ባለስልጣናት እና አመራሮች ሀብታቸውን በ42 ቀናት እንዲያስመዘገቡ ቀነ ገደብ ተሰጣቸው

የፌደራል የስነምግባርና የፀረሙስና ኮሚሽን የፌደራል፣ የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር አመራሮች እንዲሁም የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሃላፊዎች በመጪዎቹ 42 ቀናት ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ ቀነ ገደብ ሰጠ። በጊዜ ገደብ ውስጥ የሀብት ምዝገባ በማያከናውኑ አመራሮች ላይ ኮሚሽኑ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል። 

ኮሚሽኑ ማስጠንቀቂያውን የሰጠው ለመንግስት አመራሮች እና ሃላፊዎች ዛሬ ማክሰኞ ግንቦት 18፤ 2012 ባስተላለፈው የሀብት ምዝገባ ጥሪ ነው። የኢትዮጵያ መንግስት የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት እና ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ከፍተኛ ባለስልጣናት እና ተሿሚዎች ሀብታቸውን በይፋ እንዲያስመዘግቡ አዋጅ ያወጣው የዛሬ አስር ዓመት ነበር። አዋጁ የባለስልጣናት ሀብት የመመዝገብ እና አፈጻጸሙን የመከታተል ስልጣን በአዋጅ የሰጠው ለፌደራል የስነምግባርና የፀረሙስና ኮሚሽን ነው። 

“በአዋጁ መሠረት ሀብትና የገቢ ምንጫቸውን በወቅቱ የሚያስመዘግቡ የመንግስት ተሿሚዎች ያሉትን ያህል አንዳንድ አመራሮች ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ ተደጋጋሚ ጥሪ ቢደረግላቸውም ለማስመዝገብ ፍቃደኛ አይደሉም” ሲል ኮሚሽኑ በዛሬው የምዝገባ ጥሪ ላይ አመልክቷል። እስከ ሰኔ 30፤ 2012 ቀን ድረስ ገደብ በተቀመጠለት የሀብት ምዝገባ ከዚህ ቀደም ሀብታቸውን ያስመዘገቡም “እድሳት” እንዲያከናውኑ ተጠይቀዋል።

በ2002 ዓ.ም የወጣው የሀብት ማሳወቅ እና ማስመዝገብ ሥርዓት አዋጅ ማንኛውም ተሿሚ በራሱና በቤተሰቡ ባለቤትነት ወይም ይዞታ ሥር የሚገኝ ሀብትና የገቢ ምንጮች፣ የማሳወቅና የማስመዝገብ ግዴታ እንዳለበት ይደነግጋል። ማንኛውም ተሿሚ፣ ተመራጭ ወይም የመንግሥት ሠራተኛ ሀብቱን በአዋጁ መሠረት ለምዝገባ ሳያሳውቅ ከቀረ ወይም ሆን ብሎ ትክክል ያልሆነ የምዝገባ መረጃ ከሰጠ በኢትዮጵያ የወንጀል ህግ እንደሚጠየቅ አዋጁ ያስቀምጣል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)