ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ በህዳሴው ግድብ ላይ የጀመሩትን የሶስትዮሽ ውይይት ሊቀጥሉ ነው። በሱዳን ጋባዥነት ነገ ማክሰኞ ሰኔ 2፤ 2012 በኢንተርኔት የቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት እንዲካሄድ ቀጠሮ በተያዘለት በዚህ ውይይት የአሜሪካ፣ የደቡብ አፍሪካ እና የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ታዛቢዎች ይሳተፋሉ ተብሏል።
በውይይቱ ላይ በህዳሴው ግድብ ድርድር እስካሁንም እልባት ያልተደረሰባቸው ጉዳዮች በአጀንዳነት እንደሚቀርቡ የሱዳን ዜና አገልግሎት (ሱና) ምሽቱን ዘግቧል። ሶስቱ ሀገራት ከታዛቢዎች ሚና ጋር በተያያዙ የአካሄድ ጉዳዩችም ላይ ይወያያሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የዜና ወኪሉ በዘገባው ጠቅሷል።
ለኢትዮጵያ እና ግብጽ አቻዎቻቸው የውይይት ጥሪ ያቀረቡት የሱዳኑ የመስኖ እና ውሃ ሃብት ሚኒስትር ያሲር አባስ፤ ሶስቱ ሀገራት “ስምምነት ላይ ለመድረስ ጋሬጣ የሆኑባቸውን ጉዳዩች የመፍታት አቅም አላቸው” ብለዋል። ከህዳሴው ግድብ የውሃ ሙሌት እና አስተዳደር ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ስምምነት እንዳይደረስ እንቅፋት እንደነበሩ ያስታወሱት ሚኒስትሩ ሶስቱ ሀገራት ለዚህ መፍትሔ ያበጁለታል የሚል “ተስፋ እና መተማመን” እንዳላቸው ገልጸዋል።

ሱዳን በጉዳዩ ላይ የሚደረጉ ድርድሮች “በቅን ልቦና ሊደረጉ ይገባል” የሚለው እምነቷን አጠንክራ እንደምትቀጥልበት ሚኒስትሩ አስታውቀዋል። ሀገራቸው ጉዳዩን የሚመለከቱ የዓለም አቀፍ ህጎችን ብታከብርም የራሷን ጥቅም ከማስጠበቅም ወደ ኋላ እንደማትል አስምረውበታል። ሚኒስትሩ ከትላንት በስቲያ ቅዳሜ በሱዳን ብሔራዊ ቴሌቪዝን ጣቢያ ላይ በተላለፈ የከፍተኛ ባለስልጣናት ቃለ ምልልስም ይህንኑ አቋም አንጸባርቀዋል።
ሚኒስትሩ ሱዳን በህዳሴ ግድብ ላይ በምታራምደው አቋም “አንዴ የግብጽ፤ ሌላ ጊዜ የኢትዮጵያ ደጋፊ አድርጎ” የመወንጀል አካሄድ እንደሚስተዋል ጠቁመው፤ ሆኖም ሀገራቸው የምትከተለው አካሄድ “ብሔራዊ ጥቅሟን ማስጠበቅ ነው” ብለዋል። ኢትዮጵያ ግድቡን በውኃ መሙላት ከመጀመሯ በፊት በሶስቱ አገሮች መካከል ስምምነት ሊደረስ እንደሚገባም በቃለ ምልልሳቸው ገልጸዋል።
የህዳሴ ግድብ ውኃ ሲሞላ በሱዳኖቹ ሮሴይረስ እና ስናር ግድቦች ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል ያሉት የመስኖ ሚኒስትሩ ይህም “አስቀድሞ ከስምምነት መድረስን አንገብጋቢ ያደርገዋል” ብለዋል። ከኢትዮጵያ ድንበር በ60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ሮሴይረስ ግድብ፤ በህዳሴ ግድብ ላይ ጥገኛ እንደሚሆንም አስታውሰዋል። ሚኒስትሩ “በግድቡ የከፋ ተጽዕኖ የሚደርስባት ሱዳን ነች” ሲሉም ተደምጠዋል።
በቃለ ምልልሱ ላይ የተሳተፉት የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስማ መሀመድ ሀገራቸው የህዳሴው ግድብ “ውሃ አሞላል እና አስተዳደር መርህን የተመለከተ ስምምነት እንዲፈጸም” አጥብቃ እንደምትሻ ተናግረዋል። ይህ ስምምነት እውን እንዲሆን ሀገራቸው በተለያዩ የድርድር ዙሮች ሀሳብ ማቅረቧንም በቃለ ምልልሱ አጽንኦት ሰጥተው አንስተዋል።
“በግድቡ የከፋ ተጽዕኖ የሚደርስባት ሱዳን ነች”
የሱዳን የመስኖ እና ውሃ ሃብት ሚኒስትር ያሲር አባስ
ሱዳን ሁልጊዜም ለድርድር ጥሪ የምታቀርበው ልዩነቶችን ለመፍታት “ብቸኛው መፍትሔ” በመሆኑ ምክንያት እንደሆነ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ተናግረዋል። በሶስቱ አገሮች መካከል ያሉትን ልዩነቶች ለማጥበብ እና ሀሳቦቻቸውን ለማቀራረብ፤ የአሜሪካ እና የዓለም ባንክ አሸማጋዮች የተጫወቱትን ሚና ማድነቃቸውንም የሱዳን ዜና አገልግሎት (ሱና) ዘግቧል። በአሜሪካ የትሪዠሪ መስሪያ ቤት የተወከለው የሀገሪቱ የአሸማጋዮች ቡድን ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለው መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሯ፤ በህዳሴ ግድብ ላይ ከስምምነት እንዲደረስ ያለውን ከፍ ያለ ፍላጎትንም አንስተዋል።
ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ይህን ቢሉም ሀገራቸው አሜሪካ ባለፈው የካቲት ወር ለሶስቱ አገሮች ያዘጋጀችውን ስምምነት ሳትፈርም ቀርታለች። ስምምነቱ በቀረበበት የየካቲቱ የዋሽንግተን ዲሲ ስብሰባ ላይ ያልተሳተፈችው ኢትዮጵያም ስምምነቱን አልተቀበለችውም። ሶስቱ አገሮች ከአንዳች ስምምነት ሳይደርሱ የህዳሴው ግድብ በውኃ እንዳይይሞላ አሜሪካ ያስተላለፈችው ማሳሰቢያም በኢትዮጵያ በኩል ተቀባይነት አላገኘም። ከዚያም በኋላ በተከተሉት ጊዜያት ኢትዮጵያ የዋሽንግተኑን ድርድር እርግፋ አድርጋ መተዋን የውኃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ ገልጸው ነበር።
የዋሽንግተኑ ድርድር ያለ ውጤት ከተበተነ በኋላ ሱዳን የሁሉም ወገኖች አይን ያረፈባት ሆናለች። ሀገሪቱ ግብጽ ኢትዮጵያን ለማውገዝ በአረብ ሊግ በኩል ያዘጋጀችውን የውሳኔ ሐሳብ ውድቅ ማድረጓ በወቅቱ አነጋግሯል። ሱዳን፤ የህዳሴው ግድብ የውሃ ሙሌትን በተመለከተ ኢትዮጵያ ያዘጋጀችውን ሰነድም አልቀበልም ማለቷ ይታወሳል።
የዋሽንግተኑ ድርድር ያለ ውጤት ከተበተነ በኋላ ሱዳን የሁሉም ወገኖች አይን ያረፈባት ሆናለች። ሀገሪቱ ግብጽ ኢትዮጵያን ለማውገዝ በአረብ ሊግ በኩል ያዘጋጀችውን የውሳኔ ሐሳብ ውድቅ ማድረጓ በወቅቱ አነጋግሯል። ሱዳን፤ የህዳሴው ግድብ የውሃ ሙሌትን በተመለከተ ኢትዮጵያ ያዘጋጀችውን ሰነድም አልቀበልም ማለቷ ይታወሳል።

ሱዳን “የህዳሴው ግድብ በውሃ ከመሞላቱ አስቀድሞ በሶስቱ ሀገራት መካከል ስምምነት መደረስ አለበት” የሚለውን አቋሟን ደጋግማ ብታንጸባርቅም ኢትዮጵያ ግን በመጪው ሐምሌ ለመጀመር ባቀደችው የውሃ ሙሌት ለመግፋት ቆርጣለች። ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ትናንት እሁድ ግድቡን የጎበኙት የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ስለሺ በቀለም ይህንኑ በድጋሚ አረጋግጠዋል።
ዶ/ር ስለሺ “በክረምቱ ውሃ መያዝ ለመጀመር በተያዘው እቅድ መሰረት ግንባታ እየተፋጠነ ነው” ብለዋል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበኩላቸው “በቀጣይ ጥቂት ሳምንታት ውስጥ” ግድቡ ውሃ ማጠራቀም እንደሚጀምር መንግሥታቸው ከግንባታ ባለሙያዎቹ ማረጋገጫ ማግኘቱን ለብሔራዊው የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)