በተስፋለም ወልደየስ
በአማራ ክልል፤ ሰሜን ወሎ ዞን ስር ያለው የራያ ቆቦ ወረዳ አስተዳዳሪ እና የጸጥታ ዘርፍ ኃላፊ ማንነታቸው ባልታወቀ ሰዎች ተገደሉ። ሁለቱ የወረዳ አመራሮች የተገደሉት ከቆቦ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኝ እና ልዩ ስሙ መንጀሎ ተብሎ በሚታወቅ ቦታ ዛሬ እሁድ ግንቦት 23፤ 2012 ነው።
የሰሜን ወሎ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ወልደትንሳኤ መኮንን በሁለቱ ኃላፊዎች ላይ የተፈጸመውን ግድያ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። የራያ ቆቦ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ስዩም መስፍን እና የወረዳው የጸጥታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ መንገሻ ሞላ በቅርቡ የተሾሙ ወጣት አመራሮች መሆናቸው የገለጹት አቶ ወልደትንሳኤ ኃላፊዎቹ የተገደሉት በመንገድ ላይ እያሉ በጥይት ተመትተው መሆኑን ገልጸዋል።
ሁለቱ የወረዳ ኃላፊዎች እስከ ቀኑ ሰባት ሰዓት ድረስ ከእርሳቸው እና ሌሎች አመራሮች ጋር በወልዲያ ላይ በስብሰባ ላይ መቆየታቸውን የሚናገሩት የዞኑ አስተዳዳሪ ከአንድ ሰዓት ገደማ በኋላ መሞታቸውን በስልክ መስማታቸውን አስረድተዋል። ኃላፊዎቹ በጥይት ከተመቱ በኋላ “ወዲያውኑ ነው የሞቱት” ሲሉ አቶ ወልደትንሳኤ የአመራሮቹን አሟሟት አብራርተዋል።
የኃላፊዎቹ የግድያ መንስኤ ነው የተባለው ጉዳይ በፖሊስ እየተጣራ መሆኑን የዞኑ አስተዳዳሪ ተናግረዋል። ሆኖም ከአካባቢው የወጡ መረጃዎች፤ ኃላፊዎቹ የተገደሉት “በርካታ ሰዎች እና ህገ ወጥ ዕቃዎችን ጭኖ ነበር የተባለን ባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪ (ባጃጅ) ለማስቆም በሚሞክሩበት ወቅት” መሆኑን አመላክቷል።
አቶ ወልደትንሳኤ ይህንን መረጃ እርሳቸውም መስማታቸውን እና የተባለው ታርጋ የሌለው ባጃጅም በቁጥጥር ስር መዋሉን እንደሚያወቁ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት ገዳዮቹን ለመያዝ በፖሊስ አሰሳ እየተደረገ መሆኑንም አክለዋል።
በራያ ቆቦ የኮሮና ቫይረስን ስርጭትን ለመቆጣጠር የሶስት እግር ተሽከርካሪዎች ከአንድ ሰዎች በላይ እንዳይጭኑ እገዳ እንደተጣለባቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ። በወረዳው ከሰሞኑ በኮሮና ቫይረስ መያዙ ከተረጋጋጠ የድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ ሰዎችን በለይቶ ማቆያ አስቀምጦ በተደረገ ምርመራ ሁለት ግለሰቦቹ በቫይረሱ መያዛቸው ተደርሶበታል።
ከትናንት በስቲያ አርብ እና ትላንት ቅዳሜ የምርመራ ውጤታቸው የታወቀው ሁለቱ ግለሰቦች በአሁኑ ወቅት በቆቦ ሆስፒታል የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው ነው ተብሏል። የተገደሉት የራያ ቆቦ የወረዳ ኃላፊዎች የተሳተፉበት የዛሬው የወልዲያ ስብሰባም በአካባቢው ያለውን የኮሮና ቫይረስ የስርጭት ሁኔታ የገመገመ እንደነበር የሰሜን ወሎ ዞን አስተዳዳሪ ተናግረዋል። ስብሰባው የኮሮና ቫይረስ ወደ ህብረተሰቡ እንዳይስፋፋ መደረግ ስላለባቸው ዝግጅቶች ከመከረ በኋላ ተጠናቅቋል ብለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)