በአዲስ አበባ ኢትዮጵያ ሆቴል አካባቢ ጥብቅ አሰሳ እና ፍተሻ ሲደረግ ዋለ

ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ ኢትዮጵያ ሆቴል አካባቢ ጥብቅ አሰሳ እና ፍተሻ ሲደረግ ውሏል። አሰሳው ከተለመደው በተለየ መልኩ በርካታ የጸጥታ ኃይሎችን ያሳተፈ እንደነበር በስፍራው ተገኝቶ የነበረው የ”ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ ተመልክቷል። 

ከቀኑ ስምንት ሰዓት ገደማ የተጀመረው የጸጥታ ኃይሎች አሰሳ እና ፍተሻ እስከ ቀኑ አስራ አንድ ሰዓት ገደማ ድረስ ዘልቋል። በእነዚህ ሰዓታት ከኢትዮጵያ ሆቴል የቀድሞው የጉምሩክ መስሪያ ቤት እስከነበረበት ድረስ የነበረው መንገድ ተዘግቶ ፍተሻ ሲደረግ ታይቷል። ከብሔራዊ ትያትር ፊት ለፊት የሚገኘው የመኪና ማቆሚያ ስፍራም በጸጥታ ኃይሎቹ ቁጥጥር ስር ውሎ ነበር። 

የኢትዮጵያ ሆቴልን በሚጎራበተው፤ እንደ ሺህ ሰለሞን ሱፐር ማርኬት እና ላይን ባርን የመሳሰሉ አገልግሎት ሰጪዎችን በያዘው ህንጻ የነበሩ ተገልጋዮች ለሰዓታት ባሉበት እንዲቆዩ ተገድደው ውለዋል። በህንጻው የሚሰሩ ሰራተኞችም ወደ ስራቸው ለመመለስ በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡም በጸጥታ ኃይሎቹ ሲከለከሉ ታይቷል። 

ጉዳዩ መቋጫ እስኪያገኝ ድረስ ሰራተኞቹ ብሔራዊ ትያትር በሚገኝበት ስፍራ ለአራት ሰዓታት ያህል መጠበቃቸውን ለ”ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። እንደ ሰራተኞቹ ሁሉ በርካቶች ከመንገድ ባሻገር ሆነው በአካባቢው ሲከናወን የቆየውን ጉዳይ ያለመሰልቸት ሲከታተሉ ተስተውለዋል። 

ደረታቸውን በጥይት መከላከያ የሸፈኑ እና በተለምዶ በከፍተኛ ባለስልጣናት እጀባ ወቅት አገልግሎት ላይ ሲውል የሚታየውን ጠብመንጃ ይዘው በተጠንቀቅ አካባቢውን ሲቆጣጠሩ የነበሩት ሲቪል ለባሽ የጸጥታ ኃይሎች ሁኔታ በብዙዎች ዘንድ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። “ሴኪዩሪቲ” የሚል የእንግሊዘኛ ጽሁፍ በጎናቸው የተጻፈባቸው ተሽከርካሪዎች በአካባቢው በርከት ብለው መታየታቸውም ለጉዳዩ አትኩሮት እንዲሰጥ ሌላ ምክንያት ሆኗል። 

የመከላከያ ሰራዊት እና የፖሊስ የደንብ ልብስ የለበሱ አባላት ጭምር ተሰማርተው የዋሉበትን የዛሬውን አሰሳ እና ፍተሻ፤ በአካባቢው ካለው የውጭ ሀገር ገንዘብ የጥቁር ገበያ ጋር ያያዙት በርካቶች ነበሩ። በስፍራው የነበሩ የ”ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የጸጥታ ምንጭም የዚህን መላምት እውነትነት አረጋግጠዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)