የደቡብ ኦሞ ዞን ምክር ቤት በ“ኦሞቲክ ክልል” የመደራጀት ሀሳብን ውድቅ አደረገ

በተስፋለም ወልደየስ

የደቡብ ኦሞ ዞን ምክር ቤት ዛሬ ረቡዕ ሰኔ 17፤ 2012 በጂንካ ከተማ ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ የ“ሰላም አምባሳደሮች” የተሰኘው ቡድን ዞኑን በአሞቲክ ክልል ስር ለማደራጀት ያቀረበውን ምክረ ሃሳብ ውድቅ አደረገ። ምክር ቤቱ የዞኑ ህዝብ ራሱን ችሎ በክልል ለመደራጀት ፍላጎቱን የገለጸባቸው የሰነድ፣ የድምጽ እና የቪዲዮ ማስረጃዎች ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በድጋሚ እንዲቀርብ ውሳኔ አሳልፏል። 

ምክር ቤቱ በዛሬው ጉባኤ በአራት አጀንዳዎች ላይ ቢወያይም ሰፊ ጊዜውን ወስዶ የመከረው ግን ዞኑ ያቀረበው የክልልነት ጥያቄ የደረሰበት ደረጃን በተመለከተ እንደነበር የዞኑ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ መላኩ ለማ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። እስከ ምሽት አንድ ሰዓት ተኩል ገደማ ድረስ የዘለቀው ጉባኤው “ጫን ያለ” እንደነበር ኃላፊው ገልጸዋል። 

ከክልልነት ጥያቄው ጋር በተያያዘ የጉባኤው ተሳታፊዎች በተደጋጋሚ ካነሷቸው ሃሳቦች ውስጥ የ“ሰላም አምባሳደሮች” የተሰኘው ቡድን የተመለከቱ ላቅ ያለ ቦታን እንደሚወስዱ አቶ መላኩ አስረድተዋል። ቡድኑ የደቡብ ክልልን የአደረጃጀት ጥያቄዎች ለመፍታት ያዘጋጀው ምክረ ሃሳብ “የዞኑን ህዝብ ፍላጎት ያንጸባረቀ አይደለም” በሚል በተሳታፊዎች መተቹትን አብራርተዋል። 

ፎቶ፦ የደቡብ ኦሞ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን መምሪያ

በቀድሞው የተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አባዱላ ገመዳ የሚመራው እና 83 አባላትን የያዘው ቡድን የተሻሻለ ያለውን ምክረ ሃሳብ ከሁለት ሳምንት በፊት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በተካሄድ ስብሰባ ላይ አቅርቦ ነበር። ምክረ ሃሳቡ በህዝበ ውሳኔ ክልል መሆኑን ካረጋገጠው የቀድሞው የሲዳማ ዞን ውጭ ያሉትን የደቡብ አካባቢዎች በሶስት ክልሎች መልሶ የሚያዋቅር ነው። 

በዚህም መሰረት የደቡብ ኦሞ ዞን “ኦሞቲክ” በሚል መጠሪያ በሚታወቀው አካባቢ በሚመሰረተው ክልል ውስጥ እንዲካተት በምክረ ሃሳቡ ተደልድሎ ነበር። አስራ ስድስት ብሔሮችን በውስጡ ከሚይዘው የደቡብ ኦሞ ዞን ጋር በጋራ ክልል እንዲመሰርቱ የታሰቡት የጋሞ፣ ጎፋ፣ ኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ደራሼ፣ ቡርጂ፣ አማሮ እና ኮንሶ ዞኖች እንዲሁም ልዩ ወረዳዎች ናቸው። ሲያወዛግብ የቆየው የወላይታ ዞን የክልልነት ጥያቄ ጉዳይም በዚህ ክልል ስር እንዲጠቃልል በምክረ ሃሳቡ ተካትቶ ነበር።

የ“ሰላም አምባሳደሮች” ቡድን ምክረ ሃሳቡን ከማቅረቡ በፊት በዞኑ በመገኘት ከየብሔር ብሔረሰቡ የተውጣጡ ተወካዮችን በዞኑ ማዕከል ማናገሩን የኮሚዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊው አስታውዋል። የውይይቱ ውጤት ህዝቡ ከገለጸው በተቃራኒ መሆኑ በዛሬው ጉባኤ ተቃውሞ መቀስቀሱን ጠቁመዋል።   

“[ከውይይቱ] በኋላ ‘የህብረተሰቡ አቋም ምንድነው?’ የሚለውን ገጽታ ወስደው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በትክክል፣ ምንም ነገር ሳይሸራርፍ ያቀርባሉ ተብሎ ነበር የሚጠበቀው። ነገር ግን ሄዶ የቀረበው ይሄ አይደለም፤ ሌላ ነው” ሲሉ አቶ መላኩ የነበረውን ሂደት ያስረዳሉ። “አጥኚ ቡድኑ ምክረ ሃሳቡን ካቀረበ በኋላ ሲሰማ የህብረተሰቡ አንደበት፣ ፍላጎት ሳይሆን እዚያ የተንጸባረቀው የኮሚቴዎች ፍላጎት ነው” ብለዋል። 

የ“ሰላም አምባሳደሮቹ” አካሄድ “ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ጭምር በተሳሳተ መንገድ ውሳኔ ሊያስወስን ይችላል” በሚል የሰጉት የጉባኤው ተሳታፊዎች አጥኚ ቡድኑ የህዝብ ውይይት ሲያደርግ በነበረ ሰዓት የተያዙ ሰነዶችን፣ ድምጾችን እና በቪዲዮ የተቀረጹ ማስረጃዎችን በሙሉ በድጋሚ ለጽህፈት ቤታቸው እንዲቀርብ ውሳኔ ማስተላለፋቸውን የመምሪያ ኃላፊው ተናግረዋል። በምክረ ሃሳቡ ስለ ደቡብ ኦሞ ዞን የቀረበው “የጥቂት ሰዎች አስተሳሰብ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲረዱልን ነው” ሲሉም አክለዋል።    

ፎቶ፦ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት

የደቡብ ኦሞ ዞን ህዝቡን “እውነተኛ ፍላጎት ያሳያሉ” የተባሉ ሰነዶች በቅርቡ በተካሄደው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ስብሰባ ዋዜማ ለምክር ቤቱ ቀርቦ እንደነበር የሚጠቅሱት አቶ መላኩ በዚያን ጊዜ እነዚያው ሰነዶች ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ገቢ መደረጋቸውን አመልክተዋል። አሁን በተሟላ መልኩ የተደራጁት ማስረጃዎች ከጽህፈት ቤቱ በተጨማሪ በድጋሚ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲቀርብ “ጉባኤው ከውሳኔ ላይ ደርሷል” ብለዋል።

በደቡብ ክልል ውስጥ ካሉ 17 ዞኖች ውስጥ አንዱ የሆነው የደቡብ ኦሞ ዞን  በክልልነት የመደራጀት ጥያቄውን ለክልሉ ምክር ቤት ያቀረበው በመጋቢት 2011 ዓ.ም. ነበር። የክልሉ ምክር ቤት ተመሳሳይ ጥያቄዎች እንዳቀረቡ ሌሎች ዘጠኝ ዞኖች ሁሉ ጉዳዩን በመደበኛም ሆነ በአስቸኳይ ጉባኤ ሳይመለከት በመቅረቱ ተቃውሞዎች ሲቀርቡበት ቆይቷል።  

“አሁን ዳግም ለደቡብ ክልል ምክር ቤት የምናቀርበው ጥያቄ የለንም። ጥያቄያችን መቶ ፐርሰንት ምላሽ የሚያገኘው ሕገ መንግስታዊ በሆነ አግባብ ስለሆነ፤ ሕገ መንግስቱን ተከትለን፣ መርህ ላይ ሆነን፣ ሕገ መንግስታዊ ምላሽ ለማግኘት፤ ህዝቡም፣ የመንግስት አካሉም፣ ምክር ቤቱም ሰላማዊ ትግል በማድረግ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዳግም እንዲኬድ አቅጣጫ ተቀምጧል” ሲሉ አቶ መላኩ የዛሬውን ጉባኤ ውሳኔ ጠቅለል አድርገው አቅርበዋል።

“አሁን ዳግም ለደቡብ ክልል ምክር ቤት የምናቀርበው ጥያቄ የለንም። ጥያቄያችን መቶ ፐርሰንት ምላሽ የሚያገኘው ሕገ መንግስታዊ በሆነ አግባብ ስለሆነ…ሰላማዊ ትግል በማድረግ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዳግም እንዲኬድ አቅጣጫ ተቀምጧል”

አቶ መላኩ ለማ – የደቡብ ኦሞ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ

ከሁለት ሳምንት በፊት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በተካሂደው ስብሰባ የ“ሰላም አምባሳደሮች” ቡድን ያቀረበው ምክረ ሃሳብ ወደ ፊዴሬሽን ምክር ቤት እንዲመራ ውሳኔ መተላለፉ ቢነገርም የደቡብ ክልልን ወደ ሶስት ቦታ የመክፈል እቅዱ ከየአቅጣጫው ተቃውሞ እየገጠመው ይገኛል። ባለፈው ሳምንት በተካሄደው የደቡብ ክልል ምክር ቤት አስቸኳይ ጉባኤ የተሳተፉ አባላት ምክረ ሃሳቡን ሲተቹት ተደምጠዋል።

የምክር ቤቱ አባላት የየወከሉትን ዞን እየጠቀሱ ያቀረቡት የክልልነት ጥያቄ ተግባራዊ እንዲሆን አሳስበዋል። የክልልነት ጥያቄያችን “ተደማጭነት አላገኘም” ያሉ የወላይታ ዞን ተወካዮች ራሳቸውን ከምክር ቤት አባልነት ጭምር አግልለዋል። ተወካዮቹ አባል የሆኑብት የወላይታ ዞን ምክር ቤት ከትናንት በስቲያ ሰኞ ሰኔ 15፤ 2012 ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ የክልላዊ መንግስት እንዲቋቋም እና ለዚህም ዝግጅት እንዲደርግ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)