ህዝብን የወከሉ ሁለት ተቋማት “በህገ መንግስቱ ትርጉም ሂደት ላይ አልተደመጥንም” ሲሉ አቤቱታ አቀረቡ

በሐይማኖት አሸናፊ

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶችና የዴሞክራሲ እድገት ማዕከል እና ሴንተር ፎር አድቫንስመንት ኦፍ ራይትስ ኤንድ ዴሞክራሲ (ካርድ) የተሰኙት ሁለት የሲቪክ ተቋማት፤ የሕዝብ ጥቅምን በመወከል የምርጫ ጊዜ መዛወርን በሚመለከት በከሳሽነት ወይም በጣልቃ ገብነት ለመሟገት፤ ለሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ያቀረብነው አቤቱታ አልተደመጠም ሲሉ ቅሬታቸው አሰሙ።

ሁለቱ ተቋማት ግንቦት 13፣ 2012 ለጉባኤው በጣልቃ ገብነት ለመሟገት ማመልከቻ በማስገባት በጉዳዩ ለመሳተፍ መጠየቃቸውን ገልጸዋል። ይሁንና አጣሪ ጉባኤው በጉዳዩ ላይ ጭብጥ ይዞ ካለማከራከሩ ባሻገር የጉባኤው ጽህፈት ቤት “ማመልከቻውን ለመቀበሉ የደረሰኝ ቁጥር ወይም ሌላ ማረጋገጫ እንኳን ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም” ሲሉ ተቋማቱ አስታውቀዋል።

አጣሪ ጉባኤው የጣልቃ መግባት ጥያቄውን ወደ ጎን ብሎ ሳያከራክር ወይም እንደ አማራጭ የባለሙያ ምክር የመስጠት ጥያቄያቸውን ወደ ጎን ማለቱን የተቋማቱ ተወካዮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በላኩት መግለጫ ጠቅሰዋል። “ለአጣሪ ጉባኤው አስተያየት ለማቅረብ በህግ ሶስተኛ ዲግሪ መያዝ ወይም በአጣሪ ጉባኤው መመረጥ አይገባም። ይልቁንም የሕገ መንግስቱ ባለቤት የሆነው እና ያገባኛል ያለ አካል ሊደመጥ ይገባ ነበር” ብለዋል።

ሁለቱ ተቋማት ሕጋዊ ሰውነት እንዳላቸው ድርጅቶች “አማራጭ የማቅረብ እና የመደመጥ መብት አለን” በሚል አቤቱታውን ለአጣሪ ጉባኤው ማስገባታቸውን አስታውቀዋል። ጉባኤው ግን ይህንን ችላ በማለት ውሳኔውን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በመላኩ አቤቱታቸውን ለህዝብ ይፋ ለማድረግ መወሰናቸውን የካርድ ዋና ዳይሬክተር በፍቃዱ ሃይሉ “ለኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

“የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት ጥሪ በማቅረብ ክርክራችንን ያዳምጣል ብለን እንጠብቃለን” ብለዋል ዳይሬክተሩ። “ይህ የማይሆን ከሆነ ግን በሕጉ መሰረት ወደ ቀጣዩ አካል ይግባኝ እንላለን” ሲሉም አክለዋል።

ሁለቱ አቤት ባይ ተቋማት ከአቤቱታቸው ጋር 13 ገጽ ያለው እና ሰፊ ክርክርን የያዘ የህዝብ ጥቅም ተሟጋች (public interest litigant) እና የፍርድ ሰጪ አካል ደጋፊ ጽሁፍ (amicus curie) ለአጣሪ ጉባኤው አስገብተዋል። ከፍተኛ የትምህርት ዝግጅት ባላቸው ሶስት የህግ ባለሙያዎች እንደተዘጋጀ በተነገረለት በዚህ አቤቱታ የአጣሪ ጉባኤውን ተዓማኒነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ክርክር ተነስቷል። ጉባኤው “የነፃ እና የገለልተኛ ዳኝነት መርሆዎች ሊገዙት ይገባል” ሲልም አቤቱታው ሞግቷል።

የገዢው አሊያም የማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አባል የሆኑ እና ማንኛውም የጥቅም ግጭት ያለባቸው የጉባኤው አባላት በገዛ ፈቃዳቸው ወይም በአጣሪ ጉባኤው ትዕዛዝ በዚህ ጉዳይ ላይ ውሳኔ ከመስጠት እንዲታቀቡ የሚል የብይን ጥያቄም አቅርበዋል። የተወሰኑት የጉባኤው አባላት ከዚህ በፊት የነበሩ እንደ ጸረ ሽብር አዋጅ ያሉ አፋኝ ህጎችን በመደገፍ ታዋቂነት ያካበቱ ጠበቆች ከመሆናቸው አንጻር ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወሰድ ሲሉም አመልካቾቹ ጠይቀዋል። የፖለቲካ ፓርቲ አባል የሆኑ የጉባኤው አባላት በዚህ ጉዳይ ላይ መሰየማቸው እንዲቀጥል ካስፈለገም ከፓርቲያቸው እንዲለቅቁም ባለሙያዎቹ ለአጣሪ ጉባኤው ባስገቡት አቤቱታ ጠይቀው ነበር።

አመልካቾቹ የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ የባለሙያ እና የምስክርነት ቃል በተቀበለበት ሂደት “የፍርድ ስልጣንን የተመለከተውን ክርክር ችላ ብሏል። በቂ ክርክር አልተደረገበትም። ይህም ስህተት ነው” ሲሉ ወቅሰዋል። ለዚህም አብዛኞቹ ግብዓት የሰጡ ባለሙያዎች ቦርዱ ይህንን ጉዳይ የመመልከት ስልጣን የለውም የሚል አስተያያት መስጠታቸውን አጽንኦት ሰጥተውበታል። 

አጣሪ ጉባኤው ከተወካዮች ምክር ቤት የተጠየቀውን ጉዳይ የማስተናገድ ስልጣን የለውም ካሉ ባለሙያዎች ውስጥ ዶ/ር ሙሉጌታ አረጋዊ፣ ዶ/ር ሙሉጌታ መንግስት፣ ዶ/ር ወንድወሰን ደምሴ፣ ሙሉ በየነ፣ ምሕረተአብ ገብረ መስቀል፣ ኣብራሃ መሰለ፣ ገብረሂወት ሓዱሽ፣ ገብረመስቀል ሃይሉ እና ገብረአበዝጊ ወልደ ስላሴ እንደሚገኙበት ዘርዝረዋል። 

የቃል ምስክርነት እንዲሰጡ የተጠየቁት ዶ/ር ሰለሞን አየለ፣ ዶ/ር ዮናታን ተስፋዬ፣ ዶ/ር አደም ካሴ እና ዶ/ር ዘመላክ አይተነውም የተለያዩ አዋጆችን በማጣቀስ “አጣሪ ጉባኤው ይህንን ጉዳይ ከተወካዮች ምክር ቤት በቀጥታ ተቀብሎ መመልከት የሚያስችለው ሕግ የለም” ማለታቸውን አቤት ባዮች አስረድተዋል። ምሁራኑ በህጉ መሰረት ጉዳዩ ከተወካዮች ምክር ቤት ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ተመርቶ፤ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ወደ አጣሪ ጉባኤው ቢመራው ብቻ “አግባብ ይሆን ነበር” የሚል አስተያየት መስጠታቸውን አቤቱታው ያጣቅሳል። 

አቤቱታውን ያዘጋጁት ባለሙያዎች “አጣሪ ጉባኤው በስልጣኑ ላይ በምሁሮቹ የተነሱትን ተቃውሞዎች ትኩረትና አጽንኦት ሰጥቶ ማየት እንደሚገባው እንዲሁም የፍርድ ስልጣን ጉዳይ በዝርዝር ሳይመረምር መታለፍ እንደሌለበት እናሳስባለን” ሲሉ ለአጣሪ ጉባኤው አመልክተው ነበር። “ለጉባኤው በትርጉም ጥያቄነት የቀረበው የምክረ ሃሳብ ጥያቄ፤ በሕገ መንግሥቱ የፖለቲካ ጥያቄ ንድፈ ሐሳብ (political question doctrine) መሠረት ፤ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤም ሆነ ፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ሊያዩት የሚችሉት ፍሬ ሀሳብ አይደለም” ሲሉም አክለዋል። 

ለሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤው የቀረበው ፍሬ ጉዳይ በፍርድ ሊወሰን የሚገባው ወይም የሚችል ጉዳይ (justiciable matter) አለመሆኑን የሚጠቅሱት ባለሙያዎቹ አጣሪ ጉባኤው በፖለቲካ ጥያቄ ንድፈ ሐሳብ (political question doctrine) መሸፈን አለመሸፈኑን ሳይወስን እንዳያልፍ ሲሉ የውሳኔ ጥያቄ አቅርበዋል። ጥያቄው በፍርድ ወይም በፖለቲካዊም ወይም በማንኛውም አመክንዮ ቢታይ፤ ጉዳዩ የአገረ መንግሥቱ አንድነትን እና የሕዝቦችን ስምምነት በሚያበረታታ መንገድ እንዲወሰንም ሁለቱ ተቋማት ጠይቀዋል።

አቤቱታውን ያዘጋጁት ባለሙያዎች አጣሪ ጉባኤው ራሱን በፖለቲካ ጥያቄዎች ውስጥ አስገብቶ የፖለቲካ አንድምታ ያላቸው ቴክኒካዊ ትርጉም ውስጥ ለመግባት ከወሰነ መመልከት ይገባዋል ያሏቸውን ነጥቦች አስቀምጠዋል። “ከዚህ ቀደም የተደረጉ ምርጫዎች ኢ-ዴሞክራሲያዊ ናቸው” ያሉት አመልካቾቹ በተለይም የመጨረሻዎቹ ሁለት ምርጫዎች “ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰትንም ጭምር አስከትለዋል” ብለዋል።

“የአሁኒቷ ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት፣ አስርት ዓመታት ከፍተኛ መጠን ያለው የመፍረስ ወይም የመፈርከስ ስጋት ገጥሟታል” ሲል አቤቱታው ያስረዳል። የአቤቱታው አዘጋጆች ይህ ሁኔታ “የተወሰነ መሻሻል ቢያሳይም መሠረታዊ የሚባል የመረጋጋት ሽግግር ግን ገና አልተደረገም” የሚል እምነት እንዳላቸውም አስታወቀዋል።

“በተለይም በትላልቅ ከተሞች የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን፤ በቅርብ ጊዜያት የታዩት ሕዝባዊ አመፆች እስኪመጡ ድረስ፤ የአገረ መንግሥቱ የመፈርከስ ስጋት ውጤቶች ሳይነኳቸው ተጠብቀው ቆይተዋል። አንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች በመፈረካከስ ሂደት ውስጥ አልፈዋል ወይም የመንግሥት መፈረካከስ፣ ማስተዳደር አለመቻል፣ ሽምቅ ውጊያ ወይም እንደ የጦርነት ወንጀሎች እና በስብዕና ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ያሉ ከፍተኛ የወንጀል ተግባራትን ተሸክመዋል” ሲሉም በአቤቱታው አብራርተዋል። 

የግጭቶቹ መነሾም ጊዜያዊ ምክንያት ቢኖራቸውም ስረ መሰረታዊ ምክንያቶቻቸው ግን “የሕገ መንግሥታዊ ቀውስ፣ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና የዲሞክራሲ እጦት መደራረብ ነው” ሲሉም አስረድተዋል። “የመንግስት አምባገነናዊ አውቅላችኋለሁ ባይነትና ከእኔ ውጭ ሌላ አማራጭ አይኑር ባይነት” ተጨማሪ ምክንያቶች መሆናቸውንም ባለሙያዎቹ በአቤቱታቸው አንስተዋል። 

የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤው የሚያሳልፈው ውሳኔ “እነዚህን የአገረ መንግሥት መፍረስ ስጋት የሚሆኑ ምክንያቶችን እንዳይባባሱ የሚያደርጉ ቅድመ ሁኔታዎችን ባካተተ መልኩ ሊሆን ይገባል” ሲሉ ሙግታቸውን አቅርበዋል። የምርጫ ማራዘምን ጉዳይ ለመፍታት የተያያዘው መንገድም ከተቃዋሚዎች ጋር የሚደረግ የምክክር ሂደት ወይም መዋቅር ካልታከለበት የአገረ መንግስቱን መፍረስ እንዳያባብስ ስጋት እንዳላቸውም ገልጸዋል።

“መንግስት በአሁኑ ወቅት እየመራ ባለው የሽግግር ወቅት ከፍተኛ የሚባሉ የፓርቲ እና ሀገራዊ መሻሻሎች ማድረጉ አይካድም” ያሉት ተቋማቱ “የሽግግር ጊዜ ፍትህ አመራርን ጨምሮ ከፍተኛ ክፍተቶችም ያሉበት ነው” ሲሉ ነቅሰዋል። የሽግግር ጊዜ የድርድር ሂደቶችም “በአግባቡ አለመካሄዳቸው” ሌላው ድክመት መሆኑንም ጠቅሰዋል።  መንግስት እንደ ጸረ ሽብር ህግ ያሉ ህጎችን ቢያሻሽልም እንደ የጥላቻ ንግግር ህግን መሰል አዳዲስ ህጎችን በመውጣት ተቺዎቹን ለማሰር መጠቀሙም እንደ ድክመት ተነስቷል።

የሕገ መንግስት አጣሪ ጉባኤው ጉዳዩ ፖለቲካዊ ጥያቄ መሆኑን ችላ ብሎ ወደ ውሳኔ መስጠት የሚሄድ ከሆነ፤ ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት “ምርጫው በሚራዘምበት ጊዜ የምክክር ሂደት ወይም መዋቅር እንዲዘረጋ የሚያስገድድ ወይም የሚያበረታታ ውሳኔ ሊወስን ይገባል” ብለዋል አቤት ባይ ተቋማቱ። መንግሥት የሚወስደው ምርጫን የማራዘም እርምጃ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን፣ የሰራተኞች ማህበራትንና ሌሎች የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን፣ እንዲሁም የማህበረሰቡን አካላት ያካተተ የምክክር አካሄድ መከተል እንዳለበት የሚያስገድድ ውሳኔ ይሰጥልን ሲሉም አክለዋል። 

ለአጣሪ ጉባኤው ከተወካዮች ምክር ቤት የተላከው ጥያቄ፤ “መንግስት የሚፈልገውን ድምዳሜ ያዘሉ እና ክፍትና ቢሆናዊ (hypothetical) ናቸው” ያሉት ተቋማቱ በዚህም ሳቢያ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም ሆነ ማናቸውንም መብት ሊገድቡና ሊጥሱ የሚችሉ እርምጃዎችን መውሰድ አለመውሰዱን በሚመለከት በየወሩ ለአጣሪ ጉባኤው ሪፖርት እንዲያቀርብ እንዲታዘዝ አሳስበዋል። ከዚህ በተጨማሪም የኮሮና ቫይረስ ለረጅም ጊዜ ሊቆይ ስለሚችል፤ መንግስት ወይም የምርጫ ቦርድ በሽታው የሚሰራጭበትን እድል ሳያባብስ፤ ምርጫ የሚካሄድበትን ሁኔታና አቅም ለመገንባት ምን እቅድ እንዳለው ለአጣሪ ጉባኤው ሪፖርት እንዲያቀርብ ትዕዛዝ እንዲተላለፍ ሲሉም ጠይቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)