በሐይማኖት አሸናፊ
ግብጽ የህዳሴ ግድቡ ላይ በሚደረጉ ድርድሮች ወቅት “ ‘የቅኝ ግዛት ስምምነቶች ተፈፃሚ አይሆኑም’ በሚል በኢትዮጵያ ዘንድ የሚነሳው ጥያቄ አግባብ አይደለም፤ ስምምነቶቹ አሁንም ተፈፃሚ ናቸው” ስትል ከትናንት በስቲያ አርብ፤ ሰኔ 12፤2012 በድጋሚ ለጸጥታው ምክር ቤት በላከችው አቤቱታ አመለከተች።
የግብጹ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሽኩሪ በማመመልከቻቸው አባሪ ላይ ኢትዮጵያ በ1894 ዓ.ም ከታላቋ ብሪታኒያ እና ከጣሊያን ጋር የተፈራረመችውን ስምምነት ዋቢ በማድረግ “ውሉ ተፈጻሚ ነው” ሲሉ መከራከሪያ አቅርበዋል፡፡ ሳሜህ “ኢትዮጵያ በቅኝ ተገዝታ አታውቅም። አባይን በተመለከተ የፈረመቻቸው ማንኛውም አይነት ስምምነቶች ነፃ አገር ሆና ስለፈረመቻቸው ገዢ ናቸው” ሲሉም ሞግተዋል።
“ኢትዮጵያ በአባይ ላይ የሚደረግ እና የውሃውን ፍሰት ሊይዝ የሚችል ማንኛውንም አይነት ግንባታ ላለማካሄድም ወይም እንዲካሄድ ላለመፍቀድ፤ በ1894ቱ ስምምነት ላይ ቃል ብትገባም ይህንን መቃወሟን ቀጥላለች” ስትል ግብጽ ኢትዮጵያን ወንጅላለች። ግብጽ በአጼ ምኒልክ በኩል የተፈረመውን ይህንን ስምምነትም አባሪ አድርጋም ለምክር ቤቱ ልካለች።
የስምምነቱ አንቀጽ ሶስት “ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ፣ በጣና ብሎም በሶባት ላይ ምንም አይነት ግንባታ አታከናውንም፤ እንዲከናወንም ፈቃድ አትሰጥም” ይላል። ነገር ግን ከታላቋ ብሪታኒያ ንግስት እና ከሱዳን ጋር ስምምነት በማድረግ ግንባታዎች ሊካሄዱ እንደሚችሉ የ1984ቱ ስምነት ያትታል።
“ኢትዮጵያ የቅኝ ግዛት ስምምነቶችን የምታነሳው ለፖለቲካዊ አላማ ነው” ስትል የወቀሰችው ግብጽ በህዳሴው ግድብ ላይ በሚደረገው ድርድር “ኢትዮጵያ ዋና ኢላማውን ለማሳት፣ እውነታውን ለማጣመም ብሎም ትኩረት ለማጥፋት አስባ የምታነሳው ሃሳብ ነው” ብላለች።
በህዳሴው ግድብ ላይ የሚደረገው ድርድር “ስለ አንድ ፕሮጀክት ብሎም ከአባይ ገባር ወንዞች መካከል አንዱን ብቻ የሚመለከት ነው” ያለችው ግብፅ “የውሃ ክፍፍልን የተመለከቱ ጉዳዮች በዚህ ድርድር ላይ መነሳታቸው ስህተት ነው” ስትልም ለጸጥታው ምክር ቤት አብራርታለች።
ግብጽ ባለፈው ሚያዚያ ወር ለጸጥታው ምክር ቤት አስገብታው በነበረው የመጀመሪያው አቤቱታዋ ላይ “ኢትዮጵያ የታላቁ የህዳሴ ግድብን የውሃ ሙሌት በመጪው ሰኔ 2012 ለመጀመር በመወሰኗ ለቀጠናው ሰላም እና መረጋጋት አደጋ ደቅናለች” ብትልም ከትላንት በስቲያ ባስገባቸው ማመልከቻዋ ግን ስጋት ያለችውን ወደ ዓለማቀፍ ደረጃ ከፍ አድርጋ አቅርባለች። ታላቁ የህዳሴ ግድብ ያለ ስምምነት የሚሞላ ከሆነ ዓለማቀፍ ሰላም እና ደህንንነትን አደጋ ውስጥ ሊጥሉ የሚችሉ አጸፋዊ እርምጃዎች ልትወሰድ እንደምትችልም አስጠንቅቃለች።
ግብጽ ለዚህ ዛቻዋ መሰረት ያደረገችው የተባበበሩት መንግስታትን ቻርተር ነው። “የህዳሴ ግድቡ በአባይ ወንዝ ላይ የሚገነባ ግዙፍ ፕሮጀክት ነው። 100 ሚሊዮን ግብጻዊያንም ህይወታቸው በዚሁ ወንዝ ላይ የሚመሰረት በመሆኑ ያለ ስምምነት ግድቡን መሙላትም ሆነ ወደ ስራ ማስገባት ወሳኝ ብሔራዊ ጥቅማችን ይነካል” ሲሉ የግብጹ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በማመመልከቻቸው ላይ ገልጸዋል። “ማንኛውም የተባበሩት መንግስታት አባል አገር ወሳኝ ብሄራዊ ጥቅሙን የመጠበቅ መብት አለው” ያለችው ግብጽ ስለዚህም “አጸፋውን የመመለስ መብት” እንዳላት ለምክር ቤቱ አስረድታለች።
“የህዳሴ ግድቡ በአባይ ወንዝ ላይ የሚገነባ ግዙፍ ፕሮጀክት ነው። 100 ሚሊዮን ግብጻዊያንም ህይወታቸው በዚሁ ወንዝ ላይ የሚመሰረት በመሆኑ ያለ ስምምነት ግድቡን መሙላትም ሆነ ወደ ስራ ማስገባት ወሳኝ ብሔራዊ ጥቅማችን ይነካል”
የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሽኩሪ
ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ግብጽ በህዳሴው ግድብ የውሃ ሙሌት ላይ ያላትን አቤቱታ በድጋሚ ያስገቡበት ምክንያት “ስምምነት ላይ ሳይደረስ፣ ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትሯ ጭምር፣ በመጪው ሐምሌ ወር የግድቡን የውሃ ሙሌት ለማስጀመር ማሰቧን መግለጿ ነው” ብለዋል። የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ለጸጥታው ምክር ቤት ባስገቡት ደብዳቤ ላይ ካስረገጧቸው እውነታዎች በተቃራኒ፤ “ድርድሮቹ ውጤታማ ያልሆኑት ኢትዮጵያ በምታስቀምጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች እና እንቅፋቶች ነው” ሲሉ ሳሜህ በማመልከቻቸው ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ከምታነሳቸው ክርክሮች መካከል በአባይ ተፋሰስ አገራት በ2002 የተፈረመው አጠቃላይ የማዕቀፍ ስምምነት (ሲ.ኤፍ. ኤ) “በህዳሴው ግድብ ላይ በሚደረጉ ድርድሮች ላይ ተፈፃሚነት ይኖረዋል” የሚለው ነው። ግብጽ ስምምነቱን “ያልፈረምኩት እንዲሁም የማይመለከተኝ ነው” ስትል ለጸጥታው ምክር ቤት በላከችው አቤቱታ አባሪ ላይ ሞግታለች። የአባይ ወንዝ የታችኛው ተፋሰስ አገራት የሆኑት ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳንም ሆኑ ግብጽ የማዕቀፉ ፈራሚ ስላልሆኑ “ስምምነቱ አይገዛቸውም” ስትል ሙግቷ ሌሎች ሀገራትን ባከተተ መልኩ አስፍታ አቅርባለች።
“ግብጽ ራሷን ከአዳዲስ አውነታዎች ጋር ማስታረቅ እና በተፋሰሱ አገራት መካከል የተፈረመውን የስምምነት ማዕቀፍ መፈረም ይገባታል” ስትል ኢትዮጵያ አቋም መያዟንም የሳሜህ አቤቱታ ኮንኖታል። “ኢትዮጵያ በሁለገብነት እና በቀጠናዊ ትብብር አምናለሁ ብትልም የታላቁን የህዳሴ ግድብ ጉዳይ አንዴም ቢሆን በናይል ቤዚን ኢኒሺዬቲቭ ጥላ ስር አቅርባው አታውቅም” ሲሉ ሚኒስትሩ በአቤቱታቸው ከስሰዋል።
ኢትዮጵያ በአሜሪካ የረቀቀውን ስምምነት አልፈርምም ማለቷ “አስገራሚ ነው” ያለችው ግብጽ ለጸጥታው ምክር ቤት የመጨረሻውን የስምምነት ረቂቅ አያይዛ አቅርባለች። ባለፈው የካቲት ወር ኢትዮጵያ ባልተገኘችበት የዋሽንግተን ዲሲ ስብሰባ ሱዳንም ይህንን ስምምነት ከመፈረም ተቆጥባለች። በስምምነቱ ላይ ፊርማዋን ያኖረችው ግብጽ ብቻ ነበረች።
ግብጽ ለጸጥታው ምክር ቤት ሌላም የስምምነት ሰነድ በአባሪነት አያያዛ አቅርባለች። ስምምነቱ የተደረገው በኢትዮጵያ የሽግግር መንግስት ጊዜ በወቅቱ የሀገሪቱ ፕሬዘዳንት በነበሩት በአቶ መለስ ዜናዊ እና በግብጹ አቻቸው ሆስኒ ሙባረክ መካከል ነበር። በሰኔ 24፤ 1985 በካይሮ የተፈረመውን ይህ የማዕቀፍ ስምምነትም ስምንት አንቀጾችን የያዘ ነው።
ግብጽ የጸጥታው ምክር ቤት ጉዳዩን በአስቸኳይ “የአፍሪካ የሰላም እና ደህንነንት ጉዳይ” በሚመለከተው አጀንዳው ስር እንዲመለከተው አሳስባለች። ምክር ቤቱም ሆነ የዓለማቀፉ ማህበረሰብ “ኢትዮጵያ በሃላፊነት ስሜት ሚዛናዊ ስምምነት ላይ እንድትደርስ ያበረታታልኝ” ስትልም ተማጽናለች። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)