የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ከስልጣናቸው ለቀቁ

350

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም በገዛ ፍቃዳቸው ከስልጣናቸው መልቀቃቸውን የትግራይ ክልል መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ ዘገበ። አፈ ጉባኤዋ ከስልጣናቸው የለቀቁት “ሕገ መንግስቱን ከሚጥስ እና አምባገነን ስርዓት ጋር መስራት አልፈልግም” በሚል ምክንያት እንደሆነ መገናኛ ብዙሃኑ ገልጿል። 

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም በገዛ ፍቃዳቸው ከስልጣናቸው መልቀቃቸውን የትግራይ ክልል መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ ዘገበ። አፈ ጉባኤዋ ከስልጣናቸው የለቀቁት “ሕገ መንግስቱን ከሚጥስ እና አምባገነን ስርዓት ጋር መስራት አልፈልግም” በሚል ምክንያት እንደሆነ መገናኛ ብዙሃኑ ገልጿል።

የአፈ ጉባኤዋን ውሳኔ በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ወደ ጽህፈት ቤታቸው ብንደውልም የጽህፈት ቤቱ ሰራተኛ ስለ “ጉዳዩ እንደማያውቁ” ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ወይዘሮ ኬሪያ ዛሬ ወደ ጽህፈት ቤታቸው አለመግባታቸውንም ጠቁመዋል። 

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የዚህን ዓመት ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባውን ከነገ በስቲያ ሰኔ 3 እና በማግስቱ ሰኔ 4፤ 2012 ለማካሄድ ለአባላቱ ጥሪ አድርጎ ነበር። በኢትዮጵያ ሊካሂድ የነበረው የጠቅላላ ምርጫ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት መራዘሙን ተከትሎ የተወካዮች ምክር ቤት በሕገ መንግስቱ የተቀመጡ አንቀጾች ጉዳዩን በግልጽ እንደማያስረዱ በመጥቀስ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ተርጎሞ እንዲልክለት ጠይቆ ነበር።

የፌዴሬሽን ምክር ቤትን በህግ ጉዳዮች የማማከር ስልጣን ያለው የሕገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ፤ ጉዳዩ “የሕገ መንግስት ትርጉም ያስፈልገዋል ወይስ አያስፈልገውም” የሚለውን ለመወሰን የሕገ መንግስት እና ሌሎችን ባለሙያዎች ያሳተፈ ምክክር ለሳምንታት ሲያደርግ ቆይቷል። የሕገ መንግስት አጣሪ ጉባኤው ከምክክሮቹ በኋላ የደረሰበትን ውሳኔ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት መላኩን ባለፈው ሳምንት አስታውቆ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)