ኢዜማ ኢትዮ ቴሌኮምን በከፊል ወደ ግል የማዘዋወር ጥድፊያ ይቁም ሲል ጠየቀ

በሐይማኖት አሸናፊ 

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) በኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ ወሳኝ ሚና የሚጫወተው የኢትዮ ቴሌኮምን ድርሻ ለመሸጥ “መንግስት እየሄደበት ያለውን ሩጫ በአስቸኳይ ሊያቆም ይገባል” ሲል ጠየቀ። ፓርቲው “መንግስት በቂ ጥናት ሳያካሂድ፣ ቅድሚያ ለሚፈልጉ ጉዳዮች ቅድሚያ ሳይሰጥ፣ ሕዝብ እና ወኪሎቹ ሳይመክሩ እንዲሁም ሕጋዊ ቅቡልነቱን ሳያረጋግጥ በውጪ ጫና የወሰነውን ውሳኔም ይቀልብስ” ሲል አሳስቧል።  

ገዢው ፓርቲ “ያለ ውይይት እና ግልፅነት በጎደለው መልኩ” የኢትዮ ቴሌኮምን ከፊል ድርሻ ለመሸጥ የሚከተለው አካሄድ፤ በዓለም ባንክ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ምክር “የምጣኔ ሃብት ማሻሻያ ካደረጉ አገሮች ጋር ተመሳሳይ መንገድ ውስጥ” ያስገባው እንደሆነ ፓርቲው ጠቁሟል።

አሁን እየተደረገ ያለው ማሻሻያ “ወደፊት ተመርጦ ሥልጣን የያዘ መንግሥት እንኳን ሊያስተካክላቸው የማይችሉ ውሳኔዎችን የማስተላለፍ መብት በፍፁም የለውም” ሲል ኢዜማ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በላከው መግለጫ ላይ ገልጿል። ገዢው ፓርቲ እንዲህ ያሉ ትልልቅ ማሻሻያዎችን “በምርጫ ፖሊሲው ላይ ይፋ አድርጎ የሕዝብን ፈቃድ ሊያገኝ ይገባል” ሲልም ፓርቲው አስታውቋል።

ኢዜማ “ጥድፊያ” ያለውን ይህንን ሂደት በተለይም ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ የቴሌኮም የአክሲዮን ድርሻ ዋጋ ዓለም ላይ ከመውረዱ ጋር በማያያዝም አብራርቷል። በመላው አለም 40 ትልልቅ ዓለም አቀፍ የቴሌኮም ኩባንያዎች በአለም አቀፍ የገበያ መረጃ ቋቶች ላይ መመልከት እንደሚቻለው የአክሲዮን ደርሻ ዋጋቸዉ “ቀይ ዞን” ውስጥ መግባቱን በማስረጃነትም አቅርቧል።

ይህበዚህ ወቅት የሚደረግ የህዝብን ንብረት ወደ ግል የማዛወር ሂደት የሚያስገኘው የውጪ ምንዛሬ መጠን የቱንም ያህል ቢሆን ገዥ ያጣ ንብረት በሚጣልበት ዋጋ እንደተሸጠ ይታሰባል”

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ)

“ይህም በዚህ ወቅት የሚደረግ የህዝብን ንብረት ወደ ግል የማዛወር ሂደት የሚያስገኘው የውጪ ምንዛሬ መጠን የቱንም ያህል ቢሆን ገዥ ያጣ ንብረት በሚጣልበት ዋጋ እንደተሸጠ ይታሰባል” ሲል ፓርቲው አስጠንቅቋል።

“በኮቪድ-19 አማካኝነት በአለማችን የኢኮኖሚ ስርአት እና ትብብር ላይ ለውጦች ሊፈጠሩ ይችላሉ” የሚል አንድምታ ያለው የኢዜማ ትንታኔ ለዚህም ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ሀገራት በተለይም የህክምና መሣሪያዎችን ለማግኘት ያጋጠማቸውን ችግር በማሳያነት አንስቷል። አገራቱ የህክምና መሣሪያዎችን ከዚህ በፊት በሚያገኙት ፍጥነት እና ፍላጎት ልክ ማግኘት አቅቷቸው እንደተቸገሩ እና በዚህም ምክንያት እርስ በርስ ያላቸውን የኢኮኖሚ ግንኙነት እና ጥገኝነት ቆም ብለው እየተመለከቱ መሆኑን አብራርቷል። 

“ይህም በተለይም አገራት ሉዓላዊነታቸው እና የምርት ነፃነት ላይ በትኩረት እንዲሠሩ የማንቂያ ደውል ሆኖላቸዋል” ብሏል በመግለጫው። “የበሽታውን ውጤት እና አለም የምትገባበት የኢኮኖሚ ሥርዓት ለውጥ በማይተነበይበት ወቅት የሚወሰን እንዲህ ያለ ትልቅ ውሳኔ ዋጋ ሊያስከፍል ይችላል” ሲልም መንግስት የኢትዮ ቴሌኮምን ወደ ግል ለማዘዋወር የሚከተለው አካሄድ ላይ ያለውን ስጋት ገልጿል። 

መንግስት የኢትዮ ቴሌኮምን ድርሻ ለመሸጥ በምክንያትነት ያስቀመጣቸው “የውጪ ምንዛሬ እጥረትን መፍታት እና ዘርፉን ማዘመን” የሚሉ መሆናቸውን ያስታወሰው የፓርቲው የፖሊሲ ትንተና “በሂደቱ ሊከተሉ የሚችሉ ትልልቅ አደጋዎች ጋር ባግባቡ የተነፃፃረ አይደለም” ሲልም ተችቷል።

“በ21ኛው ክፍለ ዘመን የቴሌኮሙ ዘርፍ በመገናኛና መረጃ አስተላላፊነት ሳይወሰን ወታደራዊ፣ ፋይናንስ፣ መገናኛ-ብዙኃንና የፈጠራ ሥርዓቱን መቆጣጠሪያ ሆኖ ሳለ እንደ ተራ መረጃ ማስተላለፊያ ብቻ በማየት ለውጪ ድርጅቶች ለመሸጥ ማሰብ የአገርን ህልውና አደጋ ላይ መጣል ነው”

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ)

“በ21ኛው ክፍለ ዘመን የቴሌኮሙ ዘርፍ በመገናኛና መረጃ አስተላላፊነት ሳይወሰን ወታደራዊ፣ ፋይናንስ፣ መገናኛ-ብዙኃንና የፈጠራ ሥርዓቱን መቆጣጠሪያ ሆኖ ሳለ እንደ ተራ መረጃ ማስተላለፊያ ብቻ በማየት ለውጪ ድርጅቶች ለመሸጥ ማሰብ የአገርን ህልውና አደጋ ላይ መጣል ነው” ብሏል ፓርቲው። “የተቋሙ ባለቤትነት በከፊልም ቢሆን በግል ይዞታነት ሲወሰድ መንግሥት እነዚህን ለሀገራችን ወሳኝ የሆኑ ጉዳዮችን መቆጣጠር አቅምም አብሮ መቀነሱ አይቀሬ ነው” ሲልም አክሏል።

መንግስት በቅርቡ የኢትዮ ቴሌኮምን 40 በመቶ ድርሻ ለድንበር ተሻጋሪ ድርጅቶች ለመሸጥ “የሃብት ግመታ ሥራ እና ሽያጩን የሚያማክሩ አማካሪ ድርጅቶችን እየመረጠ እንደሚገኝ ደርሼበታለሁ” ያለው ኢዜማ “ይህ ድርጊት እንዲቆም እና መንግሥትም ቆም ብሎ እንዲያስብም” ጠይቋል።

ፓርቲው ያወጣው መግለጫ በኢትዮ ቴሌኮም የድርሻ ሽያጭ ላይ ሰፊ ትችት ያቅርብ እንጂ የቴሌኮም ዘርፉን ለውድድር መክፈት (ሊበራላይዜሽን) ፖሊሲን በተመለከተ ግን ምንም ያለው ነገር የለም። የኢዜማ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ናትናኤል ፈለቀ በሚቀጥለው ሳምንት ፓርቲው ይፋ በሚያደርገው የፖሊሲ ዝርዝር ላይ ይህንን አቋሙን እንደሚያሳውቅ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)