በሐይማኖት አሸናፊ
ዝነኛ የኦሮምኛ ሙዚቃ ዘፋኝ የሆነው አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ዛሬ ሰኞ ሰኔ 22፤ 2012 በገላን ኮንዶሚኒየም አካባቢ መገደሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሸነር ጌቱ አርጋው አረጋገጡ። ፖሊስ ገዳዮቹን ለማፈላለግ ሃይል ማሰማራቱንም ገልጸዋል፡፡
ኮሚሸነሩ “ፖሊስ በስፍራው ተገኝቶ በሂደቱ ውስጥ ያሉ ጉዳዮችን በዝርዝር እያጣራ [ነው]። ከግድያው በስተጀርባ ያሉ ግለሰቦችንም መረጃ በተመለከተ በየወቅቱ ለኢትዮጵያ ህዝብ የምንገልጽ መሆኑን እናሳውቃለን” ሲሉ ለብሔራዊው ቴሌቪዝን ጣቢያ “ኢቲቪ” ተናግረዋል።፡በመላው አዲስ አበባ ፍፁም ሰላማዊ ሁኔታ መኖሩንም ገልፀዋል። “የአዲስ አበባ ፖሊስም፤ የፌደራል ፖሊስም ሌሎች የጸጥታ አካላትም በዚህ ሂደት ውስጥ የተሳተፉትን በቁጥጥር ስር ለማዋል ድርጊቱ ከተፈጸመበት ጊዜ ጀምሮ በጋር ርብርብ እያደረጉ [ነው]” ሲሉም አክለዋል።
ፖሊስ መረጃው ከደረሰው ሰዓት ጀምሮ መደበኛ ስራውን እየሰራ መሆኑን ያስታወቁት ኮሚሽነሩ ግድያው በተፈጸመበት ገላን ኮንዶሚኒየም አካባቢ አሁን ያለው ሁኔታ “ጸጥ፤ እረጭ ያለ” መሆኑን ጠቁመዋል። በመላው አዲስ አበባ ፍፁም ሰላማዊ ሁኔታ መኖሩንም ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በሃጫሉ ሞት የተሰማቸውን ሀዘን“ውድ ህይወት አጥተናል” ሲሉ በግል የፌስ ቡክ ገጻቸው ገልጸዋል:: “የዚህ ድንቅና አንፀባራቂ ወጣት አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ህይወት መቀጠፍ ከተሰማ ጀምሮ በከባድ ሀዘን ውስጥ ለምንገኝ ሁሉ መፅናናትን እመኛለሁ” ብለዋል።
“የዚህን ክፉ ድርጊት ሙሉ የፖሊስ ምርመራ ሪፖርት እየተጠባበቅን እንገኛለን” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የድርጊቱን መጠን በመረዳት በሀገራችን ውስጥ ስለሚከናወኑ እንቅስቃሴዎች ትኩረት ሰጥተን የምንከታተልበት ወቅት ላይ ነን” ሲሉም አስገንዝበዋል። ህዝቡ ሀዘኑን በሚገልጽበት ጊዜ “ራሱን እንዲጠብቅ እና ተጨማሪ ወንጀሎችን እንዲከላከልም” አሳስበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)