የወላይታ ተወካዮች በደቡብ ክልል ምክር ቤት ስብሰባ ላለመሳተፍ አድማ መቱ

በተስፋለም ወልደየስ

በደቡብ ክልል ምክር ቤት የወላይታ ዞን ተወካዮች በመጪው ሐሙስ እና አርብ የተጠራውን የክልሉን አስቸኳይ ምክር ቤት ስብሰባ አንሳተፍም አሉ። የወላይታ ተወካዮች ስብሰባውን ላለመሳተፍ የወሰኑት የዞኑ ህዝብ ለምክር ቤቱ ያቀረበው በክልልነት የመደራጀት ጥያቄ “ተደማጭነት አላገኘም” በሚል ነው። 

የወላይታ ዞን በራሱ ምክር ቤት አማካኝነት ክልል ሆኖ ለመደራጀት ውሳኔ ያሳለፈው በታህሳስ 2011 ነበር። ዞኑ ይህንኑ ጥያቄውን በዚያው ወር ለደቡብ ክልል ምክር ቤት በጽሁፍ ያቀረበ ቢሆንም ጉዳዩ በክልሉ ምክር ቤት ደረጃ ሳይታይ ቀርቷል። የደቡብ ክልል ምክር ቤት ጉዳዩን ለመመልከት “በተደጋጋሚ ዳተኝነት በማሳየቱ እና ለህዝብ ጥያቄ ምላሽ በመንፈጉ” በምክር ቤቱ ዞኑን የወከሉ አባላት መጪውን አስቸኳይ ስብሰባ ላለመሳተፍ መወሰናቸውን የወላይታ ዞን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ አበበች እራሾ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር”ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ሕገ መንግስት መሰረት የወላይታ ዞን ብሔር ምክር ቤት ክልል የመመስረት ጥያቄውን ከወሰነበት ጀምሮ ባለው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የክልሉ ምክር ቤት ምላሽ መስጠት ይገባው እንደነበር የሚጠቅሱት አፈ ጉባኤዋ ሆኖም የደቡብ ክልል ምክር ቤት “በስልጣኑ ስር የወደቀውን ህዝበ ውሳኔ የማካሄድ ስራዎች” ባለመስራቱ ሂደቱ መስተጓጎሉን ጠቁመዋል። በክልሉ ምክር ቤት ያሉ የወላይታ ተወካዮች ምክር ቤቱ መደበኛ ጉባኤውን ባካሄደበት ባለፈው የካቲት ወር ጉዳዩ “በአጀንዳነት እንዲያዝ፤ ህዝበ ውሳኔም እንዲፈጸም” ጥያቄዎች ማቅረባቸውን አስታውሰዋል።   

“አባላቱ ተሰሚነት አላገኙም። የወላይታ ዞን ምክር ቤትም እንደ ብሔር ምክር ቤት ያቀረበው የጽሁፍ ጥያቄም ምላሽ አላገኘም። ስለዚህ በሚቀጥለው ሰኔ 11 በሚካሄደው ጉባኤ አባላቱ ‘ምንም ተሰሚነት ስለሌለን መገኘት አንችልም’ በሚል petition [ፊርማ] ተፈራርመው ለክልሉ ምክር ቤት፣ ርዕሰ መስተዳድር፣ ብሔረሰቦች ምክር ቤት እና ለደቡብ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ዛሬ አስገብተዋል” ሲሉ አፈ ጉባኤዋ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። 

ፎቶዎች፦ የወላይታ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ

የደቡብ ክልል ምክር ቤት 348 አባላት ያሉት ሲሆኑ ከእነዚህ ውስጥ ሰላሳ ዘጠኙ የወላይታ ዞንን ወክለው ምክር ቤቱን የተቀላቀሉ ናቸው። በመጪው ሐሙስ የሚካሄደውን የምክር ቤቱን ስብሰባ ላለመሳተፍ በፊርማቸው ያረጋገጡ የዞኑ የምክር ቤት ተወካዮች 38 መሆናቸውን ወይዘሮ አበበች ተናግረዋል። ቀሪው የዞኑ የምክር ቤት አባል በህይወት እንደሌሉና በምትካቸው ሌላ ግለሰብ አለመመረጡንም ጠቁመዋል። 

የዞኑ ተመራጮች ዛሬ ያሳለፉት ውሳኔ ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ከተካሄደው እና የደቡብ ክልል አዲስ አወቃቀር ለመወሰን ከተካሄደው ስብሰባ ጋር የተያያዘ እንደሁ የተጠየቁት አፈጉባኤዋ የአባላቱ ውሳኔ “ከስብሰባው ጋር አይገናኝም” ብለዋል። በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በተደረገው ስብሰባ፤ በህዝበ ውሳኔ ክልል መሆኑን ያረጋገጠውን የሲዳማ ዞንን ጨምሮ የደቡብ ክልል በአራት ክልሎች እንዲከፈል የቀረበ ምክረ ሃሳብ ውይይት ተደርጎበት ነበር። ምክረ ሃሳቡ አብላጫ ድጋፍ አግኝቶ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲመራ ከስምምነት ላይ ቢደረስም፤ የወላይታ ዞን ጉዳይ ተጨማሪ ውይይት እንዲደረግበት ውሳኔ መተላለፉን በስብሰባው የተሳተፉ ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” መግለጻቸው የሚታወስ ነው። 

በአዲስ አበባው ስብሰባ ላይ የወላይታ ዞን ራሱን ችሎ በክልል እንዲደራጅ ከተሳታፊዎች ተደጋጋሚ ሀሳቦች ቀርበው ነበር ተብሏል። የወላይታ ዞን አስተዳደር በስብሰባው ማግስት ባወጣው መግለጫ “የቀረበው ምክረ ሀሳብ ከዚህ ቀደም ከቀረበው ጋር ተመሳሳይ የሆነ በመሆኑ፤ መርህን ያልጠበቀ፣ ወጥነት የጎደለው እና የሕዝባችንን ነፃነትም ሆነ የሕዝቦችን አንድነት በሙላት ያልመለሰ እና ከዚህ ቀደም ከሕዝባችን ጋር ከተማከርነው የተለየ በመሆኑ ውጤቱን አልተቀበልንም” ሲል አስታውቋል። በስብሰባው ላይ የተሳተፉ የወላይታ ዞን አመራሮች “የወላይታ ህዝብ ጥያቄ ‘በልዩነት ይታይ’ የሚል ሀሳብ በግልጽ ማንሳታቸውን መግለጫ ጠቅሷል። 

“የቀረበው ምክረ ሀሳብ ከዚህ ቀደም ከቀረበው ጋር ተመሳሳይ የሆነ በመሆኑ፤ መርህን ያልጠበቀ፣ ወጥነት የጎደለው እና የሕዝባችንን ነፃነትም ሆነ የሕዝቦችን አንድነት በሙላት ያልመለሰ እና ከዚህ ቀደም ከሕዝባችን ጋር ከተማከርነው የተለየ በመሆኑ ውጤቱን አልተቀበልንም”

ስብሰባውን የመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ የዞኑ አመራሮች ያቀረቡትን “ሀሳብ በመቀበል” በቅርብ ቀናት ውስጥ የውይይት መድረክ ለማዘጋጀት ቃል መግባታቸውን መግለጫው አትቷል። ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ውይይት ጎን ለጎን የፌደሬሽን ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላትም በጉዳዩ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ከህዝብ ጋር እንደሚወያዩ የዞኑ አስተዳደር መግለጫ ጠቁሟል።  

የወላይታ ዞን “በክልል ለመደራጀት ላቀረብኩት ጥያቄ የደቡብ ክልል ምክር ቤት ተገቢውን ምላሽ አልሰጠኝም” በሚል ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ከሰባት ወር በፊት ይግባኝ አስገብቷል። ይግባኙ “በፌዴሬሽን ምክር ቤት አጣሪ ጉባኤ እየታየ ነው” ሲሉ ወይዘሮ አበበች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። የወላይታ ዞን ሰባት አባላት ያሉበት ኮሚቴ አቋቁሞ ጉዳዩን እየተከታተለ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ኮሚቴው የዞኑ ምክር ቤት አፈ ጉባኤን፣ የዞኑን አቃቤ ህግ እንዲሁም ከወላይታ አገር ሽማግሌዎች ምክር ቤት እና “ዬላጋ” ከተሰኘው የወላይታ ወጣቶች ስብስብ ተወካዮችን ያካተተ መሆኑንም አብራርተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)