ከፍተኛ ሙቀት በማሳየቷ ምክንያት በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ካሉ ለይቶ ማቆያዎች መካከል በአንዱ ባለፈው ሐሙስ ግንቦት 20፤ 2012 ገብታ የነበረች ወጣት የራሷን ሕይወት አጠፋች። ወጣቷ ራሷን ያጠፋችው ገና የምርመራ ናሙና ሳትሰጥ ሲሆን ህይወቷ ካለፈ በኋላ በተደረገ ምርመራ ከኮሮና ቫይረስ ነፃ መሆኗ ተረጋግጧል።
ከአዲስ አበባ ወደ አርባ ምንጭ በመጓዝ ላይ የነበረችው ሟች በአቅራቢያው ባለ ከተማ ላይ በተደረገ የሙቀት ልኬት ወቅት ከፍተኛ ሙቀት በማሳየቷ በአርባ ምንጭ ከተማ ካሉ የለይቶ ማቆያዎች መካከል አንዱ በሆነው የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እንድትቆይ መደረጉን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ለ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
አንድ በኮሮና ቫይረስ የተጠረጠረ ሰው ወደ ለይቶ ማቆያ ከገባ በኋላ ተከታታይ የሙቀት መጠን ተለክቶ መሻሻል ካለ ተጠርጣሪዎች ወደ ቤታቸው እንዲሄዱ ይደረጋል። ሙቀቱ ከቀጠለ እና ሌሎች የኮሮና ቫይረስ ምልክቶች ከታዩ ግን ናሙና ተወስዶ ወደ ሃዋሳ ላብራቶሪ ይላካል።
የ25 ዓመት ወጣት የሆነችው ሟች ወርቅነሽ ዲባባ ይህንን ደረጃ ሳታልፍ ወደ ለይቶ ማቆያው በገባች እለት “የራሷን ህይወት አጥፍታለች” ሲሉ የዩነቨርሲቲው ፕሬዘዳንት ገልጸዋል። ህይወቷ ካለፈ በኋላ አርብ ግንቦት 21፤ 2012 ናሙናዋ ተወስዶ ወደ ሃዋሳ የተላከ ሲሆን በማግስቱ የደረሰው የምርመራ ውጤትም ሟች ከቫይረሱ ነፃ እንደነበረች የሚያሳይ ነበር ሲሉ ፕሬዘዳንቱ አክለዋል። (በሐይማኖት አሸናፊ – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)