በሐይማኖት አሸናፊ
ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ ተሟጋች ተቋም አምንስቲ ኢንተርናሽናል በኢትዮጵያ የጸጥታ ኃይሎች ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን እያደረሱ መሆኑን የሚያጋልጡ ማስረጃዎች ይፋ አደረገ። የሰብአዊ መብት ጥሰቶቹ በተለይም በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች የከፉ መሆናቸውን ተቋሙ አስታውቋል።
አምንስቲ ይህን ያስታወቀው በኢትዮጵያ ለአንድ አመት የደረገውን የሰብአዊ መብቶች ክትትል በተመለከተ ዛሬ አርብ ግንቦት 21፤ 2012 ባወጣው ሪፖርት ነው። ሰባ ሁለት ገጾች ያለው ሪፖርቱ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ እና ምዕራብ ጉጂ ዞኖች እንዲሁም በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን እስከ ካለፈው ታህሳስ ወር ድረስ ያለውን የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ገምግሟል።
ተቋሙ ለሪፖርቱ ጥንቅር ሰማንያ ግለሰቦችን ከአዲስ አበባ፣ ጎንደር፣ ሃርቀሎ፣ ባላምቤል፣ አዶላ፣ ሻኪሶ እና ሃዋሳ ከተሞች በቃለ መጠየቅ ማሳተፉን ገልጿል። ከሰማንያዎቹ ውስጥ አብዛኞቹ “በፀጥታ ኃይሎች ጥቃት የደረሰባቸው ናቸው” ተብሏል። ጥቃት ከተፈጸመባቸው ውስጥ ሃያ አንዱ ሴቶች መሆናቸውን ያመለክተው ሪፖርቱ ከእነርሱ ውስጥም አርሶ አደሮች፣ አርብቶ አደሮች፣ ነጋዴዎች፣ ተማሪዎች፣ የመንግስት ሰራተኞች፣ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች እና መምህራን እንደሚገኙበት ጠቁሟል።
በምዕራብ እና ደቡብ ኦሮሚያ የነበሩት ግጭቶች ከቀድሞው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ወታደራዊ ክንፍ በተገነጠለው፤ ራሱን የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ብሎ በሚጠራው ኃይል እና በመንግስት ጦር መካከል የተደረጉ እንደነበሩ አምንስቲ አስታውቋል፡፡ የምዕራብ ኦሮሚያ ክፍል ሆሮ ጉዱሩ፣ ምዕራብ ወለጋ፣ ምስራቅ ወለጋ፣ ቄለም ወለጋ ዞኖችን የያዘ ሲሆን ደቡብ ኦሮሚያ በበኩሉ ምስራቅ ጉጂ፣ ምዕራብ ጉጂ እና ቦረና ዞኖችን ያቀፈ ነው።

በጉጂ ተፈጸሙ የተባሉ “ግድያዎች”
አምንስቲ ኢንተርናሽናል አገኘሁት የሚለው የስም ዝርዝር እንደሚያሳየው ከጥር 2011 በኋላ ብቻ በምስራቅ እና በምዕራብ ጉጂ ዞኖች ውስጥ 39 ሰዎች በጸጥታ ኃይሎች ተገድለዋል። የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋሙ በምስራቅ ጉጂ፤ በጎሮ ዶላ ወረዳ እና በምዕራብ ጉጂ፤ ዱግዳ ዳዋ ወረዳዎች ውስጥ ከተገደሉት ሰዎች ውስጥ 23ቱ በኦሮሚያ ፖሊስ እና በመከላከያ ሰራዊት አባላት እጅ ህይወታቸው ለማለፉ ማረጋገጫ እንዳለው ገልጿል።
“በዱግዳ ዳዋ ወረዳ 16 ሰዎች በጸጥታ ኃይሎች ህይወታቸው ለማለፉ አምንስቲ አሳማኝ መረጃ በእጁ ይገኛል” የሚለው ሪፖርቱ “በጎሮ ዶላ ወረዳ ከተገደሉት ሰዎች መካከል አራቱ የሚዛመዱ ሲሆኑ ቤተሰቦቻቸውም ላልተገባ እስር ኢላማዎች ነበሩ” ሲል አክሏል።
ሪፖርቱ “ጥቅምት 8፤ 2012 ከታሰሩበት ተወስደው ተገድለዋል” ያላቸውን የሶስት ሰዎች ማንነትም ይፋ አድርጓል። “በራሮ ቀበሌ ታስረው ነበር” የተባሉት ሟቾች የ42 ዓመቱ ጨደቻ ሚኤሳ ሃላሊኬ፣ የ15 እና የ16 ዓመት ታዳጊዎች የሆኑት አብዱላሂ ጎሉ ሃላሊኬ እና ቋንቄ ኡቱራ ሱሬ ናቸው። አብሯቸው ታስሮ የነበረውን ፈልማ ጃለታን በእማኝነት ይጠቅሳል።
“ህይወታቸው አልፏል ብዬ የማምንበት ምክንያት፤ ከምሽቱ 2 ሰአት አካባቢ ወታደሮቹ መጥተው ከመካከላችን ከወሰዷቸው ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ የተኩስ ድምፅ ተሰማ” ሲል ፈልማ ለአምንስቲ አስረድቷል። ይህንን የፈልማን የምስክርነት ቃል በለቱ ለማ የተባለ የአካባቢው ነዋሪም ያረጋግጣል። በራሮ ቀበሌ አጎቱ እና 11 የአጎቱ ልጆች ታስረው እንደነበር የሚገልጸው በለቱ፤ ከታሰሩበት ተወስደው የተገደሉ ሰዎች አስክሬን ተገኝቷል ይላል።
“አብዱላሂ ጎሉ እና ደቻሳ ሚኤሳ ከእነዚህ መካከል ሲሆኑ ቃንቄ ደግሞ ከኔ ጋር በጋብቻ ይዛመዳል፡፡ ሶስቱም ጥቅምት 8፤ 2012 ተገድለው በራሮ ቀበሌ ነው የአካባቢው ነዋሪዎች ሬሳቸውን ያገኙት፡፡ ደቻሳ ባለትዳር እና የ 12 ልጆች አባት ነበር” ሲል በለቱ ለአምንስቲ ተናግሯል። በወቅቱ ታስረው የነበሩት ግለሰቦች ቁጥጥር ስር የዋሉት በአካባቢው የሚንሳቀሰውን “የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ወይም ሸኔን ደግፋችኋል” በሚል እንደነበር ሪፖርቱ ጠቁሟል።
“ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ይሆናል ተኩሱን የሰማሁት። በጠዋት በወታደሮቹ ካምፕ አካባቢ ሄደን ሬሳውን አገኘነው። እጅ እና እግሩ ተሰብሯል፤ መደብደቡም ያስታውቃል”
ቦና ጃለታ (የዘመዱን አሟሟት ለአምንስቲ የገለጸ የኦሮሚያ ክልል ነዋሪ)
የአምንስቲ ሪፖርት በሸኔ ደጋፊነት ተጠርጥሮ ከታሰረ በኋላ ተገደለ የተባለን የ28 ዓመት አርሶ አደር ታሪክም አካትቷል። ባለ ትዳር እና የሶስት ልጆች አባት የነበረው ቦዲሻ ጪሉቄ የእርሻ ስራውን እያከናወነ ነበር ወታደሮች ፈልገውት ወደ ቤቱ መጥተው እንደነበር ያወቀው። ለምን እንደፈለጉት ለመጠየቅ ወደ ወታደሮቹ ሲሄድ ተይዞ በአቅራቢያው ወዳለ የወታደሮች ካምፕ መወሰዱን ተከትሎት የሄደ የቤተሰብ አባል ይናገራል። ቦዲሻን ለማነጋገር ሲሞክር ከዚያ በወታደሮቹ መከልከሉን የሚገልጸው የቤተሰብ አባል ለዚህም የተሰጠው ምክንያት “የሸኔ ደጋፊ ነው” የሚል እንደነበር ያስረዳል፡፡
የቦዲሻ ዘመድ የሆነው ቦና ጃለታ፤ በዕለቱ የጥይት ድምፅ መስማቱን እና ቦዲሻ ይሆናል ብሎ መስጋቱን ለአምንስቲ ገልጿል። ነገር ግን በአካባቢው የሰዓት እላፊ በመጣሉ ምክንያት ወጥቶ ለማረጋገጥ አለመቻሉን መለስ ብሎ ያስታውሳል። “ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ይሆናል ተኩሱን የሰማሁት። በጠዋት በወታደሮቹ ካምፕ አካባቢ ሄደን ሬሳውን አገኘነው። እጅ እና እግሩ ተሰብሯል፤ መደብደቡም ያስታውቃል። ሽማግሌዎች ጣልቃ እስከሚገቡ ድረስም ሬሳውን እንዳናነሳ ወታደሮቹ ከልክለውን ነበር” ይላል ቦና።
የቀብር ስነስርአቱ በከተማ ውስጥ ቢካሄድም “ለሸኔ ልታቀብሉ ነው” በሚል ለለቀስተኛው ምግብ እና ውሃ እንዳይወስዱ መከልከላቸውን ተናግሯል። በአካባቢው ባህል መሰረትም በቀብር ላይ በሬ የሚታረድ ቢሆንም፤ ወታደሮች በሬውንም ወደ ቀብር እንዳይወስዱ እንዳገዷቸው አክሏል።
አምንስቲ ከዚህ በተጨማሪ በጉጂ ባሉ አካባቢዎች በመከላከያ ሰራዊት ስለተገደሉ ሰዎች የቅርብ ዘመዶቻቸውን እና የአይን እማኞችን በመነጋገር በርከት ያሉ ታሪኮችን በሪፖርቱ አስፍሯል። በአካባቢዎቹ ሰፋፊ የጅምላ እስሮች እንዳሉ እና የተያዙ ሰዎች መብቶች እንደማይጠበቁም ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል።

ከቅማንት ጋር የተያያዙ ግጭቶች በጎንደር
የአምንስቲ ሪፖርት በአማራ ክልል ተፈጽመዋል ያላቸውን ግድያዎች እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ዘርዝሯል። የቅማንትን ማንነት ለማስመለስ የተቋቋመው ኮሚቴ ያነሳው የማንነት ጥያቄ ደም አፋሳሽ ግጭቶችን ማስከተሉን ሪፖርቱ ገልጿል። ኮሚቴው “በጎንደር የሚገኙ 126 ቀበሌዎች በቅማንት ብሔረሰብ ስር ሊሆኑ ይገባል” የሚል ጥያቄ ቢያነሳም ረጅም ግዜ ከፈጀ ድርድር የየብሔረሰብ ጥናት በኋላ ህዝበ ውሳኔ ተካሂዶ 72 ቀበሌዎች በቅማንት ልዩ ዞን ስር እንዲቋቋሙ ተደርጓል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ በመስከረም 2010 በስምንት ቀበሌዎች ባካሄደው ህዝበ ውሳኔ ጉባይ፣ መቃ እና ልንጫ የተባሉት ቀበሌዎች ከሌሎች የቅማንት አካባቢዎች ጋር በመልክዓ ምድር አቀማምጥ ባይገናኙም አብዛኛው ነዋሪ የቅማንትን ማነንት መርጠዋል። ይህንንም የህዝበ ውሳኔ ውጤት የፌዴሬሽን ምክር ቤት በጥቅምት 2010 አጽድቆታል።
ሆኖም የአማራ ክልል ባለስልጣናት ሶስቱ ቀበሌዎች “በሚዋቀረው የቅማንት ልዩ ዞን ውስጥ መካተት አይችሉም” የሚል ክርክር አቅርበዋል። የቅማንት አክቲቪስቶች በበኩላቸው ሶስቱ ቀበሌዎቹ “ምንም እንኳን ከሌሎቹ በቅማንት ልዩ ዞን ውስጥ ከሚካተቱት ቀበሌዎች ጋር ባይዋሰኑም የዞኑ አካል መሆን አለባቸው” ሲሉ ተሟግተዋል። ይህ የሀሳብ ልዩነት በቅማንት እና በአማራ ማህበረሰቦች መካከል ውጥረቶችን የፈጠረ ሲሆን በማህበረሰቦቹ መካከል ግጭቶች እንዲቀሰቀስ ምክንያት ሆኗል።

በአማራ ክልል በምዕራብ እና በመካከለኛው ጎንደር በተለይም በፀገዴ፣ በጭልጋ፣ በቋራ እና በመተማ አካባቢዎች በተቀሰቀሰ ግጭት ሞት፣ የአካል ጉዳት ብሎም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከሁለቱም ወገኖች መፈናቀል አስከትሏል። በምዕራብ እና ማእከላዊ ጎንደር ዞኖች ውስጥም በአማራ እና በቅማንት ማህበረሰቦች መካከል ከመስከረም 2011 እስከ ጥቅምት 2012 የዘለቁ ግጭቶች ተከስተዋል።
እንደ አምንስቲ ሪፖርት ገለጻ በእነዚህ ጊዜያት የክልሉ የልዩ ፖሊስ አባላት እና የቀበሌ ሚሊሺያዎች፤ በቋራ፣ መተማ እና ጭልጋ የቅማንት ማህበረሰብ አባላትን ኢላማ ባደረጉ ጥቃቶች ላይ ተሳትፈዋል። ግጭቶቹ በበረቱባቸው አካባቢዎች ካምፖች መስርተው ያሉ የመከላከያ ሰራዊት አባላትም ከአካባቢው ነዋሪዎች ጥሪ ቢደረግላቸውም “በፍጥነት ጥቃቶቹን ለማስቆም ምላሽ አልሰጡም” ሲል ሪፖርቱ ይከስሳል።
በመተማ ከተማ፤ በጥር ወር 2011፤ በ24 ሰአታት ውስጥ ብቻ 58 ሰዎች ህይወታቸው ሲያልፍ፣ በጅምላ መቃብር መቀበራቸውንም አምንስቲ በሪፖርቱ አጋልጧል። ከጎንደር ከተማ የጸጥታ ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየውም መስከረም 18፤ 2012 በጎንደር እና አካባቢው በነበረ ግጭት የ43 ሰዎች ህይወት አልፏል፤ 12 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል። የሰዎችን ህይወት የቀጠፉት ግጭቶች አዘዞ፣ 18 ቀበሌ፣ ቁስቋም፣ አራዳ፣ ማለዲባ እና ወለቃ በተባሉ ቦታዎች የተከሰቱ መሆናቸውን ሪፖርቱ ዘርዝሯል።
ለአምንስቲ አስተያየታቸውን የሰጡት የአማራ ክልል የሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ እንደሚሉት ግን የፀጥታ ኃይሎች ጣልቃ ባይገቡ ኖሮ ጉዳቱ ከዚህም ሊብስ ይችላል። ኃላፊው “የፀጥታ ኃይሎቹ በጎንደር ከተማ በነበረው ጥቃት ተባባሪ ነበሩ” የሚለውን ክስ ውድቅ አድርገውታል። ከሁለቱም ወገን በግጭቱ የተጠረጠሩ 90 ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለው የነበረ ቢሆንም የክልሉ መንግስት ነፍስ በማጥፋት ከተጠረጠሩት ውጪ ሌሎቹን ከእስር ፈትቷል። ለዚህም እንደምክንያት የተሰጠው የህዝብ ለህዝብ እርቅ ለማውረድ ጉባኤዎች መደረጋቸው ነው።

መንግስት እነዚህን መሰል ግጭቶች ለመቆጣጠር በየአካባቢው ኮማንድ ፖስቶችን ማቋቋሙን ሪፖርቱ አስታውሷል። የተለያዩ የጸጥታ ሁኔታዎችን መሰረት በማድረግ በሶስት ክልሎች ውስጥ የተዋቀረው ኮማንድ ፖስት በአማራ ክልል ሶስት ቦታዎች፣ በኦሮሚያ ክልል ደግሞ ሁለት ቦታዎች መቋቋሙን ገልጿል። በደቡብ ክልል ደግሞ አንድ አጠቃላይ ኮማንድ ፖስት ተቋቁሞ፤ እንደ ሌሎቹ አካባቢዎች የተለያዩ የጸጥታ ኃይሎች የማቀናጀት ስራ እየሰራ ይገኛል።
እነዚህ ኮማንድ ፖስቶች “ሰብአዊ መብቶችን በዘፈቀደ ወይም ያለ ፍርድ ቤት ፈቃድ የመገደብ ስልጣን አላቸው” ብሏል አምንስቲ። የኮማንድ ፖስቶቹ ኃላፊዎች የተወሰኑ ባንዲራዎችን ከመያዝ እንደሚያግዱ፣ ሞባይል ስልኮችን መጠቀም እንደሚከለክሉ አሊያም እንደሚወርሱ ሪፖርቱ ያስረዳል። ኮማንድ ፖስቶቹ የሰአት እላፊ እና የእንቅስቃሴ ገደብ የመጣል፣ የፍተሻ ኬላዎችን የማዘጋጀት እና አንዳንዴም ኃይልን በመጠቀም ሰዎችን ያለፈቃዳቸው የማፈናቀል ስልጣን እንዳላቸውም ያብራራል።
የጅምላ እስር
በኦሮሚያ ክልል የተቋቋሙት ኮማንድ ፖስቶች ሸኔን እና አባ ቶርቤን በመደገፍ፣ በመመገብ እንዲሁም መረጃ በማቀበል በጠረጠሯቸው ግለሰቦች ላይ “የጅምላ እስሮችን ፈጽመዋል” ሲል አምንስቲ በሪፖርቱ ወንጅሏል። አምንስቲ ለዚሁ ጥናት ያነጋገራቸው የፀጥታ ኃይሎችም ሁሉም የጅምላ ታሳሪዎች “ሸኔን በመደገፍ፣ መረጃ በመስጠት እና በመመገብ የተጠረጠሩ” መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
በምዕራብ እና ምስራቅ ጉጂ የሚፈጸሙ የጅምላ እስሮችን የሚያከናውኑት የቀበሌ ሚሊሺያዎች፣ የኦሮሚያ ፖሊስ እና የመከላከያ ሰራዊት አባላት እንደሆኑ የሚጠቁመው ሪፖርቱ በእስረኞቹ ላይ ክስ እንዳማይመሰረት፣ ጠበቃ ማግኘት እንደማይችሉ እንዲሁም ያለ ምንም ፍርድ ለወራት ተይዘው እንደሚቆዩ ያብራራል። ከጅምላ እስር ባሻገርም የጸጥታ ኃይሎቹ ለማሰር የፈለጉትን ሰው ማግኘት ሳይችሉ ሲቀሩ የቤተሰብ አባላትን መያዝ እና መኖሪያ ቤት እንደሚያወድሙም አምንስቲ ገልጿል፡፡
ኮማንድ ፖስቶቹ ከምስራቅ እና ምዕራብ ጉጂ ብቻ ሳይሆን ከመላው ኦሮሚያ “በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በጅምላ አስረዋል” ሲል የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋሙ ይወነጅላል። እስረኞቹም በጦላይ የወታደሮች ማሰልጠኛ እና በሰንቀሌ የፖሊስ ማሰልጠኛ ካምፖች ውስጥ እንዲቆዩ እንደሚደረግ አትቷል።
በጦላይ ብቻ ከጥር 2011 እስከ መስከረም 2012 ባሉት 9 ወራት ውስጥ ብቻ ከ10 ሺህ የማያንሱ ሰዎች ተይዘው እንደነበር አምንስቲ የሰበሰባቸው ማስረጃዎች አረጋግጠዋል። ኢትዮጵያ ካወጣቻቸው የአገር ውስጥ ህጎችም ሆነ ከተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ህጎች ጋር በሚጣረስ መልኩ እነዚህ እስረኞች ወደ ፍርድ ቤት እንደማይቀርቡ እና ክስም ሳይመሰረትባቸው እስከ 5 ወር ድረስ በእስር እንደሚቆዩ አምንስቲ ገልጿል።

የጅምላ እስሮቹ በወታደራዊ ካምፖቹ ውስጥ ብቻ ሳይሆኑ በፖሊስ ጣቢያዎች ውስጥም እንደሚፈጸሙ የአምንስቲ ሪፖርት ይጠቁማል። ይህንንም ከሚያስረዱት የዓይን እማኞች መካከል በምስራቅ ጉጂ፤ ጎሮ ዶላ ወረዳ፤ በራሮ ቀበሌ አርሶ አደር የሆኑት ቦሩ ሃላሊኬ ይገኙበታል። የ42 አመቱ ጎልማሳ “ሸኔን ትደግፋለህ” በሚል ጥርጣሬ በተደጋጋሚ ሲታሰሩ እንደነበር ያስረዳሉ፡፡
“ኮማንድ ፖስቱ ከተቋቋመ በኋላ ፖሊስ ሃርቄሎ ጣቢያ አራት ጊዜ አስሮኛል። በእስር ወቅት በፖሊስ የሚነገረኝ ‘ከሸኔ ተዋጊዎች ጋር ግንኙነት አለህ ወይም ትደግፋለህ ወይም ትመግባለህ’ የሚል ነው። በመጨረሻ ከእስር ስለቀቅም 10 ሺህ ብር ዋስ በማስያዝ ነው። ፖሊሶቹ አስሮ ከማቆየት ውጪ፤ እንኳን ፍርድ ቤት ሊወስዱኝ ጥያቄ እንኳን አይጠይቁኝም ነበር” የደረሰባቸውን ለአምንስቲ ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የኖቤል ተሸላሚ መሆናቸውን በመቃወም ለ“አሜሪካ ድምፅ” ራዲዮ የአፋን ኦሮሞ አገልግሎት ቃለ ምልልስ የሰጡት ሁሴን ገለሞም በሃርቄሎ ፖሊስ ጣቢያ ተይዘው መቆየታቸውን ያስረዳሉ። “የኦሮሚያ ፖሊስ አባላት ከ2011 ጀምሮ ደጋግመው አስረውኛል። ቃለ ምልልሱን ካደረግኩ ከቀናት በኋላም ለሁለት ሳምንት ያክል ጎሮ ዶላ ፖሊስ ጣቢያ ታስሬ ቆይቻለሁ” ብለዋል።
በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች የሚያዙ እስረኞች ቤተሰቦቻቸው ለፍርድ ቤት አቤቱታ ቢያሰሙም፤ ፖሊስ ፍርድ ቤት እንደማያቀርባቸው እና ለዚሀም የተያዙት በኮማንድ ፖስቱ መሆኑን ጠቅሰው መልስ እንደሚሰጡ ነዋሪዎች ገልጸዋል። በነገሌ ከተማ ታስሮ የነበረው አብዱራህማን አህመድ በወቅቱ ለፍርድ ቤት አቤት ቢልም ፍርድ ቤቱ ከግምት እንዳልከተተለት ለአምንስቲ አስረድቷል።
በተመሳሳይ በነገሌ ፖሊስ ጣቢያ ለአንድ ወር ታስሮ ኋላ ላይ ወደ ሰንቀሌ የወታደሮች ማሰልጠኛ የተወሰደው ጉታ ብርሃኑም እሱ እና ሌሎች እስረኞች “በዋስ ለመፈታት ለዞን ፍርድ ቤት ማመልከታቸውን ያስታውሳል። “የኦሮሚያ ፖሊስ ለዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሰጠው መልስ፤ የታሰርነው በኮማንድ ፖስቱ ስለሆነ ቤቱ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን መመልከት እንደማይችል ገልጿል” ይላል። “ዳኛው ‘እኔ በዋስ ብለቅህ ኮማንድ ፖስቱ መልሶ ያስርሃል’ ብሎኛል፤ ከዚያ ፖሊሶቹ ወደ ሰንቀሌ ወሰዱኝ” ሲል ጉታ የደረሰበትን ለአምንስቲ ተናግሯል።
የእስረኞች አያያዝ ሁኔታ
ከነገሌ ፖሊስ ጣቢያ ወደ ሰንቀሌ የተወሰደው አብዱራህማን አህመድ “ሰንቀሌ ውስጥ የቆየሁት ለአንድ ወር ቢሆንም 30 አመት የቆየሁ ያህል ነው የሚሰማኝ” ይላል። በዚያው በሰንቀሌ፣ በሃርቄሎ፣ በፊንጫ ውሃ እና ጦላይ ታስረው የነበሩ ሰዎች የአብዱራህማንን ስሜት ይጋራሉ። በእነዚህ ቦታዎች በቂ ምግብ እና መኝታ እንደሌለ የቀድሞ ታሳሪዎች ይናገራሉ።
በሃርቄሎ ፖሊስ ጣቢያ ኮማንድ ፖስቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን አስሮ የነበረ ሲሆን ፖሊስ ጣቢያው በዚህ ምክንያት በከፍተኛ ሁኔታ ተጨናንቆ እንደነበር በቦታው የነበሩ ይናገራሉ። እንደ አምንስቲ ጥናት ከሆነ ፖሊስ ከአዋቂዎች ጋር ህፃናትን አብሮ የሚያስር ሲሆን ከፍተኛ የምግብ እጥረትም ነበር። አብዛኞቹ እስረኞች ራቅ ካሉ ቀበሌዎች የሚመጡ በመሆናቸው ከቤተሰቦቻቸው ምግብ አይቀርብላቸውም። በዚህ ምክንያትም የተወሰኑ የጣቢያው ፖሊሶች የአካባቢው ነዋሪ ለእስረኞች ምግብ እንዲያመጡ ይጠይቁ እንደነበር አምንስቲ በሪፖርቱ ጠቁሟል።
“በረሃብ ራሳቸውን ስተው የሚወድቁ እስረኞች ነበሩ”
በሰንቀሌ ታስረው የነበሩ እስረኞች
ይህ የምግብ እጥረት በሰንቀሌም መታየቱን የሚገልጸው ሪፖርቱ ከባድ ምርመራ እና ቅጣቶች መኖራቸውንም ያስረዳል። በሰንቀሌ ታስረው የነበሩ ሰዎች በቆርቆሮ በተሰሩት እስር ቤቶች ውስጥ እንዲውሉ በኦሮሚያ ፖሊስ ይገደዱ እንደነበር ለአምንስቲ ገልጸዋል። ጠዋት ለአጭር እረፍት፤ ምሽት ደግሞ መፀዳጃ ቤት ለመሄድ ብቻ ከቆርቆሮ ቤቶቹ ይወጡ እንደነበርም ይናገራሉ። ገላቸውንም በሳምንት አንድ ጊዜ ብቻ ነው እንዲታጠቡ ይፈቀድላቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።
እስረኞቹ በቀን ሶስት ዳቦ ብቻ የሚቀርብላቸው ሲሆን ለሶስት ተከታታይ ቀን ይህም ያልቀረበበት ጊዜ እንደነበር ገልጸዋል። በዚህ ወቅትም “በረሃብ ራሳቸውን ስተው የሚወድቁ እስረኞች ነበሩ” ይላሉ። በምግቡ ጥራት ላይ አቤቱታቸውን ያሰሙት የእስረኞች ተወካዮችም በኦሮሚያ ፖሊስ ድብደባ እንደደረሰባቸው ይናገራሉ። ከተወካዮቹ መካከል የሆነው አብዱራህማን እንደሚለው ይህንን ተከትሎ በነበረው የረሃብ አድማ ማስተባበር ምክንያት ተወካዮቹ ለብቻቸው ተገልለው እንዲቀመጡ እና ለሁለት ተከታታይ ቀናት ምግብ እንዳይቀርብላቸው ተደርጓል።
ጾታዊ ጥቃቶች በእስረኞች ላይ
በፊንጫ ውሃ ታስራ የነበረቸው ሞሚና ሮባ እርሷን ጨምሮ እስረኞች “የሸኔ ተዋጊዎችን ትደግፋላችሁ” በሚል በመከላከያ ሰራዊት አባላት እንደሚደበበደቡ ተናግራለች። በቁጥጥር ስር ስትውል የአራት ወር እርጉዝ የነበረችው ሞሚና በደረሰባት ድብደባ ፅንሱ እንደተቋረጠም ትገልጻለች።
“ድብደባ ማታ ማታ የሚከናወን ሲሆን፣ ከታሰርንበት ክፍል አውጥተው ጠጠር ላይ እንድንበረከክ በማድረግ ይመቱናል። እኔም በታሰርኩበት ቀን እና በማግስቱ ተደብድቤያለሁ። ነፍሰጡር መሆኔን ስነግራቸው፤ ነፍሰ ጡር መሆን ያለመሆኔ ልዩነት እንደሌለውና ሊገድሉኝም እንደሚችሉ ነገሩኝ” ስትል ሞሚና የደረሰባትን ለአምንስቲ አስታውቃለች።
በፊንጫ ውሃ ለአንድ ወር ከቆየች በኋለ ወደ ሰንቀሌ የተሸጋገረቸው ሞሚና እዚያ ከደረሰች በኋላ ፅንሱ መቋረጡን እና ይህም በፊንጫ ውሃ በነበረው ድብደባ እና በሰንቀሌ በነበረው አያያዝ መሆኑን አብራርታለች። ፅንሱ ከተቋረጠ በኋላም ህክምና ያለማግኘቷን ለአምንስቲ ገልጻለች።
አምንስቲ ጥናቱን በሚያካሂድበት ወቅት የተለያዩ የጾታዊ ጥቃቶች እንደደረሱ መረጃ እንደደረሰው እና ይህም ለአቅመ ሄዋን ያልደረሱ ሴቶች ላይም ጭምር የተፈፀመ ስለመሆኑ በሪፖርቱ ላይ አስፍሯል። ነገር ግን ብዙዎቹ ለመናገር እንደሚፈሩ እና ሁለት ሴቶች ግን ስለደረሰባቸው ጥቃት ለመናገር መድፈራቸውን ጠቁሟል። በሃርቄሎ ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ የመደፈር ሙከራ የደረሰባት አንድ ሴት እና በዱቂሳ መጋዳ ቀበሌ አስተዳደር ቢሮ ውስጥ በቡድን ተገዳ የተደፈረች ሌላ ሴት የደረሰባቸው ጥቃት በሪፖርቱ ተጠቅሷል።
ኤቢሴ ኤባ በጥር 2011 በሁለት የዱቂሳ መጋዳ ቀበሌ ሚሊሺያዎች መያዟን ለአምንስቲ ገልጻለች። ባለቤቷ እና ወንድሟ በመከላከያ ሰራዊት አባላት መገደላቸውን የምትናገረው ኤቢሴ ከዚያ በኋላ ተደብቃ መቆየቷን አስረድታለች። የያዟት ሚሊሺያዎች ስልኳን በመውሰድ በውስጡ ማስረጃ እንዳለው እና የመከላከያ ሰራዊት አባላት ይህንን ካዩ ሊገድሏት እንደሚችሉ እንደነገሯት ወደ ኋላ መለስ ብላ ታስታውሳለች።
“ለወታደሮቹ እንሰጥሻለን በሚል ማስፈራሪያ ከሁለቱም ጋር እንድገናኝ ተገደድኩ። አንደኛውን በቅፅል ስሙ ቀዮ ይባላል። በቀበሌው የሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ነው የሚሰራው። ሌላኛው የቀበሌው ሚሊሽያ አዛዥ ነው”
ኤቢሴ ኤባ (ተገድዳ መደፈሯን ለአምንስቲ ያስረዳች እስረኛ)
“ለወታደሮቹ እንሰጥሻለን በሚል ማስፈራሪያ ከሁለቱም ጋር እንድገናኝ ተገደድኩ። አንደኛውን በቅፅል ስሙ ቀዮ ይባላል። በቀበሌው የሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ነው የሚሰራው። ሌላኛው የቀበሌው ሚሊሽያ አዛዥ ነው” ስትል ኤቢሴ ለአምንስቲ ተናግራለች። በሄርቄሎ ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ የቆየችው ጫልቱም ፖሊሶች ምሽት ላይ ከመጸዳጃ ቤት ስትመለስ ይዘው አስገድደው ሊደፍሯት እንደሞከሩ ገልጻለች።
“ከመፀዳጃ ስመለስ ፖሊሶቹ ልጄን ለቤተሰቦቼ እንድሰጥ ጠየቁኝ። እኔም ልጄ ስለሚጠባ ያንን ማድረግ እንደማልችል ነገርኳቸው። እነሱም ይሄንን ያሉኝ ሸኔዎች ቢሆኑ እንደምስማማ እና ልጁንም ያመጣሁት ከእነሱ ጋር ላለመተኛት ብዬ እንደሆነ ተናገሩ። በዚህ መሃል ስሜታዊ ሆኜ መጮህ ጀመርኩ። መምታት ሲጀምሩ እና ስንታገል አለቀስኩ። ግብግቡን እና ድምፄን የሰሙ ወንዶች እስረኞች ግድግዳውን መደብደብ እና መጮህ ሲጀመሩ ጥለውኝ ሄዱ” ስትል ጫልቱ ተናግራለች።
የደረሰባቸውን ጥቃት ለአምንስቲ ያካፈሉ ሁለቱም ሴቶች ድርጊቱን የፈጸሙትን ወንዶች እንደሚያውቋቸው ቢገልጹም በቀልን በመፍራት ክስ ለመመስረት እንዳልቻሉ በሪፖርቱ ተመልክቷል።
የአምንስቲ መደምደሚያ
አምንስቲ ለአንድ አመት ያክል ያካሄደውን የሰብአዊ መብት ክትትል ሲያጠቃልል በኢትዮጵያ ከሰብዓዊ መብት አጠባበቅን በተመለከተ ማሻሻያዎች ቢኖሩም አሁንም በጸጥታ ኃይሎች የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች አሳሳቢ መሆናቸውን በመጥቀስ ነው። በጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አህመድ የሚመራው መንግስት ወደ ስልጣን ከመጣ ወዲህ እንደ ፀረ ሽብር እና የሲቪል ተቋማት ህጎች ያሉ ጨቋኝ ህጎችን በማሻሻል፣ በውጪ ያሉ የፖለተካ ኃይሎች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ በመፍቀድ፣ በሺህዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞችን በመፍታት እና በመሰል ተግባራት ያስመዘባቸውን ማሻሻያዎች አምንስቲ አድንቋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ማሻሻያዎቹን በመተግበር “አንድ እርምጃ ተራምዷል” የሚል እምነት ያለው አምንስቲ ሆኖም የቀድሞው ልምድ ያለቀቀው የጸጥታ ኃይሎች የኃይል አጠቃቀም “ጉዞው ረጅም ርቀት እንዳይሄድ አግዶታል” ብሏል፡፡ መንግስት በፀጥታ ኃይሎች እየደረሱ የሚገኙትን የስብአዊ መብት ጥሰቶች በፍጥነት እንዲያስቆምም ጠይቋል። “የጸጥታ ኃይሎች ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰዎችን መግደል፣ ማሰር ወይም ከመኖሪያ አካባቢያቸው በጉልበት ማፈናቀል እና የተቃዋሚ ኃይሎችን በመደገፍ የጠረጠሯቸውን ሰዎች ሃብት እና ንብረት ማውደም እንዲያቆሙ መንግስት በልዩ ሁኔታ ትዕዛዝ ሊሰጥ ይገባል” ሲል አምንስቲ አሳስቧል።
አምንስቲ ከዚህ በተጨማሪም “የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ደርሶባቸዋል” በተባሉ አካባቢዎች በገለልተኛ አካላት፣ ያለአድልዎ፣ ጥልቅ እና ተዓማኒነት ያላቸው ምርመራዎች እንዲደረጉ ጥያቄ አቅርቧል። በእነዚህ ምርመራዎች በቂ መረጃ ከተገኘ፤ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች “ወንጀሎችን የፈፀሙ አካላት ለህግ ቀርበው እንዲጠየቁ ሊያደርጉ ይገባል” ብሏል።
አምንስቲ በሰብአዊ መብት ክትትሉ የደረሰባቸው ግኝቶችን በተመለከተ ምላሽ እንዲሰጡ ለሰላም ሚኒስቴር፣ ለመከላከያ ሚኒስቴር፣ ለጠቅላይ አቃቤ ህግ፣ እና ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በደብዳቤ ጥያቄ ማቅረቡን በሪፖርቱ ጠቅሷል፡፡ ተመሳሳይ ደብዳቤዎች ለኦሮሚያ ክልል መስተዳድር፣ ለአማራ እና ኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽኖች፣ ለአማራ እና ለኦሮሚያ ክልል የፀጥታ ቢሮዎች መላኩንም አስታውቋል። ሆኖም ከእነዚህ ሁሉ የፌደራል እና የክልል መስሪያ ቤቶች ውስጥ ምላሽ የሰጠው የአማራ ክልል የሰላም እና የፀጥታ ቢሮ ብቻ መሆኑን ገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)