የደቡብ ኦሞ ዞን ምክር ቤት በክልልነት ጥያቄ ላይ አቋም ለመያዝ አስቸኳይ ጉባኤ ጠራ

በደቡብ ክልል በክልልነት ለመደራጀት ጥያቄ ካቀረቡ ዞኖች መካከል አንዱ የሆነው የደቡብ ኦሞ ዞን፤ በጉዳዩ ላይ አቋም ለመያዝ ለነገ ሰኔ 17፤ 2012 አስቸኳይ ጉባኤ ጠራ። በጉባኤው ላይ የዞኑ ተወላጅ የሆኑ የደቡብ ክልል ከፍተኛ አመራሮች እና የክልሉ ምክር ቤት አባላት እንደሚሳተፉ ተገልጿል። 

የደቡብ ኦሞ ዞን የህዝብ ግንኙነት ጽህፈት ቤት እንዳስታወቀው የነገው ጉባኤ በ2011 ዓ.ም. በዞኑ ምክር ቤት የጸደቀው የክልልነት ጥያቄ የደረሰበትን ደረጃ እና የተሰጠውን ምላሽ በተመለከተ ይመክራል። ከውይይቱ በኋላም ጉባኤው በጉዳዩ ላይ ያለውን አቋም ይፋ እንደሚያደርግ የዞኑን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ናኪያ አናቆሲያን ጠቅሶ አስታውቋል። 

የዞኑን በክልልነት የመደራጀት ጥያቄ በተመለከት ትላንት ሰኞ ሰኔ 15 በጂንካ ከተማ ውይይት መካሄዱንም የከተማዋ አስተዳደር ገልጿል። የጂንካ ከተማ መካከለኛ አመራሮች በተሳተፉበት በዚህ ውይይት “የሰላም አምባሳደሮች” የተሰኘው ቡድን ያቀረበው የጥናት ውጤት ተተችቷል። 

ቡድኑ ከዚህ ቀደም በጂንካ ከተማ ከህዝብ ጋር ባደረገው ውይይት፤ ዞኑ ራሱን ችሎ ክልል ሆኖ እንዲደራጅ በምክር ቤት የተላለፈው ውሳኔ ድጋፍ አግኝቶ እንደነበር አመራሮቹ አስታውሰዋል። ሆኖም ቡድኑ በስተመጨረሻ ባቀረበው ምክረ ሃሳብ ዞኑ ከወላይታ፣ ጋሞ፣ ጎፋ እና ሌሎች ብሔሮች ጋር በአንድ ክልል እንዲዋቀር ማድረጉ ተቀባይነት እንደሌለው መግለጻቸውን የጂንካ ከተማ አስተዳደር ያወጣው መረጃ አመልክቷል።     

የጂንካውን ስብሰባ የተሳተፉ አመራሮች “ከእነዚህ ዞኖች ጋር በመሆን ክልል እንዲመሰረት የታሰበው 16 ብሄር ብሄረሰብን መብት የሚጨፈልቅ በተለይም ደግሞ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብታችን ዕድል የሚዘጋ በመሆኑ በፍጹም መደራደር አንችልም” ማለታቸውን አስተዳደሩ ገልጿል። አመራሮቹ “የቡድኑ ምክረ ሀሳብ ጨርሶ የተሳሳተና የተዛባ አካሄድ ስለሆነ በተገቢው አካል ታይቶና እርምት ተደርጎ ፍትሃዊ ምላሽ እንዲሰጠን” በማለት መጠየቃቸውንም አክሏል።

በደቡብ ክልል 17 ዞኖች እና አራት ልዩ ወረዳዎች ያሉ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ አስሩ በክልልነት የመደራጀት ጥያቄያቸውን ለክልሉ ምክር ቤት ማስገባታቸውን ባለፈው ሳምንት በተካሄደው የምክር ቤቱ አስቸኳይ ጉባኤ ላይ ተጠቅሶ ነበር። የክልልነት ጥያቄ ካቀረቡት ዞኖች መካከል አንዱ የሆነው የወላይታ ዞን ምክር ቤት ትላንት ሰኔ 15፤ 2012 ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ የወላይታ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት እንዲቋቋም ውሳኔ ማሳለፉ አይዘነጋም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)