የኮሮናን ወረርሽኝ ለመከላከል በሚቀጥለው ሳምንት ተጨማሪ እርምጃዎች እንደሚወሰዱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ተናገሩ

በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል በሚቀጥለው ሳምንት ተጨማሪ እርምጃዎች እንደሚወሰዱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ፡፡ መንግስታቸው በሌላው ሀገር እንደሚታየው በኢትዮጵያ ያለውን የገበያ እንቅስቃሴ መሉ ለሙሉ እንደማይዘጋም ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ይህንን የገለጹት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን አስመልክቶ ዛሬ ቅዳሜ ፤ መጋቢት 26 ምሽት በሰጡት መግለጫ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግስት በቀጣይነት የሚወስዳቸው አዳዲስ እርምጃዎች “ሀገር እና ትውልድን ለማስቀጠል” የሚደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

“ወረርሽኙ በሚቀጥለው ሳምንት ያለውን አካሄድ (trend) በማየት ተጨማሪ እርምጃዎች በመውሰድ ሀገር እና ትውልድ ለማስቀጠል ጥረት የምናደርግ ይሆናል” ብለዋል፡፡ የግብይት እንቅስቃሴን መሉ ለሙሉ የመዝጋት እርምጃ ግን በመንግስታቸው እንዳልታሰበ ጥቆማ ሰጥተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ይህን አይነት እርምጃ እንድትወሰድ የሚሹ ሰዎች እንዳሉ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግስታቸው ይህን መተግበር የማይፈልግበትን አመክንዮ አስረድተዋል፡፡ “ኢትዮጵያን የተሻለ አቅም እንዳላቸው ሀገራት እንዳንዘጋ የሚያደርገን፤ ሁላችሁም ቤታችሁ ግቡ ብንል ቤት የሌላቸው፣ በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎች እንዳሉ ስለምናውቅ [ነው]” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲህ አይነት እርምጃ ቢወሰድ መጠለያ ያላቸውም ጭምር ችግር ላይ እንድሚወድቁ ገልጸዋል፡፡

“ኢትዮጵያን የተሻለ አቅም እንዳላቸው ሀገራት እንዳንዘጋ የሚያደርገን፤ ሁላችሁም ቤታችሁ ግቡ ብንል ቤት የሌላቸው፣ በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎች እንዳሉ ስለምናውቅ [ነው]”

“ቤት ያላቸውም ቢሆኑ በቀን ወጥተው የዕለት ጉርሳቸውን ካልሰሩ፣ መንግስት ምግብ ማቅረብ የማይችል፤ እነሱ ደግሞ የማይወጡ፣ የማይበሉ ከሆነ፤ በአንድ መንገድ ህይወታቸውን ብንታደግም በሌላ መንገድ ህይወታቸውን ስለምናጣ [ነው]” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡ በዚህም ምክንያት “ሌላ ሀገር የታየውን እንዳለ አምጥቶ መተግበር” እንደሚያስቸግር አብራርተዋል፡፡

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በመከላከል ረገድ በኢትዮጵያውያን ዘንድ “እምብዛም የባህሪ ለውጥ አልታየም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህም ምክንያት “ስጋታችን ከፍተኛ ሆኗል” ብለዋል፡፡ “እስካሁን ኢትዮጵያ ውስጥ በበሽታው የሞተ ሰው ባለመኖሩ በሽታውን ቀለል አድርጎ የማየት እና ገዳይ እንዳልሆነ የመመልከት ዝንባሌ ይታያል” ሲሉም በህብረተሰቡ ዘንድ የሚታየውን መዘናጋት በመግለጫቸው አንስተዋል፡፡

በአፍሪካ የተሰራጨው የኮሮና ቫይረስ አሁን ባለው ራሱን የማባዛት አካሄድ ከቀጠለ እና ወደ ማጥቃት ከተሸጋገረ “የመከላከል አቅማችን በእጅጉ ሊፈተን ይችላል” ብለዋል፡፡ ወረርሽኙ የሚያደርሰው አደጋም “ከፍተኛ ሊሆን ይችላል” የሚል ስጋት በዓለም ጤና ድርጅት እንዳለም አክለዋል፡፡

በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 38 መድረሱን የጤና ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡ ባለፈው 24 ሰዓት ውስጥ በተደረገ 89 የላብራቶሪ ምርመራ ብቻ ተጨማሪ ሶስት ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው መረጋገጡን ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡ (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)