ገዢው ፓርቲ በደቡብ ክልል የተነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ ያዘጋጀው የክላስተር አወቃቀር ቀደም ሲል ክልሉ ሲመሰረት “የተሰራውን ስህተት የሚደግም ነው” ሲል ተቃዋሚው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ ተቸ። ገዢው ፓርቲ ከሕግ አግባብ ውጪ የሕዝብን ተቀባይነት ለማግኘት የሚያደርገውን ሩጫ “በአስቸኳይ ያቁም” ሲልም ፓርቲው አሳስቧል።
ኢዜማ ይህን ያለው የደቡብ ክልልን መልሶ ማዋቀር በተመለከተ ዛሬ ማክሰኞ ሰኔ 9፤ 2012 ባወጣው ባለ ሰባት መግለጫ ነው። መንግስት የደቡብ ክልልን ወደ አምስት የሚከፍል ምክረ ሃሳብ ለመተግበር በእንቅስቃሴ ላይ እንደሆነ መረዳቱን የገለጸው ፓርቲው አካሄዱ “ኢትዮጵያ ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ ያላገናዘበ፣ ጭራሹንም የረሳ ነው” ብሏል።
“ከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት እና ጥንቃቄ” ይጠይቃሉ ያላቸውን ወቅታዊ ሁኔታዎች የዘረዘረው ፓርቲው የደቡብ ክልል ራስን በራስ ለማስተዳደር ለቀረቡ ጥያቄዎች “ትክክለኛ እና ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት አሁን ያለንበት ጊዜ አይፈቅድም” ሲል አቋሙን በመግለጫው አንጸባርቋል። በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የሚያዙ እና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በእጅጉ እየጨመረ መምጣቱን የጠቆመው ኢዜማ ወረርሽኙን ለማቆም በተወሰዱ እርምጃዎች ምክንያት ሀገሪቱ ልታካሂደው የነበረውን ሀገራዊ ምርጫ ለመግፋት መገደዷን አስታውሷል።
ፓርቲው “ጫፍ የረገጠ ጽንፈኛ አመለካከት ያላቸው” ሲል በመግለጫው የጠራቸው ኃይሎች “ምርጫው መራዘሙን እንደሽፋን በመጠቀም ብጥብጥ ለማስነሳት ቀጠሮ ይዘዋል” ሲልም ወንጅሏል። ይህም ወቅቱን “ከፍተኛ ጥንቃቄ” የሚያስፈልግበት ያደርገዋል ብሏል። ከዚህ በተጨማሪም ከህዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያ ላይ የሚመጣውን ጫና ለመቋቋም “ከመቼውም ጊዜ በላይ ሀገራዊ አንድነት የሚያስፈልግበት” ወቅት እንደሆነም አመልክቷል::
“ገዢው ፓርቲ ለደቡብ ክልል ያዘጋጀው የክላስተር አወቃቀር አሁን በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግስት ህገ ወጥ የሆነ፣ ደቡብ ክልል ሲዋቀር የተሰራውን ስህተት በመድገም ተመሳሳይ ችግርን በአንድ ዓይነት መፍትሄ ለመቅረፍ ደግሞ የሚሞክር ነው”
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ
በዚህ ወቅት በገዢው ፓርቲ የቀረበው ምክረ ሃሳብ በደቡብ ክልል የቀረቡ የራስን በራስ ማስተዳደር ጥያቄዎች “በፍፁም መመለስ የማይችል፣ ለችግሩ መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ የፖለቲካ ትርፍ ማግኘት ዓላማ ያደረገ ነው” ሲል ኢዜማ አጣጥሎታል። የብልጽግና ፓርቲን እንቅስቃሴ “ትልቁን ደቡብ ክልል ወደ አነስተኛ ክልሎች ለመቀየር የሚደረግ ጥረት” ሲል የጠራው ፓርቲው አካሄዱ “አመጽ እና ብጥብጥ ለማንሳት ለሚሞክሩ ኃይሎች ስንቅ እንደማቀበል የሚቆጠር ነው” ሲል ስጋቱን ገልጿል።
ገዢው ፓርቲ ለደቡብ ክልል ያዘጋጀው የክላስተር አወቃቀር “አሁን በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግስት ህገ ወጥ የሆነ፣ ደቡብ ክልል ሲዋቀር የተሰራውን ስህተት በመድገም ተመሳሳይ ችግርን በአንድ ዓይነት መፍትሄ ለመቅረፍ ደግሞ የሚሞክር ነው” ሲል የኢዜማ መግለጫ ተችቷል። ለፌደሬሽን ምክር ቤት “ክልል እንሁን” የሚል ጥያቄ ያስገቡት በደቡብ ክልል ስር ያሉ ዞኖች “ክልል እንዳይሆኑ ለመከልከል ምንም ሕጋዊም ሆነ የሞራል ምክንያት የለም” የሚለው ኢዜማ፤ ገዢው ፓርቲ እየቀረቡ ያሉትን ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄዎች፤ በካድሬ እና የባለሥልጣናት መዋቅሩ በኩል ለማፈን በ”ሩጫ” ላይ ነው ሲል ከስሷል።
የብልጽግና ፓርቲ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ “የሕዝብን መሰረታዊ ጥያቄ የማይመልስ ነው” የሚል እምነት ያለው ኢዜማ አካሄዱ “ፓርቲው እያሳየ ያለውን የመብት ሰጪ እና ነሺነት ፍላጎትንም የሚያሳይ ነው” ብሏል። “ይህ በየጊዜው ከለውጡ አጠቃላይ መንፈስ እየራቀ የመጣው የገዢው ፓርቲ ፍላጎት በሀገራችን እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት የሚያደናቅፍም ጭምር ነው” ሲል ኢዜማ በተደጋጋሚ ያስተዋለውን ግድፈት በመግልጫው አንስቷል።
“ገዢው ፓርቲ ከህግ አግባብ ውጪ በሆነ የመብት ሰጪ እና ነሺነት የሕዝብን ተቀባይነት ለማግኘት የሚያደርገውን ሩጫ በአስቸኳይ ያቁም” ሲል ኢዜማ አጥብቆ አሳስቧል። “ይህ ሳይሆን ቀርቶ በዚህ ምክንያት በሰው ሕይወት እና ንብረት ላይ ለሚደርስ እያንዳንዱ ጉዳት ቀጥተኛ ተጠያቂ በራሱ ተነሳሽነት ጉዳዩን እየገፋ ያለው ገዢው ፓርቲ እንደሚሆን በግልፅ መታወቅ አለበት” ሲልም አስጠንቅቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)