የፓርላማው ኮሚቴ ስለ መጅሊስ አዋጅ ምን ተወያየ?

በተስፋለም ወልደየስ

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱ ከተረጋገጠ ወዲህ መደበኛ ስብሰባዎችን ማስተናገድ ያቆመው ዕድሜ ጠገቡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋናው አዳራሽ፤ ዕድሜ ጠገብ የሆነ ጥያቄን ለማስተናገድ ትላንት፤ ረቡዕ ግንቦት 19፤ 2012 በሩን ክፍት አድርጎ ነበር። በአዳራሹ ስብሰባ ለማካሄድ ጥሪውን ያቀረበው አካል፤ ከአራት ሰዎች በላይ በአንድ ቦታ መሰብሰብ የሚከለክለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላለመጣስ “በልዩ ሁኔታ ፍቃድ” መጠየቅ ግድ ብሎታል።

የተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህ እና ዲሞክራሲ ቋሚ ኮሚቴን “ልዩ ፍቃድ” እንዲጠይቅ ያደረገው ስብሰባ በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ለበርካታ አስርት ዓመታት ጥያቄ ሲቀርብበት የቆየ ጉዳይን የተመለከተ ነው። በትንሹ ለስድስት አስርት ዓመታት የዘለቀው ይህ ጥያቄ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት (መጅሊስ) በአዋጅ ህጋዊ ተቋም የማድረግ አላማን ያነገበ ነው።  

ዓመታት በተሻገሩ ተቃውሞዎች ጭምር የታጀበው፤ ምክር ቤቱን ህጋዊ ሰውነት የማሰጠት እንቅስቃሴ፤ ዕውን ወደ መሆን የተቃረበው ከሶስት ወር በፊት ነበር። ለዕረፍት ተበትኖ የነበረው የተወካዮች ምክር ቤት የካቲት 5፤ 2012 አስቸኳይ ስብሰባ በጠራበት ወቅት የመጅሊስ ህጋዊ ሰውነትን የተመለከተ የአዋጅ ረቂቅን እንደሚመለከት መገለጹ የጉዳዩ እልባት ማግኛ ምልክት ተደርጎ ተወስዷል።

አስር አጀንዳዎች በቀረቡበት እና ሁለት አወዛጋቢ የህግ ረቂቆች በጸደቁበት በዚያ ስብሰባ ግን የመጅሊሱ ጉዳይ ያን ያህል ትኩረት ሳይስብ አልፏል። በዕለቱ ስብሰባ የመጅሊሱ የአዋጅ ረቂቅ በዝርዝር እንዲታይ ለፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ መመራቱም መነጋገሪያነቱን አቀዛቅዞት ቆይቷል። 

የአዋጅ ረቂቁ እንደሌሎች ህጎች በርካታ ገጾች ያሉት እና ዝርዝር ጉዳዩችን ያካተተ አልነበረም። አጠቃላይ አዋጁ በአንድ ገጽ ከግማሽ እና በሰባት አጫጭር አንቀጾች የተዘጋጀ ነው። አዋጁን ለማብራራት የቀረበው ሰነድ እንኳ ከስድስት ገጽ አይዘልም። እንዲያም ሆኖ ግን ረቂቁ በተወካዮች ምክር ቤት አባላት ዘንድ በርካታ ጥያቄዎችን አስነስቷል። 

በትላንትናው የጥያቄዎች ማቅረቢያ መድረክ ከአዋጁ አስፈላጊነት እስከ የሃይማኖቶች እኩልነት እና የመንግስትና ሃይማኖት መለያየት መርህ (secularism) ድረስ የተጓዙ ጥያቄዎች ቀርበዋል። የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ተጨማሪ ገቢ በሚያስገኙ ስራዎች ላይ መሰማራት እንደሚችል በአዋጁ ረቂቅ ላይ መጠቀሱ ያሳሰባቸው የምክር ቤት አባላትም ነበሩ። በምክር ቤቱ ስር ወደፊት የሚቋቋሙ ተቋማት እና ድርጅቶች “የተለየ ምዝገባ ሳያስፈልጋቸው በአዋጁ መሰረት ህጋዊ ሰውነት እንደሚያገኙ” መደንገጉም አነጋግሯል። 

ዕውቅና ወይስ ህጋዊ ሰውነት?

በአዋጁ አስፈላጊነት ላይ ጥያቄ ያቀረቡ የምክር ቤት አባላት የእስልምና ሃይማኖት ቀድሞም ቢሆን በኢትዮጵያ ዕውቅና ማግኘቱን በማንሳት ተከራክረዋል። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በፓርላማ መድረኮች አነጋጋሪ ሀሳቦች በማንሳት የሚታወቁት የህወሓት አባል አቶ ካሳ “የእስልምና ሃይማኖት በአረብ ሀገር ሲመሰረት አማኞቹ በስደት ወደ አክሱም ከመጡበት ጀምሮ ነው ዕውቅና ያገኘው” ሲሉ የሃይማኖቱን ታሪካዊ ዳራ አጣቅሰዋል። “አሁን ህጋዊ ዕውቅና የሚለው ግን አይገባኝም” ሲሉም አክለዋል። 

አዋጁ በ1960ዎቹ ቀርቦ ቢሆን ኖሮ “ያለ ችግር” ይቀበሉት እንደነበር የጠቀሱ ሌላ የምክር ቤት አባል ብዙ የሃይማኖት ተቋማት ባሉበት በዚህ ጊዜ ግን የሃይማኖት እኩልነት ጥያቄ ስለሚያስነሳ እንደሚቸገሩ ገልጸዋል። እነዚህ የሃይማኖት ተቋማት “ዕድሜያቸው እና የሚከተላቸው የህዝብ ብዛት ምንም ይሁን ምን እኩል ናቸው” የሚል እምነት እንዳላቸው ያስረዱት አባሉ “ስለዚህ ሁሉም ዕውቅና ሊያገኙ ይገባል” በማለት ተሟግተዋል። 

ከዚህ ቀደም በነበሩ መንግስታት የተሰሩ ስህተቶችን ለማረም ሌላ ስህተት መስራት እንደማይገባም መክረዋል። ሌሎች የሃይማኖት ተቋማት ተመሳሳይ የእውቅና ጥያቄ ይዘው ቢመጡ “አናስተናግዳችሁም ነው ወይ መልሱ?” ሲሉ ጠይቀዋል። “ሂሳብ ለማወራረድ የገባንበት ወጥመድ በግልጽ ቢታይ እላለሁ” ሲሉም አሳስበዋል። 

የእርሳቸውን ሀሳብ የተጋሩት አቶ ዘሪሁን የተባሉ የምክር ቤት አባል የህዝብ ብዛት እና ታሪክን እንደ መስፈርት መጠቀም “ከሃይማኖት እኩልነት አንጻር ተገቢ አይመስለኝም” ብለዋል። ሌሎች የሃይማኖት ተቋማት እኒህን መስፈርቶች “በከፊልም፣ በሙሉም ካላሟሉ ህጋዊ ሰውነት አይሰጣቸውም ወይ?” የሚል ጥያቄም አንስተዋል። የምክር ቤት አባሉ ጥያቄውን ያነሱት በአዋጁ መግቢያ እና በማብራሪያው የተቀመጡ ገለጻዎችን ተንተርሰው ነው። 

የአዋጁ መግቢያ “የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በተግባር እውቅና ያለው የህዝብ ተቋም እንደመሆኑና ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ያለውን የሙስሊም ማህብረሰብ በመንግስት ዘንድና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚወክል በመሆኑ ህጋዊ ሰውነትና እውቅና በአዋጅ መስጠት አስፈላጊ” በመሆኑ ድንጋጌው መዘጋጀቱን ያስቀምጣል። የአዋጁ ማብራሪያ በበኩሉ “የእስልምና ሃይማኖት በኢትዮጵያ ካለው ረዥም ታሪክና፣ ከሃይማኖቱ ተከታዮች ብዛት አንጻር የዚህ ሃይማኖት አስተዳደር ተቋም የሆነውን ምክር ቤት በምዝገባ ሳይሆን በአዋጅ የህግ ሰውነት መስጠቱ ተገቢ ይሆናል” ይላል። 

“ምክር ቤቱ በዚህ መንገድ የህግ ሰውነት ቢያገኝ የማንኛውም ዜጋና ዕምነት ተከታይ መብት የሚጥስ አይሆንም። በተጨማሪም በምዝገባም ሆነ በአዋጅ ህጋዊ ሰውነትን የሚሰጠው መንግስት ስለሆነ ህጋዊ ሰውነት በአዋጅ መሰጠቱ መንግስትና ሃይማኖት መለያያትን መርህ አይጥስም” ሲል ማብራሪያው ለመሰል ጥያቄዎች ምላሽ ያለውን አስቀምጧል። “የአዋጁ መውጣት የእስልምና ሃይማኖትንም ሆነ መሪ ተቋሙን ለይቶ መደገፍ አልያም ከፍ ማድረግ ሳይሆን አሁን በተግባር (defacto) ያለውን አቋም ህጋዊ (de jure) ማድረግ ብቻ በመሆኑ የአዋጁ መውጣት የመንግስት ጣልቃ ገብነትንም ሆነ በሌሎች ሃይማኖት ተቋማት ላይ ኢ-ፍትሀዊነትን አያስከትልም” ሲል ማብራሪያው አክሏል።

በስብሰባው ላይ በአስረጂነት የተገኙት በፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ መስሪያ ቤት ምክትል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ዶ/ር ጊዲዮን ጢሞቲዮስ ተመሳሳይ ሀሳብ አንጸባርቀዋል። “ይህ አዋጅ ምክር ቤቱን እያቋቋመ አይደለም። ምክር ቤቱ ቀደም ብሎ የተቋቋመ ነው። የአዋጁ ዓላማ ህጋዊ ዕውቅና መስጠት ነው” ብለዋል። ለኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በህግ ጉዳዮች ላይ ድጋፍ የሚሰጠው ኮሚቴ አባል የሆኑት እና በአስረጂነት የቀረቡት አቶ አብዱልሃኪም ጀማል “ዕውቅና እየተጠየቀ ያለው ለሃይማኖቱ አይደለም። ሃይማኖቱ በኢትዮጵያ ለ1400 ዓመት እውቅና ያለው ነው። ዕውቅና እየተጠየቀ ያለው ለተቋሙ ነው” ሲሉ በጉዳዩ ላይ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል። 

በአስረጂነት የተጠሩ ባለሙያዎችም ሆኑ የምክር ቤት አባላት “ሌሎች ሃይማኖቶች ተመሳሳይ የህግ ሰውነት” ቢጠይቁ መስተናገድ እንደሚገባቸው አመልክተዋል። ምክትል ጠቅላይ አቃቤ ህጉ በበኩላቸው ይህ አሰራር ከጠቅላይ ምክር ቤቱ የህግ ሰውነት ጥያቄም በኋላ ተግባራዊ መደረግ መቀጠሉን ምሳሌ ጠቅሰው አስረድተዋል። የሚኒስትሮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስልን ህጋዊ ሰውነት ለመስጠት የቀረበለት ረቂቅ አዋጅ በቅርቡ አጽድቆ ወደ ተወካዮች ምክር ቤት መምራቱን ጠቅሰዋል። ይህ አዋጅ ነገ አርብ ግንቦት 21፤ 2012 በሚካሄደው የፓርላማው አራተኛ ልዩ ስብሰባ ላይ እንዲቀርብ በአጀንዳ ተይዟል።

“ምዝገባው የት ገባ?”

ምክትል ጠቅላይ አቃቤ ህጉ ስብሰባው ለጥያቄ እና መልስ ከመከፈቱ አስቀድሞ ይህን መሰል ሰፊ ማብራሪያ ቢሰጡም ስብሰባውን የታደሙ የፓርላማ አባላት ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን ከማቅረብ አልገታቸውም። ወይዘሮ ሰናይት የተባሉ የምክር ቤት አባል ቀደም ሲል በፓርላማው የጸደቀ አዋጅ የሃይማኖት ተቋማትን ምዝገባ የማከናወን ስልጣን ለሰላም ሚኒስቴር መስጠቱን አስታውሰዋል። “ያንን አሰራር ትተን ነው ወደዚህ የምንገባው?” ሲሉ ጠይቀዋል። የሰላም ሚኒስቴር የሃይማኖት ተቋማትን የተመለከተ የህግ ማዕቀፍ እያዘጋጀ መሆኑ በአዋጁ ማብራሪያ መጠቀሱን አንስተው የመጅሊሱ የእውቅና ጥያቄን መጪው አዋጅ “አይፈታውም ወይ?” ሲሉ ሞግተዋል። 

በአዋጁ ማብራሪያም ሆነ በዕለቱ በነበሩ አስረጂዎች እንደተጠቀሰው በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በአዋጅ የህግ ሰውነት ያገኘችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ብቻ ናት። ቤተክርስቲያኒቱ  ህጋዊ ሰውነት ያገኘችው በ1952 በወጣው የፍትሐ-ብሔር ህግ አንቀጽ 398 መሰረት ነው። ከቤተክርስቲያኒቱ  ውጪ ያሉ ሌሎች የእምነት ተቋማት በሚመለከተው የመንግስት መስሪያ ቤት በሚደረግ ምዝገባ የህግ ሰውነት ይሰጣቸው እንደነበርም ተገልጿል። “ይህ አሰራር በበቂ ሁኔታ የዳበረና ተገቢ የሆነ የህግ ማዕቀፍ አለው ለማለት ያስቸግራል” የሚለው የአዋጁ ማብራሪያ የሰላም ሚኒስቴር እያዘጋጀው ያለው አዲስ የህግ ማዕቀፍ ችግሩን እንደሚቀርፍ ጠቁሟል። 

በስብሰባው ላይ በአስረጂነት የተሳተፉ ባለሙያዎች መጅሊሱ “በሚመለከተው የመንግስት መስሪያ ቤት በሚሰጥ ምዝገባ ብቻ ህጋዊ ሰውነት ያግኝ” የሚለውን አስተያየት አጥብቀው ተቃውመዋል። የመጀሊሱ የህግ ጉዳዮች ድጋፍ ሰጪ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ አብዱልሃኪም የመጅሊሱ በአዋጅ መቋቋም የሙስሊሙ ማህብረሰብ የረጅም ጊዜ ጥያቄ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል። ጠቅላይ ምክር ቤቱ አንድ ጊዜ በአንድ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ውስጥ ባለ ዳይሬክቶሬት ስር ሌላ ጊዜ ጭርሱኑ ሳይመዘግብ መቆየቱንም አስታውሰዋል። “በአዋጅ ይቋቋምልን” የሚለው ጥያቄ አንዱ መነሻም በአንድ መስሪያ ቤት ይሁንታ ስር መውደቅን ማስቀረት እንደሆነ አመልክተዋል።   

አዋጁ ያስፈለገው “በምዝገባ የነበረው የህግ ሰውነት ለመንግስት ጣልቃ ገብነት በር የከፈተ በመሆኑ እና ተቋሙ ላለው አለም አቀፍ ግዴታዎች አይመጥንም በሚል ነው” ብለዋል አቶ አብዱልሃኪም። ተቋሙን በአዋጅ ለማቋቋም ያስፈለገበትን ታሪካዊ ዳራ መመልከት እንደሚያስፈልግም ጠቅስዋል። የአዋጁ ማብራሪያም ይህን ታሪካዊ ዳራ ለመዳሰስ ሞክሯል። 

“ሙስሊሙ ማህበረሰብ ለዘመናት ሲጠይቅ የነበረውን በጠንካራ የህግ መሰረት ላይ የተመሰረተ ተቋም ሳይኖረው ተራ ማህበር ሆኖ መመዝገቡ በርካታ ችግሮችን አስከትሏል” በማለት የሚንደረደረው ማብራሪያው “በዚህ ምክንያት ሙስሊሙ ማህብረሰብ በሀገሪቱ ውስጥ ያለውን የህዝብ ብዛት መጠን፣ በአሰፋፈሩ፣ ከሀገሪቱ የቆዳ ስፋት አንጻር ያለውን ድርሻ፣ ከብሔር ብሔረሰቦች ስብጥርና ከፌደራላዊ መዋቅሩ አንጻርም በየጊዜው መመዝገብና ፈቃድ ማሳደስ የማያስፈልገው የሃይማኖት አስተዳደር ተቋም በህግ እውቅና ቢሰጠው ተገቢ ይሆናል” ሲል ድምዳሜውን አስቀምጧል። 

የተቋማቱ ነገር 

ለተወካዮች ምክር ቤት አባላት አስቀድሞ የተሰራጨው የአዋጁ ማብራሪያ ምዝገባ የማያስፈልገበትን አመክንዮ ቢዘረዝርም ከምዝገባ ጋር የተያያዘ ጉዳይ በፓርላማ አባላቱ ተደጋጋሚ ጥያቄ ቀርቦበታል። ጥያቄ ያስነሳው በአዋጅ ረቂቁ አንቀጽ ሁለት ላይ የተቀመጠው እና በመጅሊስ ስር ወደፊት ስለሚቋቋሙ ድርጅቶችና ማህበራት የሚጠቅሰው ክፍል ነው። እነዚህ ድርጅቶች እና ማህበራት “የተለየ ምዝገባ ሳያስፈልጋቸው” በአዋጁ መሰረት ህጋዊ ሰውነት እንደሚሰጣቸው በአዋጁ መደንገጉ “ትክክለኛ የህግ አወጣጥ አካሄድ አይደለም” በሚል ተተችቷል።   

አንድ የፓርላማ አባል “ምን ሊቋቋም እንደሚችል በማናውቀው ነገር ላይ ህግ ማውጣት ተገቢ አይደለም። አለበለዚያ በግልጽ ሊቀመጥ ይገባል” ብለዋል። ሌላ የምክር ቤት አባል “የሚቋቋሙ” የሚለው ቃል ጥቅል አገላለጽ (generic term) መሆኑን አንስተው የሃይማኖት ድርጅቶቹ እና ማህበራት ምንነት ሊቀመጥ እንደሚገባ ሞግተዋል። አዋጁ “ድርጅቶቹ እና ማህበራቱ ለምን ዓላማ እንደሚቋቋሙ እና ህጋዊ ተጠያቂነታቸው እንዴት ነው የሚለውን የሚመልስ አይደለም” ሲሉም አክለዋል። “አዋጁ ተግባራዊ በሚሆንበት ጊዜ ወደፊት ክርክር ሊያስነሳ ይችላል” የሚሉት እኚህ የፓርላማ አባል “አዋጁን ተከትሎ የሚመጡ ደንቦች ካሉ ዘርዘር ተደርጎ መቀመጥ አለበት” ሲሉም የመፍትሄ ሀሳብ ያሉትን ጠቁመዋል። 

በአዋጁ ዝግጅት ላይ የተሳተፉት አቶ አብዱልሃኪም በመጀመሪያ ለአቃቤ ህግ የተላከው ረቂቅ በርካታ ዝርዝሮች የያዘ እንደነበር አስረድተዋል። የተቋማት እና ድርጅቶች ዝርዝር በአዋጁ ላይ ያልተካተተበት ምክንያት በሃይማኖታዊ ቋንቋ የሚገለጽ እና ቴክኒካዊ በመሆኑ ለዚያ የሚቀርቡ ትርጓሜዎችን ለማስቀረት እንደሆነ ገልጸዋል። ዝርዝሮችን ማስቀመጥ ወደፊት ለማቋቋም የሚታሰቡ ተቋማትን ይገድባል ብለዋል። አቶ አብዱልሃኪም እንዳሉት ጠቅላይ ምክር ቤቱ ህጋዊ ስርዓቱ ጠብቆ የሚሰራ መሆኑ በውስጠ ታዋቂነት የተቀመጠ በመሆኑ ያንን ታሳቢ ማድረግ ይገባል። 

ይህንን የባለሙያውን ገለጻ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ጸሀፊ ቃሲም መሐመድ ታጁዲንም አጠናክረውታል። ጠቅላይ ምክር ቤቱ እስካሁን የዘካ፣ የወቅፍ፣ የሀጅ ኮሚሽን፣ የልማት እና የተራድኦ ኮሚሽን እንደሌለው ገልጸው እኒህን መሰል ከስራ ተግባራቱ የሚያያዙ ተቋማት ሊያቋቋም እንደሚችል አመላክተዋል። የተቋማቱን ምንነት “ከአሁኑ ተንብዮ ማስቀመጥ አይቻልም” ሲሉም አክለዋል። ለገለጻቸው ምሳሌ ሲያጣቅሱም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በፍትሐ ብሔር በአዋጅ ስትቋቋም “ማህበረ ቅዱሳን አቋቋማለሁ ብላ ተንብያ አልነበረም” ብለዋል።

ተጨማሪ ገቢ – እንዴት? 

ረቂቅ አዋጁ የመጅሊሱን በጀት አሸፋፈን በዘረዘረበት ድንጋጌ ላይ የጠቀሰው “የተጨማሪ ገቢ” አሰባሰብ አካሄድ ሌላው የዕለቱ አከራካሪ ጉዳይ ነበር። አዋጁ “የምክር ቤቱ በጀት ከሀገር ውስጥና ከውጪ ሀገር በሚገኙ ስጦታዎች፣ ከሙስሊሙ ማህበረሰብ በሚሰበሰቡ መዋጮዎች፣ በሃይማኖቱ ከተፈቀዱ የአገልግሎት ክፍያዎችና እርዳታዎች  የሚሸፍን ይሆናል” ይላል። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ምክር ቤቱ “በተጨማሪም ገቢ በሚያስገኙ ስራዎች ላይ መሰማራት” እንደሚችልም አዋጁ ይደነግጋል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ጥያቄ ያነሱ አንድ አባል አዋጁ “ተጨማሪ ገቢ የሚያስገኙ ስራዎች” የሚለውን በግልጽ አለማስቀመጡ ወደፊት ችግር እንደሚፈጥር ተናግረዋል። ስራዎች ሲባል “አስመጪነት እና ላኪነትን ይጨምራል ወይ?” ሲሉ እንዴት የህግ ትርጉም ክፍተት ሊፈጠር እንደሚችል ለማስረዳት ሞክረዋል። “እርሱ ነገር ካልጠራ ምክር ቤቱ ራሱ ወደ ተግባር በሚገባበት ጊዜ ችግር ሊያጋጥመው ይችላል” ሲሉ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል። 

ከህግ ፍትህና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በጽሁፍ ከቀረቡ ጥያቄዎች መካከል በአንዱ ተመሳሳይ ሀሳብ ተንጸባርቋል። ምክር ቤቱ ተጨማሪ ገቢ በሚያስገኙ ስራዎች ላይ መሰማራት እንደሚችል መቀመጡ “በተቋሙ ስም መነገድ ይችላል ማለት ነውን?” የሚል ጥያቄን አስነስቷል። ህገወጥነትን ለመከላከል ሲባል “ህጋዊ ስራዎች” በሚል አገላለጽ ቢቀመጥ እንደሚሻልም በጥያቄው ተጠቁሟል። ሌላ የምክር ቤት አባል በበኩላቸው ማንም ገንዘብ ያለው በንግድ፣ በኢንቨስትመንት እና በሌሎች መሰል ህጎች መስራት እንደሚችል መደንገጉን አስታውሰዋል። እንዲህ አይነት አካሄድ እያለ ለምን “ገቢ ማስገኛ ስራ” ብለን “ከሃይማኖቱ ጋር ለምን እናያይዘዋለን?” ሲሉ ጠይቀዋል። 

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ጸሀፊ አቶ ቃሲም መሐመድ ጠቅላይ ምክር ቤቱ በቂ የገንዘብ አቅም ከሌለው ለምዕመናኑ አገልግሎቱን በአግባቡ ሊሰጥም ሆነ በሀገር ልማት መሳተፍ እንደማይችል ገልጸዋል። ለዚህም ተጨማሪ ገቢ እንደሚያስፈልገው ገልጸው ሆኖም “ቀጥታ አስመጪ እና ላኪነት ይገባል ብሎ ማሰቡ far fetched ነው። ራቅ ይላል” ሲሉ ይህን ጉዳይ ላነሱ የምክር ቤት አባል ምላሽ ሰጥተዋል። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እየተገበረ ያለውን ህንጻ ሰርቶ የማከራየት የገቢ ማስገኛ አካሄድ እንደ ጥሩ ተሞክሮ እንደሚወስዱት ተናግረዋል። ምክር ቤቱ “ህጋዊ የሆኑ ሌሎች የገቢ ማስገቢያ ዘዴዎች ይጠቀማል” ሲሉም ለምክር ቤቱ አባላት አስረድተዋል።     

ሁለት ሰዓት ገደማ የፈጀው የጥያቄ እና ማብራሪያ ስብሰባ የተጠናቀቀው “ተገቢነት አላቸው” የተባሉ የአገላለጽ ማስተካከያዎችን በአዋጁ ላይ ለማድረግ ከስምምነት ላይ በመድረስ ነበር። ጠቅላይ ምክር ቤቱ አዋጁን ለማስፈጸም የሚያስፈልጉትን ደንብ እና መመሪያዎች እንዲያወጣ የቀረበው ሀሳብም ተቀባይነት አግኝቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)