ግብጽ የህዳሴ ግድብን በተመለከተ እየተካሄደ በሚገኘው ውይይት ላይ ከዚህ ቀደም አሜሪካ ያዘጋጀችው የስምምነት ረቂቅ የድርድሩ መሠረት እንዲሆን ግፊት እያደረገች ነው ተባለ። የሱዳን መስኖ እና ውሃ ሃብት ሚኒስቴር ትላንት ረቡዕ ሰኔ 3፤ 2012 ከተካሄደው ውይይት በኋላ ባወጣው መግለጫ ግብጽ ይህን አቋሟን በውይይቱ ላይ መግለጿን አስታውቋል።
ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ በአባይ ጉዳይ ለገቡበት የዓመታት ውዝግብ መቋጫ ያበጃል በሚል አሜሪካ ባለፈው የካቲት ወር ያዘጋጀችው የስምምነት ረቂቅ በኢትዮጵያ እና በሱዳን አልተፈረመም። በየካቲት ወር በዋሽንግተን በተካሄደው እና ኢትዮጵያ ባልተገኘችበት ስብሰባ ግብጽ ብቻዋን ሰነዱን ፈርማለች።
ይህ የስምምነት ረቂቅ የህዳሴ ግድብን ውሃ አሞላል እና የወደፊት የስራ ክንውን ጭምር አጠቃልሎ የያዘ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። የስምምነት ረቂቁ በአሜሪካ ትሬዠሪ መስሪያ ቤት መዘጋጀቱን ጭምር ያልተቀበለችው ኢትዮጵያ በትላትናው ውይይት ኢትዮጵያ 13 አንቀጾች ያሉት የውሃ አሞላል እና አመታዊ አስተዳደር ዕቅድ አቅርባለች።
ኢትዮጵያ እቅዱን ማቅረቧን የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ስለሺ በቀለ በይፋዊ የትዊተር ገጻቸው አረጋግጠዋል። የሱዳን መስኖ እና ውሃ ሃብት ሚኒስቴር ትላንት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ ደግሞ “የኢትዮጵያ ልዑካን ለስብሰባዎቹ አጠቃላይ ምክረ ሃሳብ ለማቅረብ ቃል ገብተዋል” ብሏል።
ዶ/ር ስለሺ በትላንትናው ስብሰባ አብዛኞቹ የውይይቱ አካሄድ ጉዳዮች መጠናቀቃቸውን ቢገልጹም የግብጽ የመስኖ እና ውሃ ሃብት ሚኒስቴር ግን ውይይቱ በጊዜ ሰሌዳ፣ የታዛቢዎች ሚና እና ቁጥር ላይ አተኩሯል ሲል በትላንት መግለጫው ወቅሷል። የሚኒስቴሩ መግለጫ ውይይቱ “አንዳች አመርቂ ውጤት ላይ አልደረሰም” ብሏል።
ግብጽ ውይይቱ እስከ ቅዳሜ ድረስ ተጠናቅቆ ሙሉ ስምምነት እንዲፈረም የምትሻ ሲሆን ኢትዮጵያ እና ሱዳን ግን ቀነ ገደብ አላስቀመጡም። አሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት እና ደቡብ አፍሪካ የሚታዘቡት ውይይት ዛሬ ይቀጥላል ተብሏል። ግብጽ ሶስቱ ታዛቢዎች የውይይቱ “አመቻች” ሊሆኑ እንደሚገባ በስብሰባው መጀመሪያ ላይ አቋሟን አንጸባርቃ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)