ኢትዮጵያ ከፓሪስ ክለብ አበዳሪዎች የዕዳ ክፍያ ፋታ አገኘች

ኢትዮጵያ ከፓሪስ ክለብ አባል አገራት ለተበደረችው ዕዳ የስምንት ወራት የክፍያ ፋታ አገኘች። የፓሪስ ክለብ አበዳሪ አገራት ተወካዮች ኢትዮጵያ ከሚያዝያ 23፤ 2012 እስከ ታህሳስ 2013 ዓ.ም. ድረስ ባለው ጊዜ ፋታውን እንድታገኝ መስማማታቸውን ይፋ አድርገዋል።

ለኢትዮጵያ ገንዘብ አበድረው ለስምንት ወራት የክፍያ ፋታ ለመስጠት የተስማሙት የፓሪስ ክለብ አገራት ፈረንሳይ፣ ጣልያን፣ ጃፓን፣ ኮሪያ እና ሩሲያ ናቸው። የኢትዮጵያ መንግስት በስምንቱ ወራት ለዕዳ መክፈል የነበረበትን ገንዘብ የኮሮና ወረርሽኝ የሚያሳድረውን የጤና፣ የኤኮኖሚ እና ማህበራዊ ጫና ለመቋቋም እንደሚያውል መስማማቱን ፓሪስ ክለብ ከትናንት በስቲያ ማክሰኞ ሰኔ 2፤ 2012 ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ኢትዮጵያ ወለድን ሳይጨምር እስከ ታህሳስ 2011 ዓ.ም. ብቻ ከፓሪስ ክለብ አባል አገራት የተበደረችው 696 ሚሊዮን ዶላር ዕዳ አለባት። ኢትዮጵያ ከሌሎች አበዳሪዎቿም ተመሳሳይ የዕዳ ክፍያ ፋታ ትፈልጋለች። የፓሪስ ክለብ አበዳሪ አገራት እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ ለቻድ፣ ለኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ እና ለፓኪስታን የኮሮና ወረርሽኝ ባሳደረው ቀውስ ሳቢያ ለተወሰነ ጊዜ የዕዳ ክፍያ ፋታ ሰጥተዋል።

የቡድን 20 አባል አገራት እና ፓሪስ ክለብ፤ በኮሮና ዓለም አቀፍ ቀውስ ምክንያት 77 ድሃ አገራት የሚከፍሉትን ብድር ለተወሰነ ጊዜ ለማቆም ባለፈው ሚያዝያ ወር ተስማምተዋል። በአጠቃላይ 30 አገሮች ከፓሪስ ክለብ ውሳኔ ተጠቃሚ ለመሆን ያመለከቱ ሲሆን 12 አገሮች ፋታ ተሰጥቷቸዋል።

የቡድን 20 አባል አገራት በደረሱበት ስምምነት መሰረት ተበዳሪ አገራት የኮሮና የዕዳ ክፍያ ፋታ መርሐ-ግብር ተጠቃሚ ለመሆን በተናጠል ለአበዳሪዎቻቸው ማመልከቻ ማቅረብ አለባቸው። ፓሪስ ክለብ አበዳሪ አገራት በ1964 ዓ.ም. ያቋቋሙት ኢ-መደበኛ ቡድን ሲሆን፤ ተበዳሪዎች ለሚገጥማቸው የዕዳ አከፋፈል እክል፤ ስርዓት ያለው ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት ያለመ ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)