በሐይማኖት አሸናፊ
በፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ዛሬ ጠዋት ቀርበው የነበሩት ጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስ ላይ ቀሪ ምርመራዎችን ለማካሄድ ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ የጠየቀው ፖሊስ ስድስት ቀን ተፈቀደለት።
አርብ መጋቢት 18፤ 2012 በቅርብ ዘመዳቸው መኖሪያ ቤት በቁጥጥር ስር የዋሉት ያየሰው ከመታሰራቸው አንድ ቀን በፊት “ኢትዮ ፎረም” በተሰኘው የዩቲዩብ ቻናላቸው ያሰራጩት መረጃ ለእስራቸው ምክንያት ሆኗል። የጋዜጠኛው መረጃ መንግስት በኮሮና ቫይረስ ምክንያት “200 ሺህ ጉድጓዶች እንዲዘጋጁ አዝዟል” የሚል ነበር።
ፖሊስ ጋዜጠኛ ያየሰውን በወንጀል ሕጉ ላይ “ሃሰተኛ መረጃ በማሰራጨት የተደነገገውን ተላልፈዋል” ሲል እንደጠረጠራቸው “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጧል። ያየሰው ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት የቀረቡት ቅዳሜ መጋቢት 19፤ 2012 ሲሆን ለፖሊስ የስድስት ቀን የምርመራ የጊዜ ቀጠሮ ተፈቅዶ እንደነበር ይታወሳል።
ጋዜጠኛ ያየሰው “ኢትዮ ፎረም” የተሰኘ በትግራይ ቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ የሚተላለፍ ሳምንታዊ የቴሌቪዥን የቃለመጠየቅ መሰናዶ አዘጋጅ ናቸው። የያየሰውን መታሰር የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ ድርጅቱ ሲ. ፒ. ጄ አውግዟል። ሲ. ፒ. ጄ ጋዜጠኛው በአፋጣኝ እንዲፈታ ጠይቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)