የወላይታ ዞን ምክር ቤት በክልል አደረጃጀት ላይ ውሳኔ ለማሳለፍ አስቸኳይ ጉባኤ ጠራ

በተስፋለም ወልደየስ

የወላይታ ዞን ምክር ቤት ራሱን ችሎ በክልልነት ለመደራጀት ባቀረበው ጥያቄ ላይ ለመወያየት አስቸኳይ ጉባኤ ጠራ። ነገ ሰኞ ሰኔ 15፤ 2012 በሶዶ ከተማ፣ ጉታራ አዳራሽ ይካሄዳል የተባለው አስቸኳይ ጉባኤ በክልል ጥያቄ ቀጣይ አካሄዶች ላይ ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል። 

የወላይታ ዞን የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዩች መምሪያ ኃላፊ ሶልያና አዴሎ የነገው ስብሰባ ዋነኛ አጀንዳ “የክልል አደረጃጀት የደረሰበት ደረጃ ላይ መወያየት እና ቀጣይ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ” መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። “በዋናነት አጀንዳው የክልል ጥያቄው አሁን የደረሰበትን ደረጃ መገምገም ነው። አባላቱ ናቸው ተወያይተው አቅጣጫ የሚያስቀምጡት” ብለዋል።

የዞኑ ምክር ቤት 113 አባላት ከክልል ጥያቄው ጋር በተያያዘ፣ በየጊዜው እየተገናኙ “ቀጣይ የትግል አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ አካሄዱን ሲመሩ መቆየታቸውን” ኃላፊዋ አስታውሰዋል። በነገው ጉባኤ ከምክር ቤቱ አባላት በተጨማሪ በተወካዮች ምክር ቤት የወላይታ ተመራጮች እና በደቡብ ክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች የሆኑ የወላይታ ተወላጆች ይገኛሉ ተብሏል። 

ራሳቸውን ከደቡብ ክልል ምክር ቤት ያገለሉ 38 የወላይታ ተወካዮች በነገው የዞኑ ምክር ቤት ጉባኤ ይገኛሉ ተብሏል። | ፎቶ፦ የወላይታ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ

የህዝባችን በክልል የመደራጀት ጥያቄ “ተደማጭነት አላገኘም” በሚል ራሳቸውን ከደቡብ ክልል ምክር ቤት ያገለሉ 38 የወላይታ ተወካዮች፤ የዞኑ ምክር ቤት አባልም በመሆናቸው በነገው ጉባኤ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል። ባለፈው ሐሙስ ሰኔ 11 አስቸኳይ ጉባኤውን ያካሄደው የደቡብ ክልል ምክር ቤት ሰላሳ ስምንቱ የወላይታ አባላት በሌሉበት ነበር የተደረገው። የክልሉ ምክር ቤት የደቡብ ክልልን እንደገና የማወቀር ጥያቄን በተመለከተ ሰፋ ያለ ውይይት ቢያካሂድም የወላይታ ተወካዮች ውሳኔንም ሆነ ጥያቄያቸውን ሳይመለከት አልፏል።

የወላይታ ተወካዮች የወሰዱትን ራስን የማግለል እርምጃ ተከትሎ ከክልልነት ጥያቄው ጋር የተያያዙ ተከታታይ ውይይቶች ባለፉት ቀናት ሶዶ ከተማን ጨምሮ በወላይታ የተለያዩ አካባቢዎች ሲካሄዱ መቆየታቸውን ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በስብሰባዎቹ ላይ በተደጋጋሚ ከተነሱት ሀሳቦች ውስጥ “ህዝቡ ቁጣውን ለመግለጽ ሰላማዊ ሰልፍ ይደረግ” የሚል እንደሚገኝበት ምንጮች ገልጸዋል። 

በተወካዮች ምክር ቤት የሚገኙ የወላይታ ተመራጮች እንደዚሁም በፌደራል፣ በክልል እና በገዢው ፓርቲ ውስጥ ያሉ ባለስልጣናት እና አመራሮችም ከኃላፊነታቸው እንዲለቅቁ በስብሰባዎቹ ተደጋጋሚ ጥያቄ ሲቀርብ ነበር ተብሏል። “ህዝቡ ከመንግስት አስቸኳይ ምላሽ ይፈልጋል አለበለዚያ ነገሩ ወደ ጸጥታ ስጋት ሊያመራ ይችላል” ሲሉ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ አንድ ምንጭ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)