የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከ3.2 ቢሊዮን ብር በላይ የግብር ዕዳ ተሰረዘለት

ለረዥም ዓመታት የተጓተቱ በርካታ ግንባታዎችን በማከናወን ላይ ያለው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከ3.2 ቢሊዮን ብር በላይ የግብር ዕዳ ተሰረዘለት። የገቢዎች ሚኒስቴር ለኮርፖሬሽኑ ዕዳውን የሰረዘው መንግስታዊው ድርጅት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሊያሳድርበት የሚችለውን ጫና ተቋቋሞ በግብር ከፋይነት እንዲቀጥል ለማድረግ ታስቦ እንደሆነ አስታውቋል። 

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ቅዳሜ ግንቦት 22፤ 2012 ለኮርፖሬሽኑ በጻፈው ደብዳቤ፤ ድርጅቱ እስከ 2007 ዓ.ም. በጀት አመት መክፈል የነበረበት የንግድ ትርፍ እና የተጨማሪ እሴት ታክስ ዕዳ ድምር መጠን 3.26 ቢሊዮን ብር መሆኑን አስታውሷል። ኮርፖሬሽኑ ካለበት የግብር ዕዳ ነጻ እንዲሆን የተደረገው በመንግስት በተሰጠ ውሳኔ መሰረት መሆኑን ደብዳቤው ጠቁሟል።

የገቢዎች ሚኒስቴር የጠቀሰው የመንግስት ውሳኔ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የተላለፈው ባለፈው ሚያዝያ ወር ውስጥ ነው። የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሚያዝያ 22፤ 2012 ባሳለፈው ውሳኔ ለ3,099 ግብር ከፋዮች መክፈል የነበረባቸውን ውዝፍ ግብር ሰርዟል። ይኸ የዕዳ ስረዛ ዋና ግብር፣ ወለድ እና ተያያዥ ቅጣቶችን ይጨምራል። ለግብር ከፋዮቹ ዕዳው የተሰረዘላቸው የኮሮና ወረርሽኝ ያሳደረውን ጫና ለመቋቋም ይችሉ ዘንድ እንደሆነም በወቅቱ ተጠቅሶ ነበር። 

ለኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን የግብር ምህረት የተደረገለት በተመሳሳይ ምክንያት መሆኑን የገቢዎች ሚኒስቴር በደብዳቤው ገልጿል። የኮሮና ቫይረስ የማህበራዊ እና ሰብዓዊ ቀውስ ከመፍጠሩም በተጨማሪ ከባድ የኢኮኖሚ ችግር ማስከተሉን ደብዳቤው ይጠቅሳል። 

“በኢኮኖሚው መዳከም ምክንያት ግብር ከፋዮች ስራቸውን ለማቆም ስለሚገደዱ፣ በርካታ ዜጎች ከስራ ስለሚፈናቀሉ፣ ለከፍተኛ የኢኮኖሚ ችግር [ይዳርጋል]” ሲል ደብዳቤው ያስገነዝባል። በዚህም ምክንያት “ግብር ከፋዮች ያለባቸውን ውዝፍ የታክስ ዕዳ በማቃለል፤ ለታክስ ክፍያ ሊያውሉት ይገባ የነበረውን ገንዘብ ለሥራ ማስኬጃ በማዋል በግብር ከፋይነት እንዲቀጥሉ ለማድረግ እንዲችሉ የታክስ ዕዳ ምህረት ማድረግ አስፈልጓል” ሲል ደብዳቤው አጽንኦት ሰጥቷል። 

በገቢዎች ሚኒስቴር የከፍተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ታሬሳ እንሴሱ ተፈርሞ ለኮርፖሬሽን የተላከው ደብዳቤ እንደሚያሳየው የግንባታ ድርጅቱ ከ1998 እስከ 2004 ዓ.ም. ባሉት አመታት መክፈል የነበረበት የንግድ ትርፍ፤ ፍሬ ታክስ፣ ወለድ እና ቅጣት ከ2 ቢሊዮን 689 ሚሊዮን ብር ደርሷል። በእነዚሁ አመታት ኮርፖሬሽኑ በተጨማሪ እሴት ታክስም ከፍተኛ ዕዳ እንደተመዘገበበት ደብዳቤው ያመለክታል። 

ድርጅቱ በተጠቀሱት ስድስት ዓመታት በተጨማሪ እሴት ታክስ፤ የፍሬ ታክስ፣ ወለድ እና መቀጫውን ጨምሮ መክፈል የነበረበት 578 ሚሊዮን ብር መሻገሩን የገቢዎች ሚኒስቴር ደብዳቤ ዘርዝሯል። መንግስት ለእነዚህ የድርጅቱ የግብር ዕዳዎች “ሙሉ ለሙሉ ምህረት ማድረጉንም” የከፍተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አስታውቀዋል።  

በኮሮና ወረርሽኝ ጫና ሳቢያ የግብር ዕዳ ስረዛ የተደረገለት ኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን በስሩ ከግንባታ ጋር የተያያዙ ሥራዎችም የሚያከናውኑ አራት ዘርፎችን ያቀፈ ነው። የውኃ መሰረተ ልማት ኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰኘው የድርጅቱ አንድ ክፍል በርከት ያሉ የተጓተቱ ፕሮጀክቶችን ግንባታ ሲያከናውን ቆይቷል። በ258 ሚሊዮን ብር ተጀምሮ ወጪው ወደ 1.2 ቢሊዮን ብር ያሻቀበው የጊዳቦ ግድብና መስኖ ልማት ግንባታ የተከናወነው በዚህ መስሪያ ቤት ነው። 

በኦሮሚያ እና ደቡብ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢ የተገነባው የጊዳቦ መስኖ ልማት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሥልጣን ላይ ሳሉ ተጀምሮ ከዘጠኝ አመታት በኋላ ጠቅላይ ሚኒስት አብይ አህመድ በተሾሙ ማግሥት ተመርቋል። በ1.6 ቢሊዮን ብር ተጀምሮ 3.7 ቢሊዮን ብር የወጣበት የርብ ግድብም የተሰራው በውኃ መሰረተ ልማት ኮንስትራክሽን ዘርፍ ነው። ከ5.6 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ፈሶበት ዛሬም ያልተጠናቀቀው የመገጭ መስኖ ግንባታንም የወሰደው ይሄው መስሪያ ቤት ነው። 

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን በአሁኑ አደረጃጀት የተቋቋመው፤ የኢትዮጵያ መንገድ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን እና የኢትዮጵያ የውኃ ሥራዎች ድርጅት መዋህዳቸውን ተከትሎ በ2008 ዓ.ም. ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)