የወላይታ ዞን ምክር ቤት የወላይታ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት እንዲቋቋም ውሳኔ አሳለፈ

በተስፋለም ወልደየስ

የወላይታ ዞን ምክር ቤት ዛሬ ሰኞ ሰኔ 15፤ 2012 ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ የወላይታ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት እንዲቋቋም ውሳኔ አሳለፈ። የክልሉን መንግስት ለማደራጀት የሚያስችል ሴክሬቴሪያት ጽህፈት ቤትም እንዲቋቋም እና የቅድመ ዝግጅት ስራዎችም እንዲከናወኑም ወስኗል። 

ምክር ቤቱ በሶዶ ከተማ፣ ጉተራ አዳራሽ ባካሄደው ጉባኤው በብቸኝነት የተመለከተው አጀንዳ፤ የወላይታ ብሔር በክልል የመደራጀት ጥያቄ የደረሰበትን ደረጃ ነው። በአጀንዳው ላይ ለሰዓታት የዘለቀ ውይይት ያደረገው ምክር ቤቱ በጉባኤው መገባደጃ ሰባት የውሳኔ ሀሳቦችን በሙሉ ድምጽ አጽድቋል። 

ከውሳኔ ሀሳቦቹ ውስጥ ይበልጥ ትኩረት የተሰጠው የወላይታ ክልል መንግስት እንዲቋቋም የዞኑ ምክር ቤቱ ያሳለፈው ውሳኔ ነው። ከጉባኤው መጠናቀቅ በኋላ ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳጋቶ ኩምቤ ይህንኑ ጉዳይ ቅድሚያ ሰጥተው አንስተዋል።  “የወላይታ ህዝብ ጥያቄ በክልል የመደራጀት ጥያቄ ነው” ያሉት ዋና አስተዳዳሪው የመጀመሪያው ውሳኔ ይህንን የተመለከተ እንደሆነ ገልጸዋል።    

“የህዝቡ ጥያቄ ግልጽ እና ግልጽ ነው። ህዝቡ የጠየቀው መጠሪያው የወላይታ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት [ሆኖ] በዚህ ልክ የሚጠራው፣ የስራ ቋንቋው ወላይትኛ የሆነውን፣ ዋና መቀመጫው ወላይታ ሶዶ የሆነውን ክልል ለመመስረት ነው። ከዚህ ውጭ ያሉ አማራጮች ህዝቡ ያልጠየቀው ስለሆነ ተቀባይነት እንደማይኖረው የዛሬ ምክር ቤት ወስኗል” ብለዋል አቶ ዳጋቶ። 

የወላይታ የክልልነት ጥያቄ በመንግስት በኩል “ባጠረ ጊዜ ይመለሳል የሚል እምነት አለን” ያሉት ዋና አስተዳዳሪው “ጥያቄው ሲመለስ በቀጥታ እና በፍጥነት ወደ ስራ ለመግባት የሚያግዝ የሴክሬቴሪያት ጽህፈት ቤትም እንዲቋቋም በዛሬው ጉባኤ ተወስኗል” ብለዋል። ራሱን ችሎ ይቋቋማል የተባለው ይህ ጽህፈት ቤት የፖለቲካ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ጥናት እና ዝግጅት የሚያደርግ እንደሆነም ገልጸዋል።

ጽህፈት ቤቱ “የራሱ የሆነ በጀት ያለው እና በህዝብና በመንግስት የሚደገፍ ነው” ያሉት አቶ ዳጋቶ “የተለያዩ ስራዎችን በባለቤትነት የሚሰራ ተቋም መቋቋም ስላለበት” ውሳኔው መተላለፉን አብራርተዋል። በጉባኤው ከተነሱ የዝግጅት ስራዎች ውስጥ የክልሉን ሕገ መንግስት ማርቀቅ እና የክልሉን ማህበራዊና ኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን ማዘጋጀት እንደሚገኝበት በወላይታ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዩች መምሪያ ባለሙያ የሆኑት አቶ ደሳለኝ ደረሰ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። “የክልሉ ባንዲራ ምን መምሰል አለበት?” የሚለውም በዝግጅቱ ጊዜ ከሚታዩት አንዱ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በዛሬው ጉባኤ ውሳኔ ከተላለፈባቸው ጉዳዩች ውስጥ በሕገ መንግስቱ ክልል ለመሆን በመስፈርትነት የተቀመጠው የህዝበ ውሳኔ ሂደት አንዱ ነው። የወላይታ ክልልን ለመመስረት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ህዝበ ውሳኔ እንዲደራጅ ያስችል ዘንድ የዞኑ ምክር ቤት በጉባኤው መጠየቁን አቶ ደሳለኝ ገልጸዋል። የወላይታ ብሔር በክልልነት ለመደራጀት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ላቀረበው ጥያቄም ምክር ቤቱ “አፋጣኝ ምላሽ” እንዲሰጥም አሳስቧል። 

የወላይታ ዞን ምክር ቤት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥያቄውን ያቀረበው፤ ዞኑ ራሱን ችሎ በክልልነት እንዲደራጅ ውሳኔ ባሳለፈ በዓመቱ፤ ባለፈው ታህሳስ ወር ነበር። ምክር ቤቱ ጥያቄውን ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት በይግባኝ የወሰደው “የደቡብ ክልል ምክር ቤት “በክልል ለመደራጀት ላቀረብኩት ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ አልሰጠኝም” በሚል ነበር።

የደቡብ ክልል ምክር ቤት ላይ ተመሳሳይ ቅሬታ ያቀረቡ 38 የወላይታ ተወካዮች ራሳቸውን ከምክር ቤት እስከ ማግለል የደረሰ እርምጃ ባለፈው ሳምንት ወስደዋል። የክልል ምክር ቤት ተወካዮቹ የወሰዱት እርምጃ በዛሬው ጉባኤ ተነስቶ እንደነበር የሚናገሩት የሚዲያ ግንኙነት ባለሙያው አቶ ደሳለኝ፤ ውሳኔ ከተላላፈባቸው ሰባት ጉዳዩች አንዱ እርሱ እንደሆነ አስረድተዋል።

ተወካዮቹ በክልሉ ምክር ቤት ጉባኤ ላይ ያለመሳተፋቸው “ትክክለኛ አቅጣጫ እና የህዝቡን መብት የሚያስከብር ነው” የሚሉ ሀሳቦች በዛሬው ጉባኤ ላይ መሰንዘሩን እና በተሳታፊዎች አድናቆት እንደተቸረውም ገልጸዋል። የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪም ይህንኑ በመግለጫቸው አረጋግጠዋል። ተወካዮቹ ለምን መልቀቂያ እንዳስገቡ የደቡብ ክልል መንግስት እስካሁን ድረስ አለመጠየቁን ያነሱት አቶ ዳጋቶ ይህም በጉባኤው ተሳታፊዎች በበጎ እንዳልታየ ጠቁመዋል። 

“ይሄ በድጋሚ የክልሉ መንግስት ለወላይታ ህዝብ ያለውን ንቀት የሚያሳይ ስለሆነ [ጉባኤው] አውግዟል” ብለዋል። የፌደራል መንግስት፤ መልቀቂያ ያስገቡትን የደቡብ ምክር ቤት አባላት ጠርቶ፤ ጥያቄያቸው ምን እንደሆነ እንዲያወያይ ጉባኤው ውሳኔ ማስተላለፉንም ተናግረዋል።       

በዛሬው ጉባኤ የተላለፈ ሌላ የውሳኔ ሀሳብ ከዚሁ ከክልል ምክር ቤት አባላት እርምጃ ጋር የተያያዘ ነው። ከአባልነታቸው የለቀቁት የወላይታ ተወካዮች በሌሉበት፤ የደቡብ ክልል ምክር ቤት የሚያስተላልፋቸው ውሳኔዎች በወላይታ ዞን ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት በዞኑ ምክር ቤት መጽደቅ እንዳለበት በዛሬው ጉባኤ ተወስኗል።  

በጉባኤው ተሳታፊዎች የተነሳው የተቀባይነት ጥያቄ በደቡብ ክልል ምክር ቤት ብቻ አልተወሰነም። በክልሉ የጸጥታ መዋቅር ላይም ተመሳሳይ ጥያቄ ተነስቷል። በጉባኤው ላይ የወላይታ የክልልነት ጥያቄን አስመልክቶ ሰፊ ማብራሪያ በወላይትኛ ቋንቋ ሲሰጡ የነበሩት አቶ ዳጋቶ በደቡብ ክልል ልዩ ኃይል ላይ “እምነት እንደሌላቸው” በግልጽ ተናግረዋል። 

ዋና አስተዳዳሪው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ ግን እምነት ያጡት በክልሉ የጸጥታ መዋቅር አመራሮች ላይ እንደሆነ ጠቅሰዋል። ይህን ሀሳባቸውን የጉባኤው ተሳታፊዎች እንደሚጋሩትም ጠቁመዋል። በዚህም ምክንያት በአካባቢያቸው ያለው የጸጥታ ማስከበር ስራ፤ በመጀመሪያ በህዝቡ፣ በመቀጠል ደግሞ በዞኑ የጸጥታ መዋቅር እንዲከናወን ውሳኔ መተላለፉን ገልጸዋል። የጸጥታ ሁኔታው አቅም በላይ ከሆነ ከፌደራል ፖሊስ አሊያም ከመከላከያ ሰራዊት ጋር በመተባበር እንደሚሰሩም አስታውቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)