የኳራንቲን ቆይታ በጋዜጠኛዋ አንደበት 

በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከቀን ወደ ቀን በከፍተኛ ሁኔታ እያሻቀበ ነው። በዚያኑ ልክ በኮሮና ቫይረስ ተጠርጥረው ወደ ለይቶ ማቆያ የሚወሰዱ ግለሰቦች ቁጥርም እየጨመረ መጥቷል። እንዲህ አይነት ግለሰቦች የምርመራቸው ውጤት እስኪታወቅ ድረስ እንዲቆዩ በሚደረግበት ቦታ ቀናትን ያሳለፈችው ሐይማኖት አሸናፊ የኳራንቲን ቆይታ በቂ የስነልቦና ዝግጅት ሳይደረግ ከተገባበት “መዘዙ ብዙ ነው” ትላለች።

ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ገደማ። ከአንድ ወዳጄ ጋር በሞባይል የፅሁፍ መልዕክት እየተለዋወጥን ነው። የጤና ሚኒስቴር የሚያወጣውን ዕለታዊ የኮሮና ቫይረስ ሪፖርት አንስተን መወያየት ይዘናል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በዚያን ዕለት፤ ሚያዚያ 28፤ 2012፤ ይፋ ያደረገው ሪፖርት ላይ ያልተለመደ የቁጥር ማሻቀብ መታየቱ እያነጋገርን ነው። ቫይረሱ በምርመራ እንደተገኘባቸው የተረጋገጠ አብዛኞቹ ግለሰቦች ከጎረቤት አገር የተመለሱ ኢትዮጵያውያን መሆናቸው ለእኔ የተለየ መልዕክት ነበረው። 

ከስራ ጸባዬ ጋር በተያይዘ የኮሮና ቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ ከገባበት ከመጋቢት 4 ጀምሮ የቫይረሱን ስርጭት የሚመለከቱ ሪፖርቶችን በአግባቡ ብከታተልም እንደ ሚያዚያ 28ቱ ሪፖርት ግን ይበልጥ ጠልቆ የተሰማኝ አልነበረም። ሪፖርቱ ከመውጣቱ ከ15 ቀናት በፊት ድንበር አቋርጠው ወደ ኢትዮጵያ የሚመለሱ ስደተኞችን ሁኔታ ለመመልከት ኢትዮጵያን ከጂቡቲ ጋር ወደሚያዋስናት ስፍራ ተጉዤ ነበር። በወቅቱ በሐኪሞች የሚመከሩ ጥንቃቄዎችን በሙሉ ባደርግም የሪፖርቱ ይዘት ግን ብዙ ምን አልባቶችን ወደ ህሊናዬ አመላልሷል። 

በዚህ ሀሳብ ውስጥ ሆኜ እንደ እኔ በሪፖርቱ ይዘት ሃሳብ የገባው ወዳጄም  “ምን አልባት መመርመር ይኖርብሽ ይሆን?” ሲል የመፍትሔ ሀሳብ ያለውን ጠቆም አደረገኝ። ውሳኔ ላይ ከመድረሴ በፊት የራሴን ሁኔታ ፈተሽኩ። የኮሮና ቫይረስ ዋና ዋና ምልክቶች የሚባሉት ሳል፣ ትኩሳት እና የመሳሰሉት በሙሉ አይታዩብኝም። በእርግጥ በሙቀት አካባቢዎች ረጃጅም እና አድካሚ ጉዞዎችን ሳደርግ ከርሜ ወደ አዲስ አበባ ስመለስ የተቀበሉኝ ዝናባማ ቀናት ለጉንፋን ዳርገውኛል። 

ጉንፋኑ እና ጥልቅ ድካም ተደራርበው የፈጠረብኝ የህመም ስሜት እየቀነሰ ሄዶ ወደ መጥፋቱ ቢቃረብም የሪፖርቱ ነገር ግን ስጋቴን ድጋሚ ቀስቅሶታል። ህመም ሲሰማኝ “የሚመጣው አይታወቅም” በሚል እሳቤ፤ ራሴን ሙሉ ለሙሉ በሚባል ሁኔታ በቤቴ ውስጥ ባገልልም፤ ተመርምሬ ቁርጤን የማወቅ ፍላጎቴ ሲንር እየተሰማኝ ነው። ምርመራ እንደሚያስፈልገኝ ውሳኔ ላይ ከደረስኩ በኋላ ወደ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የጥሪ ማዕከል መደወል ጀመርኩ። 

ኢንስቲትዩቱ ለዚሁ ዓላማ ያዘጋጃቸውን ሁለት አጭር የስልክ ቁጥሮችን በቃሌ አላውቃቸውም፤ ወይም በስልኬ መዝግቤ አልያዝኳቸውም፡፡ ለግሌ ጉዳይ ያስፈልገኛል ብዬ ባለመገመቴ፡፡ ይህም ብዙዎቻችን ነገሩን ከራሳችን አርቀን እንደምንመለከተው ማሳያ ነው፡፡

ብቻ ቁጥሮቹን ፈልጌ ካገኘኋቸው በኋላ ደጋግሜ ብደውልም ከዚያኛው ወገን የሚመጣው “የተይዟል” ድምጽ ብቻ ሆነ። ተስፋ ሳልቆርጥ ደጋግሜ ሞከርኩ። በግምት ቢያንስ ለአንድ ሰአት ገደማ ከቆየ ሙከራዬ በኋላ ስልኩ ጠራ። አንድ በጣም የተረጋጋች ሴት ስልኩን አነሳች። የምነግራትን ሁሉ በጥሞና ማዳመጥ ጀመረች። ከዚህ ቀደም በሚተዋወቅ ሰው ድምፅ ቀለል ያሉ ጥያቄዎችን ስትጠይቅ፤ ምላሽ ስሰጥ ቆየሁ።  

የስልክ ልውውጡ ቀጣዩን እርምጃ ያለፍርሃት ለመቀጠል ድፍረትን የሚሰጥ እንጂ የሚያስፈራ አልነበረም። ከተጠየቅኋቸው ጥያቄዎች ውስጥ በአብዛኛው የሚሰሙኝን ስሜቶች፣ ለምን ራሴን እንደጠረጠርኩ እና የተወሰኑ የግል መረጃዎች ይገኙበታል። በእርጋታ የተሞላችው ሴት መረጃውን ለአዲስ አበባ ጤና ቢሮ እንደምታስተላልፍ እና ቢበዛ በአንድ ሰአት ውስጥ እንደሚደውሉልኝ ገልፃልኝ ተሰናባበትን። 

ድራማ መሳዩ መረጃ አሰባሰብ 

በርግጥም ከአንድ ሰዓት በኋላ ስልኬ ጠራ፤ ከአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ነበር። አድራሻዬን ጠይቁኝ፤ ነገርኳቸው። ከምሽቱ አራት ሰዓት ሲል የጤና ባለሙያዎቹ የምኖርበት ግቢ በር ላይ መድረሳቸውን ገልፀው ደወሉልኝ። “ወደ ግቢ ከገባን ላንቺ ጥሩ አይሆንም፤ ያው ለማህበራዊ ህይወትሽ። ስለዚህ የምትችዪ ከሆነ በር ላይ ወጥተሽ አናግሪን” አለኝ በስልክ የማነጋግረው ባለሙያ። የጤና ባለሙያው አባባል ነገርየው ጎረቤቶቼ ላይ ሊፈጥር ስለሚችለው ሽብር እና ድንጋጤ ያስተዋልኩበት የመጀመሪያው ቅፅበት ነበር። ቢሆንም ግን የነገርየውን ክብደት በአግባቡ አለመረዳቴ የገባኝ በኋላ ላይ ነው።

የባለሙያዎቹን ጥቆማ ተከትዬ ከግቢው መግቢያ ስደርስ አንድ አምቡላንስ እና የአደጋ መብራቱን የሚያበራ፣ ባለ ሁለት ጋቢና፣ ነጭ ፒክ አፕ መኪና በሩ ላይ መቆማቸውን ተመለከትኩ። አራት ወይም አምስት የሚሆኑ ወጣት ወንዶች አፍና አፍንጫቸውን እንዲሁም እጆቻቸውን ሸፍነው በተጠንቀቅ ቆመዋል። መደንገጥ ጀመርኩ። ነጭ ጋዋን የለበሰው ባለሙያ ማንነቴን አረግጋጦ ያጠለቅኩት የአፍ መሸፈኛ ላይ የምደርበው ሌላ ሰርጂካል የአፍ መሸፈኛ ሰጠኝ፤ ደረብኩት። ቢያንስ ሶስት ሜትር ርቄ እንድቆም ነግሮኝ በጥያቄ ያጣድፈኝ ጀመር።

ምንም እንኳን ቢመሽም አላፊ አግዳሚው “ወሬ” ለማየት መጠጋት ጀመረ። ከግቢው አጠገብ በተደረደሩ ሱቆች ያሉ ሻጮች በመስኮታቸው አሻግረው ወደ ቆምንበት ጨለማ ውስጥ ያንጋጥጣሉ። ወደ ግቢ ውስጥ የሚገቡት ባለመኪኖች ተሽከርካሪዎቻቸውን ባሉበት አቁመው እና ረጅም መብራቶቻቸውን አብርተው ሁኔታውን በጥሞና ይከታተላሉ። የጤና ባለሙያዎቹም የእኔን ታሪክ ከመቀበል ባሻገር እነዚህን ሰዎች እንዲሄዱ ማዘዙ ያደከማቸው ይመስላል። ይሄኔ ነው “ፈንጂ የተጠመደበት አሸባሪ” መስዬ እንደምታያቸው የተሰማኝ። 

የሚሆነው ሁሉ ድራማ ይመስላል። የአንዳንዱ ሁኔታ ሳቅ ያጭራል። ፊቴ በተደራቢ የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎች መከለሉ በጀኝ፤ ሳቄ ሲመጣ ሳልሳቀቅ እስቃለሁ። በዚህ መሃል “ኮሮና እንደሌለብኝ ሲያውቁ ይረጋጋሉ” እያልኩ ከራሴ ጋር አወራለሁ። እዚያው የግቢ መግቢያ ላይ እንደቆምኩ የጤና ባለሙያዎቹ የጠየቁኝን ሁሉ መለስኩ። አንዱ በወረቀት፤ ሌላኛው ደግሞ በስልኩ ምላሾቼን መዝግበው ጨረሱ። በተደረገለኝ የሰውነት ሙቀት ልኬት “መደበኛ” የሙቀት መጠን እንዳለኝ መረዳታቸውንም ነግረውኛል። 

“የነገርሽን ምልክቶች የሚያሰጉ አይደሉም። ነገር ግን በጤና ጥበቃ ፕሮቶኮል መሰረት ኳራንቲን ያለበት ቦታ ደርሰሽ መምጣትሽ ተጠርጣሪ ለመሆን እና ምርመራ ለማድረግ ብቁ ያደርግሻል። ስለዚህ አብረሽን ሄደሽ፣ ናሙና ሰጥተሽ፣ ውጤት ተቀብለሽ ትመጫለሽ” ሲል ባለ ነጭ ጋዋኑ የጤና ባለሙያ ተናገረ። ልብሶቼን እና ግፋ ቢል ለ24 ሰዓት የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች ይዤ እንድመጣም ጠቆመኝ። በቤቴ እንዳለሁ ናሙና ተወስዶ፤ እዚሁ እቆያለሁ ብዬ እንጂ ወደ አስገዳጅ ለይቶ ማቆያ እንደምወሰድ ባለመገመቴ ፍርሃት ፍርሃት ይለኝ ይዟል። 

“የምኖረው ብቻዬን ነው፤ ቤቴ መቆየት አልችልም” ስል ፈራ ተባ እያልኩ ተማጸንኩ። ለጊዜው በቤት ውስጥ ክትትል እንዳልተጀመረ ተነግሮኝ መሄዴ ቁርጥ ሆነ።

አሁንም ግን አልከፋኝም። “ምን ችግር አለው?” ስል ራሴን ጠየቅኩ። “አንድ ለሊት ነው የማድረው ብለው የለ” ለራሴው መለስኩ።

ጉዞ ወደ የማይታወቀው ቦታ

ከአምስት ደቂቃ በላይ ሳልወስድ በማውቀው ልክ የጀርባ ቦርሳዬን ሞልቻት ወጣሁ። የአምቡላንሱ የኋላ በር ተከፈተልኝ። በህይወቴ ታምሜ በአምቡላንስ ተወስጄ አላውቅም፤ ዛሬ ግን ግዴታ ነውና ገባሁ። አሁን ነገሩ ሁሉ ያሳስበኝ ጀምሯል – “ከእኔ በፊት ማን ይሆን እዚህ አምቡላንስ ውስጥ የገባው?”። መጠንቀቅ ያዝኩ፤ የእጅ ጓንቱ በደንብ መጥለቁን አረጋገጥኩ። ወዴት እንደምንሄድ አላውቅም። ሹፌሩ “ጥያቄ ካለሽ አጨብጭቢ፤ መጮህ ግን አይቻልም” ብሎ ቀልዶብኝ መንዳቱን ይዞታል። “ይሄ ማለት ‘ወደ የት ነው የምንሄደው? ብዬ ብጠይቀው አይሰማውም ማለት ነው” አልኩ ለራሴ። 

ከምሽቱ 5 ሰዓት ገደማ ሲሆን አንድ የውስጥ ለውስጥ የኮሮኮንች መንገድ እንደጨረስን፤ አንድ ባለ አምስት ወለል ፎቅ የያዘ ቅጽር ግቢ ደረስን። አምቡላንሱ መግቢያው በር ላይ ቆመ። አፍታም ሳይቆይ የአምቡላንሱ በር ተከፍቶ ቦርሳዬን ይዤ እንድወርድ ተነገረኝ። አላቅማማሁም፤ ወረድኩ። አእምሮዬ ውስጥ ጥያቄ እና ፍርሃት እንጂ አንድም መልስ የለም። በሶስት ሰዓታት ውስጥ ከሞቀ ቤቴ ወጥቼ፣ በማላውቀው ሁኔታ ውስጥ በድንገት መገኘቴ፣ እንዲህ ነው ማለት ያስቸገረኝ ስሜት እና ውዝግብ ውስጥ ከትቶኛል። 

ወደ ህንጻው የሚያስገባው ደረጃ ስር አንድ ሮዝ ወንበር እየጠቆሙኝ “ቁጭ በይ” ተባልኩ። እንደ ድንበር ከተበጀው ነጭ ጣውላ ባሻገር ሐኪሞች መሰባሰብ ጀምረዋል። ሐኪሞቹ ወረቀት እና እስኪቢርቶአቸውን ይዘው ቅድም የመለስኳቸውን ጥያቄዎች ደግመው ይጠይቁኛል፤ አሁንም ሳልታክት እመልሳለሁ። የዚህኛውን ዙር የሚለየው ግን እኔም ጥያቄ መጠየቅ መጀመሬ ነው – “አሁን አትመረምሩኝም? ስንት ቀን እቆያለሁ?”። 

ሐኪሞቹ ትክክለኛውን መልስ ሰጡኝ። ከአራት እስከ አምስት ቀን እንደምቆይ እና የእለቱ ናሙና ተወስዶ በመጠናቀቁ በማግስቱ ናሙና እንደሚወሰድ ነገሩኝ። ድንጋጤዬ ከፍ ሲል ተሰማኝ። ‘ይሄኔ መሆን አለበት ሰዎች ሮጠው የሚያመልጡት’ ብዬ አሰብኩ። ነገሩ ሁሉ ድንገቴ ነው፤ ማንም ስለ ስነ ልቦና ዝግጅት አያስብም። ‘ይህን ያህል ቀን እንደምቆይ አስቀድመው ቢነግሩኝ አንድም አእምሮዬን አዘጋጃለሁ፤ ብሎም ተጨማሪ ቁሳቁሶችን እይዝ ነበር’ ስል ለራሴ ተነጫነጭኩ።

ከነርሶቹ መካከል አንዷ ወደ አንደኛ ፎቅ እንድወጣ ነግራኝ ከእኔ በተቃራኒ ባለው ደረጃ ወጣች። ከአንደኛው የህንጻው ጥግ ቆማ፤ ክፍሌን ከሩቅ ጠቁማኝ ሄደች። ምሽቱን የምቆይበትን ክፍል ሳስብ ወደ አእምሮዬ ሲመላለስ የቆየው “ብዙ ሰዎች ያሉበት ትልቅ አዳራሽ፣ መሬት ላይ የተነጠፈች ትንሽ ፍራሽ እና ንጽህናው እምብዛም የማይጠበቅ ቦታን” ነበር። የተጠቆምኩትን ክፍል በር ገፋ አድርጌ ስገባ ያገኘሁት ግን እንደዚያ አይደለም። አነስ ያለች፣ በጣም ንፁህ፣ ተኝቶ የመታከሚያ ክፍል፤ በአግባቡ ከተነጠፈ አልጋ ጋር ከፊቴ ተደቀነ። 

በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ወደማላውቀው አካባቢ፣ ሁኔታ እና ፍርሃት ውስጥ ገብቻለሁ። በዚህ መሃል ከሁለት ሰዎች ጋር በስልክ አወራለሁ። ከማፅናናት ባሻገር ቀልዶች እያወራን በሁኔታው እንስቃለን፤ ይሄ የተወሰነ አረጋጋኝ። በዚህ አጭርም ይሁን ረጅም ጉዞ “ሰው ወሳኝ ነው”፤ የመጀመሪያውን ትምህርቴን ወሰድኩ። 

ዞሮ ዞሮ ወደ አዲሷ ቤቴ ገባሁ።

ቀን አንድ – ሐሙስ

በአዲሷ ቤቴ ‘ጭራሽ እንቅልፍ አይወስደኝም’ ብዬ ባስብም ጠዋት ስነቃ ነው ጭልጥ ያለ እንቅልፍ ወስዶኝ እንደነበረ የተረዳሁት። የመኝታ ክፍሌ ያለመቆለፏ፤ መስኮቷ መጋረጃ የሌለው መሆኑ፣ አንድ ሙሉ ግቢ ፍንትው አድርጎ የሚያበራው እና በትንሿ ክፍል መሀከል ላይ የተሰቀለው የፓውዛ መብራት እንቅልፍ በአይኔ እንኳ እንደማይዞር አስረግጠውልኝ ነበር። ከእንቅልፌ የቀሰቀሰኝ ምግብ የሚያከፋፍል፤ አረንጓዴ ዘንቢል የያዘ ሰው ነበር። ሰውየው አይኑ፣ አፍንጫው፣ ባጠቃላይ ሁለመናው ተሸፍኗል። 

በሩ በኃይል ሲንኳኳ በጣም ያስደነግጣል። ቀድሞ ገርበብ ያለውን በር ልከፍትለት ስሄድ “እዛው ቁሚ” አለኝ በትዕዛዝ ድምጽ፤ ባለሁበት ደረቅሁ። “የአፍ መሸፈኛሽን አድርጊ። ከዚህ በኋላ እኔ ሳንኳኳ በር ከመክፈትሽ በፊት መስኮት ክፈቺ” ሲል አስጠነቀቀኝ። አነጋገሩ ቢያስደነግጥም ያለኝን አድርጌ “ከአልጫ ክክ አያልፍም” ያልኩትን ምግብ ተቀበልኩ። ምግቡን ከፍቼ ስመለከት፤ ዱለት እና ጥብስ። በመገረም ምግቡ የመጣበትን ጥቁር ላስቲክ መልሼ ከድኜ ዙሪያዬን ማጤን ጀመርሁ።

ያለሁት በአዲስ አበባ በስተምስራቅ አቅጣጫ በተገነባ ጤና ጣቢያ ውስጥ ነው። ነገሩ ጤና ጣቢያ አሉት እንጂ የህንፃው ግዝፈት ከአብዛኛው የግል ሆስፒታሎች ይስተካከላል።  ይህ ጤና ጣቢያ በአዲስ አበባ ከተማ ከኮሮና ቫይረስ ጋር ለሚደረገው ፍልሚያ ከተዘጋጁ የለይቶ ማቆያ ቦታዎች መካከል አንዱ ነው። አንደኛ ፎቅ ላይ ከምትገኘው፤ አራት ሜትር በሁለት ሜትር ከምትሆነው ክፍሌ በስተጀርባ በተዘረጋው መስኮት የሚስተዋለው “መደበኛ” ህይወት ግን ፍልሚያው ከነመኖሩ ጭምር የሚያስረሳ ነው። 

ባለ አምስት ወለሉን የጤና ጣቢያ ተደግፈው የተሰሩት አነስ አነስ ያሉ ቤቶችም ከጎናቸው ምን እንደሚከናወን የሚያውቁ አይመስሉም። ከጤና ጣቢያው በቀጥታ የሚዋሰኑት ትንንሽ ቤቶች አናት ላይ የተተከሉት የሳተላይት ቴሌቪዥን መቀበያ ሰሃኖች፤ በባህር ዛፎች መሃል የተሰገሰጉትን ቤቶች በቀላሉ ለመለየት ያግዛሉ። በደንብ ላንጋጠጠ ሰው ከዛፎቹ እልፍ ብሎ ያለው አነስተኛ ሜዳ ላይ የሰፈሩ ልጆች ኳስ ሲያንከባልሉ ያያል። ከርቀት ዕይታ ውስጥ የሚገባው ድንቅ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሌላው የአካባቢው የ“መደበኛ ህይወት” ተምሳሌት ነው።

ሺህዎችን መ’መገብ 

በምዕራቡ አለም የየሀገሬው ዜጎች ዋነኛዎቹን የኮሮና ቫይረስ ምልክቶችን እያሳዩ እንኳን ከጤና ተቋማት መጨናነቅ አንፃር በለይቶ ማቆያ ተቋማት የመቆየት እድል እንደሌላቸው በመገናኛ ብዙሃን ተመልክተናል። እንደ ደቡብ አፍሪካ ባሉ አገራት በከፍተኛ ክፍያ ራሱ የሚደረጉ ምርመራዎችን ለማግኘት ሰዎች ተሰልፈው መጠበቅ ግድ ብሏቸዋል። 

እንደ ኢትዮጵያ ባለች በማደግ ላይ ባለች አገር ለኮሮና ቫይረስ ተርጣሪዎች ህክምና እና ምግብን ጨምሮ ሌሎች አገልግሎቶችን በነፃ ማቅረብ መቻል ግርምት ጭሮብኛል። ራሳችንን በመጠበቅ የጤና ተቋማት እንዳይጨናነቁ ማገዝ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ቀደም ብዬም እገነዘባለሁ። ግን አሁን በተጨባጭ ከማየው አንጻር እንዴት ለሌላው ሰው ማስረዳት እችላለሁ ብዬ አስባለሁ።

ወዲህ መለስ ብዬ ደግሞ “መንግስት ይሄንን ሁሉ ሺህ ሰው በየቀኑ ለመመገብ ምን ያህል ገንዘብ እያወጣ ይሆን?” ስል እጠይቃለሁ። ‘ለክፉ ጊዜ የሚሆን የአገራችንን አቅም ከወዲሁ እየጨርስን ይሆን?’ የሚለው ሀሳብም ሽው ብሎብኛል። ሃሳብ ባይኖር ቀኑ እንዴት ይገፋል? የቀረበልኝን ውሃ ከራሴ ጋር እየታገልኩ ፉት ብዬ ቡና ከውጪ ማዘዝ ይቻል እንደው ለመጠየቅ ከክፍሌ ወጣሁ። ደረጃውን ስወርድ አንድ ፖሊስ አገኘሁ። ሲቪል በመልበሱ ፖሊስ መሆኑን ያወቅሁት ቆየት ብዬ ነው። እንደሚያመልጥ ሰው በጥያቄ አጣደፈኝ።

“ወዴት ነው? ተመለሽ! አይቻልም አልኩሽ ተመለሽ” ገና ጥያቄዬን ሳይሰማ ነው ይህን ያለው። እንደምንም ከቁጣው መሃል ፋታ ፈልጌ “እባክህን ሃኪሞቹን ጥራልኝ” ብዬ ተመልሼ ደረጃውን መውጣት ልጀምር ስንደረደር፤ አንድ ንግግራችንን የሰማች ሐኪም ከህንፃው ፊት ካሉት አነስተኛ ቢሮዎች ወጥታ ወደ እኔ መጣች። 

ቀኑ አጋማሽ ላይ ደርሷል። “ምግብ እና ቡና ፈልጌ ነበር” አልኳት። “ምነው ምግቡ አልተመቸሽም?” አለችኝ።

“አዎ፤ ስጋ አልወድም” ሌላ ምክንያት አላገኘሁም፤ ስለዚህ ዋሸሁ። 

ሃኪሟ ብታዝንልኝም በሆዷ ‘እንዴት ልትከርመው ነው’ ማለቷ አይቀርም። ምክንያቱም ከአርብ እና ረቡዕ ውጪ ሳምንቱን ሙሉ የሚቀርበው ምግብ ስጋ ነክ ነው። ከቤተሰብ ምግብ ማስገባት እንደማይቻል፤ ይህም እቃው ተነካክቶ ሲመለስ ችግር እንዳይፈጠር በማሰብ መሆኑን በእርጋታ እና በሃዘኔታ ነገረችኝ። ከቤተሰብ ለማስመጣት ሳይሆን ከምግብ ቤት ለማዘዝ ማሰቤን ነግሬያት ተስማምተን ፈቀደችልኝ። ቡና መገኘቱም አይደል፤ ሃሳቡ ራሱ አስደሰተኝ። ‘አሁን ቀሪ ቀናቱን መቋቋም ይቻላል’ ስል ራሴን አበረታታሁ።

እንዲህ ያለው የችግር ጊዜ፤ የቴክኖሎጂ እና የኢንተርኔት ላይ ንግድ እና አገልግሎት ጥቅምን በሚገባ የተረዳሁበት ሆነ። ምግቡንም ሆነ ቡናውን በኦንላይን አዝዤ ያለሁበት ድረስ በአድራሻዬ መጣ። ከቡና በኋላ ዙሪያዬን በሚገባ ማጤን እና በማስታወሻዬ ላይ መመዝገብ ጀመርኩ። ቀድሜ ቀጠሮ የያዝኩበትን ቃለ ምልልስም በኢንተርኔት ማድረግ ችያለሁ። ረዘም ላሉ ቀናት እንደምቆይ ባለማወቄ ምክንያት፤ የላፕቶፕ ቻርጀር ባለመያዜ እንጂ የተለመደውን የስራ ሂደትም መቀጠል ይቻል ነበር።

መቆያው ጤና ጣቢያ 

በጤና ጣቢያው የተለያየ አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ የህክምና ክፍሎች ወደ መኝታ ክፍልነት ተቀይረዋል። “ማዋለጃ”፣ “ድንገተኛ” የሚሉ ጽሁፎች በበሮቻቸው ላይ የተለጠፉባቸው ክፍሎች ጭምር እንደኔው ከሰው ተለይተው እንዲቀመጡ የተደረጉ ግለሰቦች ገብተውበታል። በአንድ ወለል ላይ እስከ ሶስት ሰው ተመልክቻለሁ። የየክፍሎቹ በሮች አለመቆለፋቸው ሴቶችን ለተጨማሪ አደጋ እንደሚያጋልጥ አለመታሰቡ ግን “ለምን ይሆን?” አስብሎኛል።   

መታጠቢያ ቤቶቹ “የመንግስት ጤና ጣቢያ” አይመስሉም። ንጹህ እና በአግባቡ የተሰሩ ናቸው፤ ኧረ! ውሃም አለች። በጤና ተቋሙ በነበረኝ ቆይታ ውሃም፤ መብራትም አልጠፉም። በህንፃው ግድግዳዎች ላይ የተሳሉት ስዕሎች አንድም ያዝናናሉ፤ ሁለትም ከተለመደው የህክምና ተቋም ንጣት እና መደበኛ እይታ ለየት ያደርጉታል። ከጤና ጣቢያው ጀርባ የደረቅ እና ፈሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃዎች አሉ፡፡ “ቺሚኒ” የሚመስለው የደረቅ ቆሻሻ ማቃጠያው በየእለቱ ምሽት ይለኮሳል፡፡ ሁለቱም ከክፍሌ ጀርባ ከርቀት ይታያሉ፡፡

ሐኪሞች በቀን አንዴ ወይም ሁለቴ ዞረው ክትትል ያደርጋሉ። ካላወሩ በቀር ወንድ እና ሴቱን መለየት ያስቸግራል። ሁሉ ነገራቸው ይሸፈናላ። ሐኪሞቹ ለክትትል በየክፍሉ ሲገቡ የሙቀት፤ የደም ግፊት እና የልብ ምት መለኪያ ይዘው ነው። እኔን እንኳ ከተወሰነ ቀን ውጪ ሙቀቴን ብቻ ነበር የሚለኩት። የሚሰማኝን ይጠይቃሉ። “ሐይማኖት እንዴት ነሽ? ” ጮክ ብለው ነው የሚያወሩት። “ትኩሳት አለ? ያልተመቸሽ ነገር አለ?  ምግብ ትበያለሽ? አይዞሽ ምንም ነገር ከፈለግሽ አለን፤ አትፍሪ›› ይሄ የተለመደ ንግግራቸው ነው። በትህትና እና በሀዘኔታ ያናግሩኛል።

ከዚያ ውጪ ሰው ዝር አይልም። “ባለ አረንጓዴ ዘንቢሉ ሰውዬ ብቻ በቀን ሶስቴ ይመጣል። ምግብ ከማድረስ ተግባሩ ባሻገር እርሱም ችግር ካለ ሳይጠይቅ አያልፍም። ብዙ ጊዜ ምግቡን ተቀብዬ መዝግቤ እጥለዋለሁ። አንዳንዴ ግፍ ስለሚሆንብኝ ውሃውን ብቻ ተቀብዬ “ይቅርብኝ” ስለው “ምግብ መጥቶልኝ እንደው” ይጠይቀኛል። ከዚህ ውጪ ማንንም ማዋራት የለም።

ለሰሚው ቀላል ይሁን እንጂ ከተማ መዞር፣ የቲቪ ቻናል እየቀየሩ መመልከት ወይም “የት ነሽ?” ሲባሉ “እዚህ ወይም እዚያ” ብሎ መመለስ ለለመደ ሰው ነገሩ መለስተኛ እስር ቤት ነው። ክብደቱ ግን ቀድሞ የስነ ልቦና ዝግጅት ካለማድረግ እንጂ በራሳችንም ሆነ ሳናውቅ በሽታ ቢገኝብን ከምናስተላልፍባቸው ሰዎች ጤንነት ጋር ሲነፃፀር ይህ ሁሉ ምንም ነው።

የጎረቤቴ ነገር  

በመጀመሪያው ዕለት የጤና ጣቢያ ውሎዬ ቀኑን ሙሉ ናሙና ይወስዳሉ የተባሉት ሰዎች ቢጠበቁም አልመጡም። ከራሴ በላይ ያሳሰበኝ እኔ ባለሁበት ወለል በተቃራኒ ያለች የአንዲት ወጣት ልጅ ሁኔታ ነው። ያለማቋረጥ ትስላለች። በክፍሎቻችን መካከል በትንሹ የስድስት ወይም የሰባት ሜትር ርቀት አለ። ግን የሳሏ ድምፅ ይሰማል። ሳሏ ሲመሽ እየባሰ መጣ። በሬን ገርበብ አድርጌ ስመለከት መቆም አቅቷት እንደምንም ደረጃውን ወርዳ ብትጣራም ከሐኪሞቹ መካከል ምላሽ የሰጣት የለም። 

የገባሁ ምሽት የተቀመጥኩባትን ባለ ሮዝ ቀለሟን ወንበር አልፋ፤ ወደ ሐኪሞቹ ቢሮ መሄድ ደግሞ አትችልም። ፖሊሱ በቁጣ ያጣድፋታል። ተመልሳ ትወጣለች። ወጣቷ ልጅ ከሳሏ ጋር ብቻ ሳይሆን ከእንባዋ እና ከሳጓ ጋርም ነበር የምትታገለው። ለሰዓታት ስታለቅስ መቆየቷን መገመት አያዳግትም። ከሩቅ ብመለከታትም ላጽናናት አለመቻሌ በጣም አስከፍቶኛል። ይሄ በሽታ አይኑ ይጥፋ። 

እናት እና አባቷ ቀን ላይ መጥተው ከጤና ጣቢያው ውጪ የገዙትን መድኃኒት አድርሰውላት ተመልሰዋል። መድኃኒት የያዘውን ላስቲክ ለፖሊሱ ሰጥተው ሲመለሱ በኮሪደሩ መስታወት አሻግሬ ተመልክቻለሁ። ልጃቸውን ማየት ቢፈልጉም ባለመቻላቸው በትካዜ የተወሰነ ቆመው ከተነጋገሩ በኋላ ነው የተመለሱት። መቼም ጭንቀታቸውን ለመረዳት አያስቸግርም። 

እንደምመለከታት ያየችው ወጣት “የራስ ምታት መድኃኒት አለሽ?” ስትለኝ ባንኜ “አዎ አለኝ ጠብቂኝ” ብዬ ወደ ክፍሌ ገብቼ ከቦርሳዬ ፓራሴታሞሌን ይዤ ወጣሁ። በበሮቻችን መሃል ያለ የደረጃ እጀታ ላይ “ሙሉ ስትራይፑን” አስቀምጬላት ተመለስኩ። ልክ ክፍሌ ስደርስ እሷም ከከፍሏ ወጥታ መድኃኒቱን ወሰደች።

“ከሰው መሃል ተደባልቆ ለኖረ የሰው ፍጡር እኒህ ሁሉ እንዲሁ የሚታለፉ ሳይሆኑ እንባ የሚያመጡ ክስተቶች ናቸው። የሰው ልጅ እንዲያ አዝኖ፣ ፈርቶ ባለበት ወቅት መራቅ እና ማሳቀቅ ያሳፍራል”

ከሰው መሃል ተደባልቆ ለኖረ የሰው ፍጡር እኒህ ሁሉ እንዲሁ የሚታለፉ ሳይሆኑ እንባ የሚያመጡ ክስተቶች ናቸው። የሰው ልጅ እንዲያ አዝኖ፣ ፈርቶ ባለበት ወቅት መራቅ እና ማሳቀቅ ቢያሳፍርም ግን ደግሞ ይችን ታክል መጠንቀቅ ለስንት ሰው ደህንነት እንደሚጠቅም ማሰቡ በራሱ ጊዜ ያፅናናል።

ሰአቱ በጣም እየመሸ ነው። የወጣቷ ሳል ግን ከማይቆመው ለቅሶዋ ጋር ተደማምሮ ተባብሷል። አሁን ትንፋሽ እያጠራት መምጣቱን መረዳት አልከበደኝም። ነገሩ ቢያሳስበኝ ሐኪሞቹ “ምንም ነገር ካስፈለገኝ” እንደውልላቸው የሰጡኝን ስልክ ቁጥር አውጥቼ ከምሽቱ አራት ሰዓት ገደማ ደወልኩ። ከደቂቃዎች በኋላ የተለመደውን ነጭ ልብስ ለብሰው መጡላት። ለረጅም ደቂቃ አዋሯት። ሲያጽናኗት እና ሲመክሯት ይሰማል። ግፋ ቢል ከአንድ ሰዓት በኋላ የሷም የእነርሱም ድምፅ ጠፋ።

ሐኪሞቹ ነገሮችን የሚከውኑት በተረጋጋ እና በማቆያ ውስጥ ያሉትን ሰዎች ሁኔታ በተረዳ መንፈስ ነው። ቁጣ አያውቁም። ለዚህ እንደ ማሳያ አንድ ነገር ላንሳ። ወደ ለይቶ ማቆያው በገባሁ ዕለት “ነገ ይወሰዳል” የተባለው ናሙና ሳይወሰድ በመቅረቱ ቅሬታ ገብቶኝ ነበር። አመሻሹ ላይ ሐኪሞቹን ጠርቼ ይህንኑ ቅሬታዬን ስገልጽላቸው የተለየ መልክ ሳያሳዩኝ ነበር ያደመጡኝ። 

አንደኛው ሐኪም ናሙና የሚወስዱት የህብረተሰብ ጤና ባለሞያዎች እንደሆኑ እና በቀን ውስጥ በተደጋጋሚ እንደደወላቸው ተናገረ። በአንድ ቀን ብዙ ናሙና ስለሚወስዱ ያንኑ ቀን (ሐሙስ) እስከ እኩለ ለሊት ሊመጡ እንደሚችሉ በእርጋታ አስረዳኝ። “የእኛ ኃላፊነት እዚህ እያላችሁ መሰረታዊ ፍላጎቶችችሁን እና ጤናችሁን መከታተል ነው።”  

ቀን ሁለት – አርብ

እንደ ደንቡ ቢሆን “እንዴት አደርሽ?” ተብሎ ይጠየቃል። አሁን እሱ የለም። ባለ አረንጓዴ ዘንቢሉ ሰውዬ የተለመዱትን ጥያቄዎች ጠይቆ፤ ምግቡን እና ውሃውን ሰጥቶኝ ሄደ። ሁለት ለሊት በማቆያ ባሳልፍም ናሙና አልተወሰደም። ያደክማል።

እንደተለመደው ላስቲኩን ከፍቼ ስመለከተው ሩዝ እና እንቁላል ፍርፍር ነበር። ሁሌም ቁርስ ቢያንስ ሁለት አይነት ምግብ ይቀርባል። ምሳ እና ራት፤ በትንሹ አራት አይነት። ምግቡ የተጠቀለለበት ላስቲክ በጣም የሚያቃጥል እና ትኩስ ነው። ‘እንዴት ስሙኒ ሳንከፍል ይሄንን ሁሉ አገልግሎት አቅርበው ይችሉታል?’ ስል ራሴን እጠይቃለሁ።

ከሁለት ጓደኞቼ ጋር በቋሚነት እናወራለን። ከራሴ በላይ የእነርሱ ጭንቀት ያስጨንቀኛል። ያው ስላለሁበት ሁኔታ የሚያውቁት እነሱ ብቻ መስለውኝ ነበር። ለካ በምኖርበት ግቢ በመቶዎች የሚቆጠር ሰው “እዚያ ብሎክ ኮሮና ያለባት ሰው ተገኘች” በሚል ተሸብረው ከርመዋል። 

እኔ በምኖረበት ህንፃ ላይም ሆነ በግቢው ውስጥ ብዙ ሆስተሶች፣ ፓይለቶች እና የአውሮፕላን ቴክኒሻኖች ይኖራሉ። እናም “የተጠረጠረችው ሆስተስ ነች” ብለው ተነጋግረው ጨርሰዋል። ሱቅ የሚላኩኝ የግቢው ጠባቂዎች ግን እኔ መሆኔን ጠርጥረው ይደውላሉ። ላለመዋሸት ስልክ አላነሳም። የብሎኩ ነዋሪዎች ከፍተኛ መገለል እንደደረሰባቸው ከማቆያ ስወጣ ነበር ያስረዱኝ። ተመላላሽ ሰራተኛ ያላቸው እንደቀሩባቸው፤ ከውጪ እቃ የሚሸከሙ ልጆችም እዚያ ግቢ አንገባም ማለታቸውን በስተኋላ ሰማሁ።

አርብ አድካሚም፤ ተስፋ አስቆራጭም ነበር። በትግስት ለመጠበቅ ብወስንም ለአላስፈላጊ ቀናት በማቆያው ውስጥ መቆየት በራሱ ለሌላ ጭንቀት ይዳርጋል። በመሰላቸት በስልክ ካማዋራቸው ሁለት ሰዎች ጋር ራሱ መነጋገር አቁሜአለሁ። የምታዘበውም ነገር ስላለቀ ሁኔታው ሰልችቶኛል። በዚህ መሃል የተሸፋፈኑት ሐኪሞች እኩለ ቀን አካባቢ የማይዘጋውን በር አንኳኩ። ናሙና የሚወስዱት ባለሙያዎች አብረው መምጣታቸውን ተረዳሁ።

በቴሌቪዥን የተመለከትኩትን በአፍንጫ ውስጥ የሚገባ በጣም ረጅም መሳሪያ ሳይ በጣም ደነገጥኩ። አንደኛው ባለሙያ የጆሮ ማጽጃ የሚመስል፣ በሁለቱም ጫፍ ጥጥ የተጠቀለለበት፣ ነጭ ቀጭን እንጨት እና የምትከደን የ”ሳምፕል” ማስቀመጫ ብልቃጥ ይዞ አጠገቤ ደረሰ። ከጉሮሮዬ ላይ የምራቅ ቅንጣት በመውሰድ፣ ብልቃጧ ውስጥ አንደኛውን ጫፍ በመክተት፣ እንጨቷን እዛው ሰብሮ ከደናት። የናሙና አወሳሰዱ ምንም ህመም በሌለው መልኩ የተካሄደ ነበር። “መቼ ነው ውጤት የሚመጣው” ብዬ ሰውዬውን ጠየቅኩት። “እንደ ሁኔታው ይለያያል” ብሎኝ ወጣ።

‘ውጤቱ በ24 ሰዓት ይመጣል’ ብዬ ደመደምኩ። ‘ይህም ማለት ቅዳሜ ከሰዓትን ቤቴ እውላለሁ’ በሚል እሳቤ ቀሪውን ሰዓት በተስፋ አሳለፍኩ። ነገር ግን ውጤቱ ሌላ ቢሆንስ? ለረጅም ጊዜ መቆየቴን አሰብኩ። ‘ቤተሰቦቼ ሲሰሙ ምን ይፈጠራል’ የሚለው ወደ አእምሮዬ ይመላለሳል። የጎረቤቴ ውጤትም አሳስቦኛል። የእርሷም ናሙና እስከ ትላንት ምሽት ድረስ አለመወሰዱን አይቼያለሁ። ቢያንስ እንደ እርሷ ከፍተኛ ምልክት ያለበትን ሰው በጊዜ መመርመር ቢቻል የተሻለ ነበር። አንድም አብረው በማቆያው ውስጥ ላሉ ሰዎች፤ ሌላም ሳይረፍድ ህክምና ለመስጠት።

የኮሮና መድኃኒት- “ጥምዝ መኮሮኒ” 

እንደምንም ቀኑ አልፎ 10 ሰዓት ገደማ ሲሆን ከታች የማያቋርጥ ጭቅጭቅ መሰማት ጀመረ። አምቡላንሶቹ አዲስ ሰው ይዘው መጥተዋል። በአርባዎቹ መጀመሪያ ላይ የምትገኝ ሴት ስልክ እያወራች ሮዟ ወንበር ላይ ተቀምጣለች። ከነጩ ጣውላ በስተጀርባ ሐኪሞቹ ተሰብስበው ይመለከቷታል። አፍ እና አፍንጫቸውን በጭምብል፤ እጃቸውን በጓንት የሸፈኑ ሁለት ፖሊሶች ተቀምጠው ይጠብቋታል። ጠብመንጃ ይዘዋል።

“ሄሎ ሲስትር! ባለፈው ወረዳ ወስደውኝ ተመርምሬ ነፃ ተብዬ የለ? እንዴ እኔ የማንም መጫወቻ ነኝ እንዴ?” አሁንም ጮህ ብላ በስልክ ታወራለች። ያመጧት የአምቡላንስ እና የጤና ቢሮ ሰራተኞች ጥለዋት እንዳይሄዱ ትቆጣቸዋለች። እነሱ በዝምታ አምቡላንሱን በ“ዲስ ኢንፌክታንት” ግፋ ቢል ለአንድ ሰዓት ያህል አጽድተው ሲጨርሱ ሄዱ። አዲስ ገቢዋ አላረፈችም። ፊቷን ወደ ሐኪሞቹ አዙራ ትቆጣቸዋለች፤ ያለመታከት ያባብሏታል።

“ይሄውልህ ዶክተር፤ ኮሮና የሚባል ነገር የለም። ኮሮና እኮ ጠፍቷል። አልሰማችሁም እንዴ፤ በል እኔ ልንገርህ፤ ኮሮና ጠፍቷል። ደሞ መድኃኒቱን ልንገርህ፤ ጥምዙን መኮሮኒ ቀቅለህ መብላት ነው፤ ታዲያ ጥምዙ ነው ሌላው አይሆንም”

ወደ ጤና ጣቢያ የመጣች የኮሮና ተጠርጣሪ

“ይሄውልህ ዶክተር፤ ኮሮና የሚባል ነገር የለም። ኮሮና እኮ ጠፍቷል። አልሰማችሁም እንዴ፤ በል እኔ ልንገርህ፤ ኮሮና ጠፍቷል። ደሞ መድኃኒቱን ልንገርህ፤ ጥምዙን መኮሮኒ ቀቅለህ መብላት ነው፤ ታዲያ ጥምዙ ነው ሌላው አይሆንም”።

ሐኪሞቹ በቁምነገር ምላሽ ይሰጧታል።  ወደ ፎቅ ላይ አልወጣ ብላቸው ይመስለኛል እንዲሁ ሲነጋገሩ ቀኑ መሽቶ ሐኪሞች በየክፍሉ የሚዞሩበት ሰዓት ደረሰ። ዛሬ አንዷ ሐኪም ለብቻዋ ነው የመጣችው።

ሙቀቴን፤ የልብ ምቴን እና የደም ግፊቴን ለክታ “ምነው ዛሬ ተጨንቀሻል እንዴ?” ብላ ጠየቀችኝ። የቱ ከፍ እንዳለ ባትነግረኝም ግን ሁሉም ከሚጠበቀው በላይ አላለፈም ብላ አስረዳችኝ። “ሴትየዋ በጠበጠቻችሁ አይደል? በጣም ይቅርታ። የተወሰነ ‘ሜንታል ኬዝ’ ያላት ይመስለናል። አሁን መጥተው ይወስዷታል፤ እስከዚያ ተቸገሩልን” አለች። እስከ ምሽቱ ሶስት ሰዓት ያለመሰላቸት እሷን ሲያጫውቱ ማምሸታቸው ገርሞኛል፤ እነሱ ስለእኛ ይጨነቃሉ።

አራት ሰአት አካባቢ በደረጃው መኃል ስመለከት የአፍ መሸፈኛ እና እንዳይበርዳት የሚደረብ ሰጥተዋት፤ እሷ ሮዟ ወንበር ላይ እነሱ ደግሞ ከነጩ ጣውላ ወዲያ ተሰብስበው ይሳሳቃሉ፤ ይጫወታሉ። ነገሩ ያስቀናል፤ የሚያጫውት ሰው ማግኘት ያስቀናል። አራት ሰዓት ካለፈ በኋላ እነርሱም ድምጻቸው ጠፋ። 

“ኑዛዜሽን አዘጋጀሽ”

ሶስተኛው ቀን ቅዳሜ ሲነጋ በሳቅ ነው የተጀመረው። ባለ ዘንቢሉ ሰውዬ እንደተለመደው ቁርስ ይዞ መጣ። ዛሬ በርገር እና ማኮሮኒ ነው። በየመሃሉ በስልክ የማወራቸው ሁለቱ ጓደኞቼ የሚቀርብልኝን የምግብ አይነት ከእኔ እኩል ይከታተላሉ። በርገሩ፤ ቤት ውስጥ የሚሰራ አይነት ቢሆንም፤ መቅረቡ በራሱ በጣም አሳቀን። ያልጠበቅነው ቢሆንብን። ከባህር ወዲያ ያለው ጓደኛዬ “ወይኔ አገሬ” እያለ ነገሩን ካለበት አገር አገልግሎት ጋር እያነፃፀረ በመደነቅ ያመናፍሰዋል፡፡

‘ከሰዓት መውጣቴ አይቀርም’ በሚል በጠዋት ተዘገጃጅቼ፤ ቡና እና ምግብ እንደተለመደው አዘዝኩ። ምግብ ይዞ የሚመጣው ሞተረኛ ከጤና ጣቢያው ሲደርስ፤ ያመጣውን ከግቢው በር ተቀብሎ፤ ከእኔ ደግሞ ገንዘብ ተቀብሎ የሚሰጥ ሰው ያስፈልጋል። ከህንጻው ውጪ ንቅንቅ ማለት አይቻልማ። የኤሌክትሮኒክ ክፍያ ቢኖር ደግሞ የገንዘብ ንክኪውን ማስቀረት ይቻል ነበር፡፡

ምግቡን ተቀብሎ ላመጣልኝ ሰው ገንዘቡን ስሰጠው ያልጠበቅኩትን ነገር አለኝ – “ኑዛዜሽን አዘጋጀሽ”

የህንጻውን ደረጃ ወርጄ ምግቡን ተቀብሎ ላመጣልኝ ሰው ገንዘቡን ስሰጠው ያልጠበቅኩትን ነገር አለኝ – “ኑዛዜሽን አዘጋጀሽ”። ‘ጆሮዬ ነው ወይስ አፉ ላይ ያጠለቀው ማስክ’ ብዬ ከአንዴም ሶስት ጊዜ ጠየቅኩት። ደግሞ ደጋግሞ አለኝ – “ኑዛዜሽን አዘጋጀሽ”። 

“የመሞት ሀሳብ የለኝም” ብዬው ፈገግ ብዬ ወደ ክፍሌ ተመለስኩ። ምንም የበሸታው ምልክት የለብኝም። የኮሮና ቫይረስ ቢገኝብኝም ከመሞት ይልቅ ታግሎ የመዳን እንጂ እሞታለሁ የሚል ፍራቻ አልነበረኝም። ሰውየው ፖሊስ ይሁን የጽዳት ሰራተኛ አላወቅሁም። የተናገረው ነገር ግን አስደነገጠኝ፤ ደግሞም አስገረመኝ። በእለቱ የቫይረሱን የሞት ምጣኔ ደጋግሜ “ጉግል” ማድረጌም ከዚሁ ንግግሩ የመነጨ ሊሆን ይችላል።

‘ሌላ ሰው ቢሆን ምን ያስባል?’ ራሴን ጠየቅሁ። ሁሉም ስለሚሸፋፈኑ ማን ይሁን ማን አይታወቅም። የሁሉም አለባበስ አንድ ነው። ይሄ ሰው ሐኪም ቢመስላቸውስ? ሰውየው ‘ሞት እንደሆነ አይቀርልሽም’ የሚል መልዕክቱ ምን ያህል ጉዳት እንደሚያመጣ ያወቀም አይመስለኝ። በለይቶ ማቆያ ያሉ ሰራተኞች ሐኪሞችም ይሁኑ ረዳት ባልደረቦቻቸው፣ ፖሊሶችም ይሁኑ ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች ተጨማሪ እና ከበሽታው መለዋወጥ ጋር አብሮ የሚሄድ ስልጠና እንደሚያስፈልጋቸው ይህ “ኑዛዜ” የጠየቀኝ ባልደረባ ምስክር ነው።

ብቻ ውጤቱም አልመጣም፤ ቅዳሜም መሸ። አራተኛ ለሊት! እሁድም ምንም የተለየ ነገር ሳይከሰት ነግቶ መሸ፤ ውጤቱ አሁንም አልመጣም። አሁን ነገር አለሙን ለምጄዋለሁ። ምናልባት ለቀጣይ ተከታታይ ቀናት ውጤቱ ላይመጣ እንደሚችል ራሴን አሳምኜ ተከታታይ ፊልሞች መርጬ መመልከት ጀምሬያለሁ። 

ተስፋ የመቁረጥ አይነት ስሜት አይሰማኝም። ሌሎች ሰዎች ግን ይህን ያህል ቀናት ከቆዩ በኋላ እንደእኔ አይነት ስሜት ይሰማቸው እርግጠኛ አይደለሁም። ሰዎች ቫይረሱ ይኖርብኛል ብለው ከጠረጠሩ ወደ ህክምና ከመምጣት ይልቅ ሲሸሹ እና ሲያመልጡ እየተመለከትን ነው። ብዙዎቻችን ለምን ብለን የጠየቅን ግን አይመስለኝም። በበሽታው የተያዙ ሰዎች አግባብ ያለው ጥንቃቄ በማድረግ ካልተንከባከብናቸው ተስፋ መቁረጥ ሊከተል እንደሚችል ማሰቡ ተገቢ ነው። 

የምርምራው ውጤት መጨረሻ

ሰኞ ጠዋት አራት ሰዓት አካባቢ ህንፃው ላይ ያሉ ሰዎች ይነጋገራሉ። ከወትሮው የተለየ ጫጫታ ይሰማኛል። በየመሃሉ “ውጤት መጥቶ ነፃ ተብዬአለሁ” የሚሉ ድምፆች ይሰሙኛል። ግራ ገባኝ። ሲሰነባበቱም ይሰማኛል። ከአልጋዬ ውስጥ ሳልወጣ ከ30 ደቂቃዎች በላይ ጠበቅሁ። ወደኔ ግን ማንም አልመጣም። እነዚህ ደቂቃዎች ቀላል ከመሰሏችሁ በጣም ተሳስታችኋል።

“ኦኬ! እኔ ቫይረሱ አለብኝ ማለት ነው። እነሱ እየወጡ ለኔ ያልተነገረኝ ለዚህ ነው። አሁን ለቤተሰብ ስናገር ምን እባላለሁ” እናቴ በጭንቀት ስትሞት ይታየኛል። ለደቂቃዎች አልጋዬ ውስጥ ጉልበቴን ታቅፌ ቁጭ አልኩ። ከብዙ ጥበቃ በኋላ ሐኪሟ በሬን አንኳኳች።

“ሐይማኖት አትወጪም እንዴ? ሁላችሁም ነፃ ናችሁ ተባለ እኮ!” በመጨረሻም ሰውነቴ ሲላቀቅ ይሰማኛል። አብረውኝ ሲጨነቁ ለከረሙት ሶስት ሰዎች ደወልኩ። አዎ ሶስት ሆነዋል፡፡ በመሃል ገንዘብ እና ሌሎች የሚያስፈልጉኝ ነገሮችን መጠየቅ ስለነበረብኝ አንድ ተጨማሪ ጓደኛዬም ሰምቶ አብሮን ሲጨነቅ ከርሟል፡፡ ብቻ ፈነደቅን። ሐኪሟ ግን ድጋሚ ጠራችኝ።

“የዛሬው ዜና መልካም ቢሆንም ኮሮና ከዚህ በኋላ አይዝሽም ማለት አይደለም። አሁን የበለጠ ጥንቃቄ ያስፈልግሻል። አደራ!” ትክክለኛ ምክር እንደሆነ የተረዳሁት ቀጥሎ ባሉት ቀናት ነበር። ነፃ ነሽ ስባል በቅርብም በሩቅም ያሉ ቤተሰቦቼን ሁሉ የመጠየቅ ጉጉቴ ጨመረ።

ስንወጣ የያዝነው ነገር በሙሉ “ዲስኢንፌክት” ይደረጋል። መላ አካላቱን የተሸፋፈነ ሰው፤ ጀሪካን በጀርባው ተሸክሞ፤ የሚወጣውን ሰው ሁሉ ኬሚካል ይረጫል። ሐኪሞቹ በተለመደችው የነጯ ጣውላ ድንበራቸውን አስጠብቀው አንድ በአንድ እየጠሩ ያስፈርማሉ። ሁሉም ሰው እየፈረመ እና እያመሰገነ ይወጣል። የጤና ጣቢያው ሰራተኞች የመጨረሻ እርምጃ ሁሉንም ሰው በየቤቱ ማድረስ ነው። ግቢውን ለቅቄ ስወጣ እፎይታ ቢሰማኝም፤ ለምርመራ ብቻ አንድን ሰው ለስድስት ቀን በዚህ መልኩ ማቆየት፤ ከምንም በላይ የህዝብን ሃብት ማባከን መሆኑን እያሰላሰልኩ ነበር። 

ገና ለገና ለይቶ ማቆያ ውስጥ በመግባታቸው ብቻ ሰዎች ራሳቸውን ሲጎዱ ስመለከት ምን አልባት የራሴን ታሪክ ባካፍል ይጠቅም ይሆናል ብዬ ገመትኩ።

በአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ውስጥ የነበረኝን ቆይታ በዝርዝር የመዘገብኩበት ዋነኛ ምክንያት ቆይታዬ በጣም አሰልቺ እንዳይሆን በማሰብ ነበር። ‘ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ለማድረግ በመወሰናቸው ብቻ ማህበራዊ መገለል ያጋጥማቸዋል’ የሚል ግምት ስላልነበረኝ ምናልባት ለስራዬ ግብዓት ላደርገው እንደምችል ማሰቤም አልቀረም። ኋላ ላይ ያገኘሁት ግብረ መልስ ግን አስደንጋጭ ነበር። በስተመጨረሻ ገና ለገና ለይቶ ማቆያ ውስጥ በመግባታቸው ብቻ ሰዎች ራሳቸውን ሲጎዱ ስመለከት ምን አልባት የራሴን ታሪክ ባካፍል ይጠቅም ይሆናል ብዬ ገመትኩ።

ከዚህ ባሻገርም የኮሮና ቫይረስ የያዛቸው ሰዎች፣ ከበሽታው ያገገሙ ግለሰቦች እና የህክምና ባለሙያዎች እያጋጠማቸው ያለው መገለል እና እየደረሰባቸው ያለው የስነልቦና ጫና ምናልባት በዚሁ ትኩረት ያገኛል ብዬ እገምታለሁ። በሽታው በአገራችን ገና ሚሊዮኖችን ሊይዝ እንደሚችል ከመንግስት ዘንድ የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህ ከግምት ውስጥ ሲገባ ከኮሮና ጋር ለተያያዙ እኒህን መሰል ጉዳዩች ይበልጥ ትኩረት መስጠት ለነገ የማይባል ስራ ነው እላለሁ። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)