የአገር አቋራጭ ትራንስፖርት ታሪፍ ጭማሪ ተደረገ

  • በቤት መኪኖች ላይ ተጥሎ የነበረው ፈረቃ ሙሉ ለሙሉ ተነሳ
  • ከቤት ውጭ የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ማድረግ ግዴታ ሆነ 

በሐይማኖት አሸናፊ

የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመቆጣጠር የተቋቋመው የሚኒስትሮች ኮሚቴ በአገር አቋራጭ ትራንስፖርት መደበኛ ዋጋ ላይ ተጥሎ የነበረው ጭማሪ ወደ 75 በመቶ እና መቶ በመቶ ከፍ እንዲል ወሰነ። በቤት መኪኖች ላይ ተጥሎ የነበረው ፈረቃ ሙሉ ለሙሉ መነሳቱንም ኮሚቴው አስታውቋል። 

ኮሚቴው ውሳኔውን ያሳለፈው፤ በትራንስፖርት ሚኒስቴር የተደረገ አንድ ጥናት፤ የህዝብ እንቅስቃሴን ለመቀነስ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ አስተዋጽኦ እንዳለው ማመላከቱን ተከትሎ ነው። የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማስፈጸሚያ ደንብ የአገር አቋራጭ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ከተሽከርካሪያቸው ወንበር ብዛት ከግማሽ በላይ እንዳይጭኑ በመከልከሉ ሳቢያ አገልግሎት ሰጪዎቹ ከመደበኛ ታሪፋቸው 50 በመቶ ጭማሪ እንዲያደርጉ ፈቅዶ ነበር።   

ዛሬ ረቡዕ ግንቦት 19፤ 2012 ይፋ በተደረገው ውሳኔ መሰረት መደበኛ የወንበር አቅማቸዉ ከ45 ሰው በላይ የሆኑ አገር አቋራጭ ተሽከርካሪዎች ከመደበኛ ዋጋቸው 75 በመቶ ጭማሪ ያደርጋሉ። መደበኛ የወንበር ቁጥራቸዉ እስከ 45 ሰው ለሆኑ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ደግሞ ከመደበኛ ታሪፋቸው እጥፍ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ እንዲችሉ ውሳኔው ፈቅዶላቸዋል።

በመመሪያ መልክ የተዘጋጀው የዛሬው ውሳኔ በኮድ ሁለት የቤት ተሽከርካሪዎች ላይ ጥሎት የነበረውን ከፊል የእንቅስቃሴ እገዳም ማንሳቱን ገልጿል። ከፊል እገዳው የቤት ተሽከርካሪዎችን በሙሉ እና በጎዶሎ የመለያ ቁጥር (ታርጋ) በመለየት በፈረቃ ጥቅም ላይ እንዲውሉ የሚያደርግ ነበር። እገዳው ተግባራዊ የተደረገው “ግለሰቦች ቤታቸው እንዲዉሉ በማድረግ፤ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ታሳቢ ተደርጎ ነበር” ተብሏል።

“የኮድ 2 ተሸከርካሪ ባለቤቶች በታሰበው መልኩ ቤታቸው ከመዋል ይልቅ የህዝብ ትራንስፖርት በመጠቀም እና ታርጋዎችን እየቀያየሩ የመጠቀም ሁኔታ መታየቱ እንዲሁም ተራቸው ባልሆነ ቀን ቤታቸው ከመዋል ይልቅ በሰፊዉ የመንቀሳቀስ ሁኔታ የተስተዋለ በመሆኑ የክልከላውን መልክ መቀየር አስፈላጊ ሆኗል” ሲል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አዲሱን መመሪያ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። “በመሆኑም በአጠቃላይ በኮድ ሁለት የቤት ተሸከርካሪዎች ላይ ተጥሎ የነበረዉ ክልከላ ተነስቷል” ብሏል መግለጫው። 

አዲሱ መመሪያ ከዚህ በተጨማሪም በአዲስ አበባ የሚታየውን የትራስፖርት መጨናነቅ ለመቀነስ የከተማይቱ አስተዳደር የመንግስት ሰራተኞች የስራ መግቢያ ሰአት ጠዋት 1፡30 እንዲሆን ውሳኔ አሳልፏል። የስራ መውጫ ሰዓትም 9፡30 እንዲሆን ተደርጎ ተሸጋሽጓል፡፡

ከዛሬ ጀምሮ ስራ ላይ ይውላል የተባለው አዲሱ መመሪያ የሚኒስትሮች ኮሚቴ ከዚህ ቀደም ያወጣቸውን ሁለት መመሪያዎች ማሻሻያዎች የያዘ መሆኑ ተጠቁሟል። “መመሪያ ቁጥር 4፤ 2012” የሚል ስያሜ የያዘው አዲስ ድንጋጌ የጸደቀው የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ በተገኘበት ሰሞን የነበሩ ጥንቃቄዎች መቀነሳቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት መሆኑ ተነግሯል።  

የሚኒስትሮች ኮሚቴው በመንግስት ተቋማት፣ በልማት ድርጅቶችና በግል ተቋማት ውስጥ ባደረገው ጥናት የመዘናጋት ሁኔታዎችን መታዘቡን እና ይህንንም አሳሳቢ ሆኖ እንዳገኘው ገልጿል። በህብረተሰቡ ዘንድም በግብይት ቦታዎች እና በትራንስፖርት አገልግሎት መስጫ አካባቢዎች ላይ መዘናጋትና በቂ ቅድመ ጥንቃቄ እየተደረጉ አለመሆኑን ታዝቧል። ይህንንም ለመቅረፍ የሚኒስትሮች ኮሚቴው ከዛሬ ጀምሮ ከቤት ውጭ በማንኛውም ቦታ የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል (ማስክ) ማድረግ ግዴታ እንዲሆን የወሰነ ሲሆን የመንግስት የጸጥታ መዋቅርም ይህንን እንዲያስፈፅም ትዕዛዝ ሰጥቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)