በሐይማኖት አሸናፊ
የህዳሴውን ግድብን አስመልክቶ ትላንት ሰኞ ሰኔ 15፤ 2012 በቪዲዮ ኮንፍረንስ ስብሰባውን ያካሄደው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት፤ ግብጽ ባቀረበቸው “የግልጽ ጉባኤ ይካሄድልኝ” ጥያቄ ላይ ከስምምነት ላይ ሳይደርስ ቀረ። ምክር ቤቱ ግብጽ፣ ኢትዮጵያ እና ሱዳን ውይይታቸውን እንዲቀጥሉ በማሳሰብ ያለ ውሳኔ ተበትኗል።
በትላንቱ ስብሰባ የሰኔ ወር የጸጥታው ምክር ቤት ፕሬዘዳንት የሆነችው ፈረንሳይ፤ ሶስቱ የአባይ ተፋሰስ ሀገራት ለምክር ቤቱ የላኳቸውን ደብዳቤዎች ለአባል ሀገራት አቅርባለች። አስራ አምስቱ የጸጥታው ምክር ቤት አባላት በሶስቱ አገራት መካከል የተጀመሩ የሶስትዮሽ ድርድሮችን በሙሉ ድምጽ መደገፋቸውን “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በኒው ዮርክ ካሉ ምንጮቿ አረጋግጣለች። የምክር ቤቱ አባላት “ሶስት አገራት ችግሮቻቸውን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንዲፈቱ እና ስምምነት ላይ ያልተደረሱ ቀሪ ነጥቦችንም በዚሁ አግባብ መፍታት ይገባቸዋል” ማለታቸውን ምንጮቹ ገልጸዋል።
አሜሪካ በተያዘው ሳምንት ግልጽ ጉባኤ እንዲጠራ እና የሚመለከታቸው አካላትም እንዲሳተፉ በግብጽ የቀረበውን ሃሳብ ደግፋ ቀርባለች። በምክር ቤቱ ቋሚ መቀመጫ ካላቸው አምስት አገራት መካከል አንዷ የሆነቸው ቻይና በበኩሏ “ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄዎች ያስፈልጋሉ” በሚል ከአሜሪካ ተቃራኒ አቋም ይዛለች።
በሶስትዮሹ ድርድር ታዛቢ የነበረችው ደቡብ አፍሪካ ከሌላኛዋ አፍርካዊት አገር ኒጀር ጋር በጋራ በግብጽ ለቀረበው ሃሳብ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል። ሁለቱ አገራት “ጉዳዩ ወደ ጸጥታው ምክር ቤት እንዳይታይ፣ የሶስትዮሽ ድርድሮች እንዲቀጥሉ እና በዚህ ሂደትም የአፍሪካ ህብረት ሚናውን እንዲጫወት በማድረግ ጉዳዩ ሊፈታ ይገባል” ሲሉ አቋማቸውን አሳውቀዋል።
የጸጥታው ምክር ቤት “ጉዳዩን ይያዘው ወይም አይያዘው” በሚል ጉዳይ ድምጽ ለመስጠት የዲጂታል ስብሰባው አመቺ ሆኖ ባለመገኘቱ በትላንቱ ስብሰባ ድምጽ ሳይሰጥ ቀርቷል። ስብሰባውን በፕሬዝዳንትነት የመሩት የፈረንሳይ ዲፕሎማት የምክር ቤቱ አባል አገራት ስምምነት ላይ እስኪደርሱ ንግግራቸውን እንዲቀጥሉ ወስነው የቪዲዮ ኮንፍረንሱ በዚሁ ተገባድዷል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪክ በትላንትናው ዕለታዊ መግለጫቸው የሶስቱን የአባይ ተፋሰስ ሀገራት ጉዳይ አንስተዋል። ቃል አቃባዩ “በሶስቱ አገራት መካከል የተጀመረው ድርድር መልካም የሚባሉ ለውጦችን እያሳየ ነው” ብለዋል። ሶስቱ አገራት ችግሮቻቸውን ለመፍታት እና ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ስምምነት ላይ ለመድረስ በድርድሮቻቸው ጸንተው እንዲቀጥሉም መክረዋል።
“[ሶስቱ] አገራት ሁሉንም ተጠቃሚ እና አሸናፊ በሚያደርግ፣ በቅን ልቦና እንዲሁም በአለም አቀፍ መርሆዎች ላይ በተመሰረተው በዚህ የስምምነት መርህዎ መንፈስ ተመስርተው ውይይታቸውን መቀጠል አለባቸው”
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ
የተመድ ዋና ጸሃፊ ሶስቱም አገራት በ2007 የተፈረመውን የስምምነት መርህዎች እንዲያከብሩ አፅንኦት መስጠታቸውን ቃል አቃባዩ በትላንት መግለጫቸው አስታውሰዋል። ዋና ጸሃፊው “አገራት ሁሉንም ተጠቃሚ እና አሸናፊ በሚያደርግ፣ በቅን ልቦና እንዲሁም በአለም አቀፍ መርሆዎች ላይ በተመሰረተው በዚህ የስምምነት መርህዎ መንፈስ ተመስርተው ውይይታቸውን መቀጠል አለባቸው” ሲሉ መናገራቸውን ቃል አቃባያቸው ጠቅሰዋል።
“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ስለ ስብሰባው ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ለኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ጥያቄ ብታቀርብም ይህ ዘገባ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ ምላሽ ማግኘት አልቻለችም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)