በተስፋለም ወልደየስ
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የደቡብ ክልልን በአዲስ መልክ ለማዋቀር በተዘጋጀ ምክረ ሀሳብ ላይ ከክልሉ አመራሮች ጋር ነገ ሰኞ ሰኔ 1 ፤ 2012 ሊወያዩ ነው። በውይይቱ ላይ የክልሉ የዞን እና ልዩ ወረዳ አስተዳዳሪዎች ይሳተፋሉ ተብሏል።
የነገው ስብሰባ የክልሉን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ለመወሰን የሚያስችል እንደሚሆን ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ስብሰባው አጠቃላይ የክልሉን አደረጃጀት ለመወሰን የሚደረግ እንደሆነ በውይይቱ ላይ የሚሳተፉ አንድ አመራር አረጋግጠዋል።
በ17 ዞኖች እና አራት ልዩ ወረዳዎች የተዋቀረው የደቡብ ክልል፤ የሲዳማ ዞን በክልል ለመደራጀት ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱን ተከትሎ ተመሳሳይ ጥያቄዎችን ሲያስተናግድ ቆይቷል። አስራ አንድ የክልሉ ዞኖች በየምክር ቤቶቻቸው የክልልነት ጥያቄን ቢያጸደቁም፤ በህዝበ ውሳኔ ራሱን ችሎ ክልል መሆን እንደሚችል ያረጋገጠው የሲዳማ ዞን ብቻ ነው።
የፌደራል መንግስት በደቡብ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የቀረቡ የክልልነት ጥያቄዎችን “በሰላማዊ መንገድ ለመመለስ” እና “በክልሉ የተረጋጋ አመራር ለመስጠት” በሚል ሐዋሳ ከተማን ጨምሮ ሁሉም ዞኖች፣ ከተማ አስተዳደሮች እና ልዩ ወረዳዎች ከሐምሌ 15፤ 2011 ጀምሮ በጊዜያዊ ኮማንድ ፖስት ስር እንዲሆኑ ማድረጉ ይታወሳል። የደቡብ ክልልም የቀረቡለትን የክልልነት ጥያቄዎች “በሳይንሳዊ ጥናት” እንዲመልስ አጥኚ ቡድን አቋቋሙ መፍትሄ ያለውን ሲያፈላልግ ቆይቷል።
የጥናት በድኑ ካቀረባቸው መፍትሔዎች መካከል ክልሉን ከሁለት እስከ አምስት ቦታዎች በመክፈል መልሶ ማደራጀት የሚለው ይገኝበታል። ባለፉት ወራት በክልሉ በተደረጉ የተለያዩ ውይይቶች ይህ የመፍትሔ ሀሳብ ይበልጥ ተቀባይነት ማግኘቱን እና የደቡብ ክልል እንዴት ይከፈል? በሚለው ላይ አማራጮች ሲንሸራሸሩ መቆየታቸውን ጉዳዩን በቅርበት የተከታተሉ ምንጮች አስረድተዋል። በነገው ስብሰባ ላይ የሚሳተፉ አመራር እኒህን አማራጮች የያዘ ምክረ ሀሳብ መዘጋጀቱን እንደሚያውቁ ገልጸዋል።
“ከሲዳማ ውጭ ያለውና ደቡብ ክልል የሚባለው ከዚህ በኋላ ይፈርሳል። አራት ክልሎች ተብሎ ለመደራጀት ፕሮፖዛል ቀርቧል። የነገው ውይይት ፕሮፖዛሉ ላይ ተወያይቶ መግባባት ላይ ለመድረስ ነው”
“ከሲዳማ ውጭ ያለውና ደቡብ ክልል የሚባለው ከዚህ በኋላ ይፈርሳል። አራት ክልሎች ተብሎ ለመደራጀት ፕሮፖዛል ቀርቧል። የነገው ውይይት ፕሮፖዛሉ ላይ ተወያይቶ መግባባት ላይ ለመድረስ ነው” ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
በነገው ዕለት በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት በሚካሄደው ውይይት ላይ እንዲገኙ ጥሪ የተላለፈላቸው የዞን እና የልዩ ወረዳ አስተዳዳሪዎች ዛሬ ወደ አዲስ አበባ በመግባት ላይ መሆናቸውን የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጮች አረጋግጠዋል። ውይይቱ ነገ ጠዋት እንደሚካሄድ አስቀድሞ ቀጠሮ ቢያዝም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በተመሳሳይ ሰዓት በተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እንደሚሰጡ መገለጹ መደናገርን ፈጥሯል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የደቡብ ክልል የመዋቅር ጥያቄን አስመልክቶ በክልሉ ከሚገኙ የዞን አመራሮች ጋር ከዚህ ቀደምም በአዲስ አበባ ውይይት አደርገው ነበር። በዚህ ወር መጀመሪያ በጽህፈት ቤታቸው በተደረገው ውይይት በክልሉ “ባለ ብዙ ገጽ ዕድገት እና ዘላቂ ሰላም እንዲኖር” የአስተዳደራዊ መዋቅር መርሆውን ቅድሚያ ሰጥቶ መመልከት አስፈላጊ እንደ ሆነ ከአመራሮቹ ጋር መስማማታቸውን አስታወቀው ነበር።
በዚሁ ውይይት ላይ በዝርዝር ሊታዩ የሚገባቸው ሌሎች ጉዳዩች መነሳታቸውን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ጉዳዮቹ የበለጠ ዳብረው ተመልሰን እንድንወያይባቸው ስምምነት ላይ ደርሰናል” ሲሉም በወቅቱ ገልጸዋል። በውይይቱ ላይ የቀረበው ሰነድ “የጌዲኦ፣ ቡርጂ እና አማሮ ህዝቦች ያማከለ አልነበረም” የሚል ቅሬታ ቀርቦ እንደነበር የሚያስታወሱት በስብሰባው የተሳተፉ አመራር፤ ከዚያ ተከትሎ በነበሩ ሳምንታት ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የተላኩ ሰዎች ወደ አካባቢው ተንቀሳቅሰው ከህብረተሰቡ ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።
በነገው ስብሰባ የሚቀርበው ምክረ ሀሳብ ከእነዚህ አካባቢዎች የተገኙ ግብዓቶችን ያካትታል ተብሎ እንደሚጠበቅ እኚሁ አመራር አብራርተዋል። ምክረ ሃሳቡ “ዋናው መሰረት ያደረገው የህዝብን ፍላጎት ነው” ብለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)