የመጪው ምርጫ ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ እንዲሆን ኦፌኮ እና ኦነግ ጠየቁ

በሐይማኖት አሸናፊ

የመጪው ሀገር አቀፍ ምርጫ ቀጣይ ዕጣ ፈንታዎችን የሚወስኑ አካላትም ሆኑ መንግስት ምንም አይነት ውሳኔ ከማስተላለፋቸው በፊት ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ማሳተፍ እንደሚገባቸው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) እና የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አሳሰቡ፡፡ ያለምንም ምክክር በመንግስት አካል ብቻ በሚደረግ ውሳኔ ምርጫውን ለማራዘምም ሆነ ቀጣይ የአገሪቱን እጣ ፈንታ ለመወሰን መሞከር የባሰ አገራዊ ቀውስ ሊያስከትል ይችላል ሲሉም ፓርቲዎቹ አስጠንቅቀዋል፡፡

ሁለቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይህን ያሉት ትላንት ምሽት መጋቢት 24 በጋራ ባወጡት መግለጫ ነው፡፡ “የመንግስት ስልጣን በአንድ ወገን እጅ ብቻ እንዲቆይ ማድረግ ኢ-ሕገመንግስታዊ እና ኢ-ዴሞክራሲያዊ ነው፤ ብሔራዊ ቀውስ ውስጥ ሊከተን ይችላል ብለን እንሰጋለን” ብለዋል ፓርቲዎቹ፡፡ “በዚህ አይነት መንገድ ስልጣን ላይ የሚቆይ መንግስት ቀጣዩን ምርጫ በፈለገው መንገድ መዘወር ይችላል” ሲሉም ፓርቲ ፓርቲዎቹ ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

ኦነግ እና ኦፌኮ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መጪውን ምርጫ በተመለከተ ከፓርቲዎች ጋር ተጨማሪ ምክክር ሳያደርግ ውሳኔ ማሳለፉን ተችተዋል፡፡ ቦርዱ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በወርሃ ነሐሴ ይካሄዳል ተብሎ የነበረው አገር አቀፍ ምርጫ ላይ የሚኖረውን ጫና አስመልክቶ አንድ ጉባኤ ማዘጋጀቱን የፖለቲካ ፓርቲዎቹ መግለጫ አስታውሷል፡፡ የምርጫ አስፈጻሚ መስሪያ ቤቱ ውሳኔ ላይ ከመድረሱ በፊት ሌላ አንድ ጉባኤ እንደሚያዘጋጅ ቃል ገብቶ እንደነበርም የጠቀሰው መግለጫው “በውስጥ መስመር እንኳን ስለውሳኔው ሳይገለፅ ቦርዱ መግለጫ ማውጣቱ ተገቢ አልነበረም” ሲሉ ፓርዎቹ ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡

“ህገ መንግስቱ የትኛውንም የመንግስት አካል የስልጣን ዘመኑ ካለቀ በኋላ ምርጫን እንዲያራዝም አይፈቅድለትም”

ምርጫ ቦርድ ባለፈው ማክሰኞ፤ መጋቢት 22 ቀን ባወጣው መግለጫ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት አስቀድሞ ያወጣውን የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ እንዲሰረዝ መወሰኑ ይታወሳል፡፡ ቦርዱ ከውሳኔው የደረሰው ወረርሽኙ በዜጎች እንቅስቃሴ ላይ የሚያመጣው ጫና የቅድመ ምርጫ ሂደቶቹን ያስተጓጉላል በሚል ነው፡፡ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር በመንግስት የሚወሰዱ እርምጃዎች በመጪዎቹ ወራት ሊቀጥሉ መቻላቸውን ታሳቢ ያደረገው ቦርዱ ይህ ሁኔታም ምርጫውን በተያዘለት ህገ መንግስታዊ የጊዜ ገደብ ለማከናወን እንደማያስችለው ገልጾ ነበር፡፡

ሁለቱ ፓርቲዎች ያወጡት የጋራ መግለጫ ይህንን ህገ መንግስታዊ ገደብ አንስቷል፡፡ የኢትዮጵያ ህገ መንግስት “የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስራ ዘመኑ ከማብቃቱ ከአንድ ወር በፊት አዲስ ምርጫ ተካሂዶ ይጠናቀቃል” በማለት መደንገጉን የጠቀሰው መግለጫው ህገ መንግስቱ “የትኛውንም የመንግስት አካል የስልጣን ዘመኑ ካለቀ በኋላ ምርጫን እንዲያራዝም አይፈቅድለትም” ሲል ሲል አጽንኦት ሰጥቷል፡፡ የኢትዮጵያ ህገ መንግስት ለምክር ቤቱ “በወረርሽኝ በሽታም ሆነ በሌላ በማንኛውም ሁኔታ ምርጫን ማራዘም ወይም ማቆየት የሚችልበትን ስልጣን አልሰጠውም” ሲልም አክሏል፡፡

በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ላይ በጋራ ሁሉም ወገን የራሱን ድርሻ እንዲወጣ የጠቁት ፓርቲዎቹ በዚህ ወረርሽን ሰበብ ግን እየጠበበ የመጣውን የተፎካካሪ ፓርቲዎችን እንቅስቃሴ የበለጠ ለመገደብ አላስፈላጊ ህጎችን ከማውጣት መንግስት ይቆጠብም ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ወረርሽኙን የሚመለከቱ መመሪያዎች እና መልዕክቶችም “በዋናነት ለሕዝብ ጤና ጥበቃ ባለሙያዎች መተው አለባቸው” ሲሉም ፓርቲዎቹ በመግልጫቸው አሳስበዋል፡፡ (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)