በኢትዮጵያ የኮሮና የመጀመሪያዋ ሰለባ የስንብት ጉዞ

በሐይማኖት አሸናፊ

ከመገናኛ ወደ ኮተቤ በሚወስደው መንገድ የሚጓጉዙ መንገደኞች ገብርኤል ቤተክርስቲያን መዳረሻ አካባቢ ሲደርሱ ትኩረታቸውን ቆንጥጦ የሚይዝ አንድ መደብር አለ፡፡ መደብሩ ሸቀጣ ሸቀጦችን የያዘ አይደለም፡፡ አሊያም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰቱ ከተነገረ በኋላ ተፈላጊነታቸው እና ዋጋቸው ያሻቀበው ሳንታይዘር እና የፊት መሸፈኛም አይሸጡብትም፡፡ ይልቁንም በመደብሩ በብዛት ተደርድረው የሚታዩት የሬሳ ሳጥኖች ነው፡፡

በአካባቢው ባለው የትራንስፖርት እጥረት ምክንያት አገልግሎት እየሰጡ በሚገኙ፤ በተለምዶ “ቅጥቅጥ” እየተባሉ በሚጠሩ መለስተኛ አውቶብሶች የሚጓዙ መንገደኞች ተፋፍገው መጫናቸው ምቾት ሳይነሳቸው የሬሳ ሳጥን መሸጫ መደብሩን መመልከታቸው ግን አስጨንቋቸዋል፡፡ አፍ ለአፍ ገጥመው የሆድ የሆዳቸውን የሚጫወቱ ተሳፋሪዎች በሚታዩበት መለስተኛ አውቶብስ ከኮሮና ቫይረስ ጋር የተያያዘ ጥያቄ ሲነሳም ድንጋጤ ሲፈጥር ታይቷል፡፡

ከአውቶብሱ መንገደኞች የተወሰኑቱ በአቅራቢያቸው ስላለው የኮሮና ቫይረስ ታማሚዎች ህከምና መስጫ ሆስፒታል ያውቃሉ፡፡ ሆኖም አድራሻውን ሲጠየቁ ቀጥተኛ መልስ ከመስጠት ይልቅ “በሰላም ነው፣ የታመመ ለመጠየቅ ነው ወይስ ችግር አለ?›› ሲሉ ስጋት ባዘለ ድምጽ ይጠይቃሉ፡፡

This image has an empty alt attribute; its file name is Eka-Kotebe-Hospital-1024x576.jpgኤካ ኮተቤ አጠቃላይ ሆስፒታል በሚል ስያሜ በዚህ አመት መጀመሪያ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ይህን የህክምና ተቋም በስጋት ከሚመለከቱት ውስጥ መኖሪያዋ ከሆስፒታሉ ጀርባ የሆነች ወጣት ትገኝበታለች፡፡ “ብችል ባቋራጭ እንጂ በሆስፒታሉ ዙሪያ መሄድ አልፈልግም፡፡ ምንም እሆናለሁ ብዬ ሳይሆን እንደው የሆነ የሚፈጥርብኝ ፍርሃት እና የሽብር ስሜት አለ” ትላለች ወጣቷ፡፡ “እዚህ ሰፈር የምንኖር ያው ፍርሃት ይሰማናል፤ ስለዚህ በጣም እንጠነቀቃለን፡፡ ቀሪውን ፈጣሪ ያውቃል” ስትል በስጋት የጠየመ ስሜቷን ታጋራለች፡፡ 

ወጣቷ ከሁለት ሰዓት በፊት በጤና ሚኒስቴሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ይፋ የተደረገውን የኮሮና ቫይረስ ታማሚ ህልፈተ ህይወትን የሰማች ባትመስልም ዛሬም ለጥንቃቄ በሚል ሆስፒታሉ ጋር ከመድረሷ በፊት መንገድ ማሳበሯን አልተወችም፡፡ በእርግጥ በሆስፒታሉ ደጃፍም ብታልፍ በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የመጀመሪያው ሞት የተመዘገበበት ሆስፒታል ድባብን አትመለከትም፡፡ 

ከቀኑ አስራ አንድ ሰዓት ገደማ የሆስፒታሉ ዙሪያ ገባ በጸጥታ ተውጧል፡፡ በሆስፒታሉ ቅጽር ግቢ ውስጥ ከሚታዩ ሁለት አምቡላንሶች ፈቀቅ ብሎ የቆመው የፌደራል ፖሊስ ፒክ አፕ መኪና አጠገቡ የሚታዩ የፖሊስ አባላት ሁኔታው ከተለመደው ውጭ ለመሆኑ ጥቆማ ይሰጣሉ፡፡ የፖሊስ አባላቱ በግቢው ውስጥ እንዳሉት የህክምና ባለሙያዎች እና ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች ሁሉ የፊት መሽፈኛ እና የእጅ ጓንት አድርገዋል፡፡ 

This image has an empty alt attribute; its file name is Hospital-staff-at-Eka-Kotebe-copy-1024x576.jpgከጥቂት ቆይታዎች በኋላ በሁለት ፒካ አፕ ተሽከርካሪዎች ተጭነው ከሆስፒታሉ ደጃፍ የደረሱት ሌሎች የፌደራል ፖሊስ አባላትም ተመሳሳይ የፊት እና የእጅ መከለያዎችን አጥልቀው ነበር፡፡ እነዚህኞቹ ፖሊሶች እንደባልደረቦቻቸው ታማሚዎችን የሚያመጡ አምቡላንሶችን እንዲያጅቡ የተመደቡ አልነበሩም፡፡ ይልቁንም የኮሮና ቫይረስ ህይወታቸውን የነጠቃቸውን የመጀመሪያዋን ኢትዮጵያዊት ስርአተ ቀብር በአጀባ ለማስፈጸም ወደ አካባቢው በአስቸኳይ እንዲመጡ የተጠሩ ናቸው፡፡  

የስልሳ አመቷ ኢትዮጵያዊት የኮሮና ቫይረስ በፅኑ ከጎዳቸው አውሮፓ አገራት አንዷ ከሆነቸው ፈረንሳይ ወደ አገር ቤት የተመለሱት መጋቢት 6፤ 2012 ነበር፡፡ ወደ መኖሪያ ከተማቸው አዲስ አበባ ከተመለሱ ከ13 ቀናት በኋላ የበሽታው ምልከቶች ስለታየባቸው ወደ ለይቶ ማከሚያ እንዲገቡ መደረጋቸውን የጤና ሚኒስቴሯ ዶ/ር ሊያ ትላንት አስታውቀዋል፡፡ ኢትዮጵያዊቷ መጋቢት 22፤ 2012 ቫይረሱ እንዳለባቸው በምርምራ መረጋገጡን የገለጹት ዶ/ር ሊያ ከዚያ ቀን ወዲህ ባሉ ስድስት ተከታታይ ቀናት በጽኑ ህሙማን መርጃ ውስጥ መቆየታቸውን አስረድተዋል፡፡

እሁድ መጋቢት 27 ህይወታቸው እንዳለፈው የተገለጸው የእኚህ ኢትዮጵያዊት ቀብር “የዕለቱ የዕለት ይፈጸማል” ቢባልም የተሟላ እና የተረጋገጠ መረጃ የሚሰጥ አካል በመጥፋቱ የሆስፒታሉ አስተዳዳሪዎች እና የፖሊስ አባላት ለሰዓታት እንዲጠብቁ ተገድደዋል፡፡ የሆስፒታሉ አስተዳዳሪዎች ከቀብር አስፈጻሚ ግብረ ኃይሎች እና ከህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የፈጣን ምላሽ ቡድን አባላት ጋር ተደጋጋሚ የስልክ ልውውጥ ቢያደርጉም ለጉዳዩ ወዲያውኑ ዕልባት መስጠት አልተቻለም፡፡ 

This image has an empty alt attribute; its file name is Ambulances-rushing-to-Hospital-1-1024x576.jpgበዚህ መሃል የኮሮና ቫይረስ እንዳለባቸው የተረጋገጡ አምስት ሰዎችን የያዙ አምቡላንሶች ወደ ሆስፒታሉ ተከታትለው ደረሱ፡፡ ሰዎቹ ከእሁድ በፊት በነበረው 24 ሰዓት ውስጥ ምርምራ ከተደረገላቸው 59 ግለሰቦች ውስጥ በኮሮና ቫይረስ ተጠቅተው የተገኙ ናቸው፡፡ ከአምስቱ ውስጥ አንደኛው ኤርትራዊ ሲሆን ሌላኛው ሊቢያዊ መሆኑን የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ገልጸዋል፡፡ ከታማሚዎቹ ውስጥ አራቱ የውጭ ሀገር ጉዞ ታሪክ ያላቸው ሲሆኑ አንደኛው በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት ያለው እንደሆነ ሚኒስትሯ በእሁድ ጠዋት መግለጫቸው አብራርተው ነበር፡፡

አነዚህን አዳዲስ ህሙማን ይዘው የመጡት አምቡላንሶች የአደጋ ጊዜ ድምጻቸውን ሳያሰሙ፤ ከአናታቸው ያለውን የሚብለጨልጭ መብራት ብቻ በመጠቀም፤ ወደ ኤካ ኮተቤ ሆስፒታል የሚወስደውን የተቆፋፈረ መንገድ አቧራ እያቦነኑ በፍጥነት ወደ ሆስፒታሉ ሲገቡ ታይተዋል፡፡ ወደ ሰፊው ግቢ ዘልቀው ከገቡ በኋላም አስፈላጊው የጥንቃቄ እርምጃ እየተደረገ ታማሚዎቹ ራሳቸውን ችለው ወደ ዋናው የሆስፒታሉ ህንፃ እንዲገቡ አድርገዋቸዋል፡፡ ‹‹እስካሁን ስትሬቸር ወይም ዊልቸር ላይ አድርገን ያስገባናቸው ከሁለት አይበልጡም›› ሲሉ አንድ የሆስፒታሉ ሰራተኛ ለኢትዮጵያ ኢንሳይደር ተናግረዋል፡፡ 

ማንም ወደ ግቢው የሚገባ ሰው ጫማውን በኬሚካል ማፅዳት እና አፉን በማስክ እንዲሸፍን በሃኪሞቹ ይደረጋል፡፡ ምንም ድካም የማይታይባቸው የሆስፒታሉ ሃኪሞች ወደ ቤተሰቦቻቸው አዘውትረው ስለማይሄዱ ቤተሰቦቻቸው እነርሱኑ ለመመልከት ከሆስፒታሉ ፊት ለፊት ባለው ሜዳ ላይ ሆነው ሲጠባበቁ ተስተውለዋል፡፡ ሃኪሞቹ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለአፍታ ተጨዋውተው የመጣላቸውን ስንቅ ተቀብለው መልሰው ወደ ትልቁ ህንፃ ይገባሉ፡፡

This image has an empty alt attribute; its file name is Outside-Eka-Kotebe-Hospital-1024x576.jpgበዚህ ሁሉ መካከል የሚጠበቁት የቀብር ፈፃሚዎች ሳይመጡ ሁለት ሰዓታት አልፎ ለአይን ያዝ ማድረግ ጀምሯል፡፡ በሆስፒታሉ አስተዳዳሪ እና ምላሽ በሚሰጡት ሰዎች መካከል የሚደረገው የስልክ ልውውጥ ያለመግባባት ይታይበታል፡፡ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ተኩል ገደማ ለሰዓታት ሲጠበቅ የቆየው የቀብር ፈጻሚዎች ይሁንታ መገኘቱን ተከትሎ የሟችን አስከሬን ወደ ቀጨኔ የመቃብር ስፍራ ለመውሰድ ዝግጀት ተጀመረ፡፡ 

አስከሬኑን የሚያጓጉዘው አምቡላንስ ከራሱ ላይ ያለውን ቀይ መብራት እያበራ ወደ ሆስፒታሉ ግቢ ከገባ በኋላ በህንጻው በስተግራ ባለው የህንፃው ክፍል ጀርባውን ሰጥቶ ቆመ፡፡ አምቡላሱን የሚያሸከረክሩት ግለሰብ እና ባልደረባቸው የተሟላ የደህነንት መጠበቂያዎችን እንዲለብሱ ከሆስፒታሉ አስተዳዳሪዎች ባዘዙት መሰረት እርሱኑ ማድረግ ያዙ፡፡ 

በቅድሚያ ፊታቸውን ብቻ አስቀርቶ ከእግር እስከ ጭንቅላታቸው ድረስ የሚጠለቀውን ከፕላስቲክ የተሰራ ሙሉ ልብስ ለበሱ፡፡ ከዛም ከላይ ከሰማያዊ ስስ ፕላስቲክ የተሰራውን ጋዋን፣ የእጅ ጓንት፤ የአፍ መሸፈኛ ማስክ እና ለጫማቸው መሸፈኛ የተዘጋጀውን ሰማያዊ ስስ የፕላስቲክ መሸፈኛ ተራ በተራ አደረጉ፡፡ የሆስፒታሉ ሃኪሞች የአምቡላንሱ ሰራተኞች መሸፈኛዎቹ በአግባቡ መደረጋቸውን በተደጋጋሚ ያረጋግጣሉ፡፡ ከህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የፈጣን ምላሽ ግብረ ኃይል የመጡ ባለሙያዎችም ሁሉም በትክክል መከወኑን እየተመለከቱ ያስፈፅሙ ነበር፡፡ 

በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ህይወታቸውን ያጡትን የ60 ዓመት ኢትዮጵያዊት የያዘው የእንጨት ሳጥን ከአምቡላንሶቹ ባለሙያዎች አቅራቢያ ይታያል፡፡ ሳጥኑ ከላይ በኩል የመስቀል ምልክት ይዞ ስስ ነጠላ ጣል ተደርጎበታል፡፡ አስክሬኑ በከፍተኛ ጥንቃቄ መገነዙን የሚገልጹት ባለሙያዎቹ የሳጥኑ የውጨኛው ክፍልም በተደጋጋሚ በማፅጃ ኬሚካሎች በሚገባ መፀዳቱን ለ”ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል፡፡

ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ለመሙላት ሶስት ደቂቃ ሲቀረው የስልሳ አመቷ ኢትዮጵያዊት አስከሬን ወደ መዳረሻው ቀጨኔ በሚወስደው አምቡላንስ ላይ የጀርባ በር ተከፍቶ ተጫነ፡፡ ይሄ ሁሉ ሲከናወን 43 የኮሮና ቫይረስ እንዳለባቸው የተረጋገጡ ሰዎች የተኙበት ሆስፒታል ግቢ ፀጥ ረጭ እንዳለ ነው፡፡ ከሆስፒታሉ አስተዳደሮች እና ከጥበቃዎች ውጪም ማንም አይታይም፡፡

This image has an empty alt attribute; its file name is Police-escort-ambulances-1024x576.jpgበእንዲህ ያለ የተረጋጋ ሁኔታ አስከሬኑ ጉዞውን ሲጀምር በአንድ ሌላ አምቡላንስ እና ሁለት የፌደራል ፖሊስ አባላት በጫኑ ተሸከርካሪዎች ታጅቦ ነበር፡፡ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባለሙያዎችም በላንድ ክሩዘር ሆነው የቀብር ጉዞውን ተቀላቅላዋል፡፡ የፌደራል ፖሊስ መኪኖች መንገዱ ላይ ውር ውር የሚሉትን ጥቂት መኪኖች መንገድ እያስለቀቁ ቀድማ ፀጥ ረጭ ባለችው አዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ በፍጥነት ይጓዛሉ፡፡

አምቡላንሱ እና አጀቡ ከኮተቤ በመገናኛ አልፎ ወደ ስድስት ኪሎ ሲያቀና አልፎ ሂያጆች በግርታ ሲመለከቱ ታይተዋል፡፡ በሁለት ፒክ አፕ ተሽከርካሪዎቸ የታጨኑት የፌደራል ፖሊስ አባላት አምቡላንሱን አጅበው ቀጨኔ የመቃብር ስፍራ ካደረሱ በኋላ ከቅጥር ግቢው ውጪ ተሰማሩ፡፡

አስክሬኑን የያዘው አምቡላንስ እና የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባለሙያዎችን የያዘው ተሸከርካሪ ወደ መቃብር ስፍራው ዘልቀው በመግባት የምሽት የቀብር ስነ ስርዓቱን ማስፈጸም ቀጠሉ፡፡ በአዲስ አበባ አስተዳደር የዘርፉ ሰራተኞች በመደዳ ተቆፍረው ከተዘጋጁ ጉድጓዶች መካከል በጥግ በኩል ያለው ተመርጦ ከምሽቱ ሶስት በኋላ የቀብር ስነ ስርዓቱ የተፈጸመ ሲሆን በስፍራው ወዳጅም ሆነ ዘመድ እንዲገኝ አልተደረገም፡፡ (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)