳ መሐመድ አማካኝነት ለጉባኤው በመጀመሪያ ቀርበው የነበሩ አጀንዳዎች ስድስት ነበሩ። 

በሶማሌ ክልል ፋፋን ዞን ስር የምትገኘው የቱሉጉሌ ወረዳ ተመራጭ የሆኑት ዶ/ር ኒምአን በክልሉ ያለው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሁኔታ በአጀንዳነት እንዲያዝ መጠየቃቸውን የምክር ቤት አባላት ይገልጻሉ። በቆራሄ ዞን ያለችውን የሽላቦ ወረዳን የወከሉት ዩሱፍ ኢልሚ በበኩላቸው በክልሉ ምክትል ርእሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሃመድ አስተዳደር ላይ የምክር ቤት አባላት “የማስተማመኛ ድምፅ (vote of confidence) ይስጡ” የሚል አጀንዳን ማቅረባቸውን ተናግረዋል።

ፎቶ፦ የሶማሌ ክልል መገናኛ ብዙሃን 

ከጨረር ዞን፤ ድሮር ወረዳ የተመረጡት ነዲር ዩሱፍ ደግሞ፤ የስልጣን መልቀቂያ ባስገቡት አፈ ጉባኤ ምትክ፤ አዲስ ሰው እንዲመረጥ በተጨማሪ አጀንዳነት ለማስመዘገብ መሞከራቸውን የምክር ቤት አባላቱ ያስረዳሉ። ሆኖም ሶስቱም አጀንዳዎች ላይ ምክር ቤቱ ድምጽ ሳይሰጥ ቀድሞ በተያዙት አጀንዳዎች ስብሰባው እንዲቀጥል መደረጉ በተወሰኑ የምክር ቤት አባላት ዘንድ ተቃውሞ ማስነሳቱን ያብራራሉ። 

“ለተቃውሟችን ተገቢ ምላሽ አላገኘንም” ያሉ የምክር ቤት አባላት ስብሰባውን ረግጠው መውጣታቸውን የሚናገሩት የምክር ቤት አባላት በአካባቢው በነበሩ የጸጥታ ኃይሎች ድብደባ ጭምር የታከለበት ውክቢያ እንደደረሰባቸው ገልጸዋል። የሐሙሱን ስብሰባ ረግጠው ከወጡት ውስጥ አምስቱ የዚያኑ ምሽት መታሰራቸውን መረዳታቸውንም አክለዋል። ታስረዋል ስለተባሉ ሰዎች ባለፈው ሐሙስ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ ቀርቦላቸው የነበሩት የሶማሌ ክልል የጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አብዱላሂ ሀሰን “ስብሰባውን አቋርጠው ከወጡትም ሆነ ሌላ ማንም ሰው በቁጥጥር ስር አልዋለም” ሲሉ አስተባብለው ነበር። 

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው አንድ የታሳሪ ቤተሰብ ግን በቁጥጥር ስር ያሉት የምክር ቤት አባላት መሀል ጅግጅጋ በሚገኘው ጎባልክ ፖሊስ ጣቢያ እንዳሉ አስረድተዋል። ሆኖም “ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዳይገናኙ ተከልክለዋል” ሲሉ ይወነጅላሉ። “ምግብ እንኳ በፖሊስ በኩል ነው የምንሰጠው” ይላሉ።  ውንጀላውን በተመለከተ የሶማሌ ክልል የሚሰጠውን ምላሽ ለማካተት ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም።    

“ተመሳሳይ የእስራት እርምጃ ይወሰድብናል” ብለው የሰጉ የምክር ቤት አባላት ጅግጅጋን ጥለው ወደ አዲስ አበባ መምጣታቸውን ግን “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ማረጋገጥ ችላለች። እነዚህ የምክር ቤት አባላት በሶማሌ ክልል ያለውን ችግር ለመፍታት ከፌደራል ተቋማት ጋር የመነጋገር እቅድ አላቸው። “ችግሩን መፍታት የሚቻለው ፖለቲካዊ ውይይት በማድረግ ነው” የሚሉት ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አንድ የምክር ቤት አባል “ለችግሩ ሁነኛ መፍትሄ የማይሰጠው ከሆነ መጨረሻው የሚሆነው ትርምስ ነው” ሲሉ አስጠንቅቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)