በወቅታዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የሚመክር የደቡብ ክልል አመራሮች ኮንፍረንስ ዛሬ ተጀመረ

በተስፋለም ወልደየስ 

በክልል አደረጃጀት ጥያቄ እየታመሰ የሚገኘው የደቡብ ክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት እና አመራሮች፤ የፓርቲያቸውን ኮንፍረንስ ዛሬ በሃዋሳ ከተማ ማካሄድ ጀመሩ። ለሶስት ቀናት የሚቆየው ኮንፍረንስ በወቅታዊ የሀገራዊና ክልላዊ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ አመራሩ “የጋራ መግባባት ላይ እንዲደርስ እና የስራ ክፍፍል እንዲያደርግ የተጠራ ነው” ተብሏል።

በደቡብ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ቅጽር ግቢ በተጀመረው በዚህ ክልላዊ ኮንፍረንስ ላይ የደቡብ ክልል ቢሮዎች ኃላፊዎች እና ምክትሎቻቸው፣ የዞን እና የልዩ ወረዳ ከፍተኛ አመራሮች ተሳታፊዎች ናቸው። ከብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት የተላኩ ተወካዮችም ኮንፍረንሱን እየተካፈሉ ይገኛሉ። 

ከኮንፍረንሱ አስቀድሞ የደቡብ ክልል የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች ለስብሰባ ተቀምጠው እንደነበር ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በሃዋሳ በሚገኘው የፓርቲው ጽህፈት ቤት የተካሄደው ይህ ስብሰባ ከሐሙስ ሐምሌ 9፤ 2012 ጀምሮ ለሶስት ቀናት የቆየ እንደነበርም አስረድተዋል። 

በዛሬው ኮንፍረንስ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የደቡብ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ ኮንፍረንሱ ሶስት መሰረታዊ ግቦች እንዳሉት ጠቁመዋል። የመጀመሪያው እና ዋናው ግብ በአመራሩ መካከል “የሃሳብ እና የተግባር አንድነት” መፍጠር መሆኑንም አንስተዋል። 

“የአመራር አሃዳችን የህዝባችንን ጥያቄ በፓርቲ መሪነት እንደሚመልስ፤ እንዲሁም ደግሞ ሰላሙን፣ ልማቱን እና ዲሞክራሲውን እውን እንደሚያደርግ በዚህ በሁለት ቀናት ቆይታችን ተግባብተን መውጣት ያስፈልጋል” ሲሉ አቶ ጥላሁን ለኮንፍረንሱ ተሳታፊዎች ተናግረዋል። 

የደቡብ ክልልን ፖለቲካ በቅርበት የሚከታተሉ ታዛቢዎች በክልሉ በየጊዜው የሚነሱ የአደረጃጀት ጥያቄዎች በፈጠሯቸው ችግሮች ምክንያት፤ የክልሉ መንግስት ለሁለት ዓመት ያህል መደበኛ ስራዎችን በአግባቡ ለመከወን ሲቸገር መቆየቱን ይናገራሉ። በደቡብ ክልል ካሉ ዞኖች መካከል አስሩ በዞን ምክር ቤቶቻቸው ያጸደቁትን በክልል የመደራጀት ጥያቄ ለክልሉ ምክር ቤት ያስገቡት ከዓመት በፊት ነበር። የክልልነት ጥያቄው ባለፉት ጥቂት ወራት ወደ ሌሎች ዞኖችም ተዛምቷል። 

ከመሰል ጥያቄዎች ጀርባ የየአካባቢው አመራሮች መኖራቸው፤ ክልሉን በሚያስተዳድረው ፓርቲ ደረጃ “የዓላማም ሆነ የተግባር አንድነት እንደሌለ” አመላካች መሆኑን የፖለቲካ ታዛቢዎቹ ያስረዳሉ። የክልሉን አመራሮች ከሳምንት በፊት በጽህፈት ቤታቸው የሰበሰቡት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድም የክልልነት ጥያቄውን የሚያራግቡት የየአካባቢው አመራሮች መሆናቸውን በመጥቀስ ወቀሳ ሰንዝረዋል።

“ራሱ አመራሩ ‘እኛ አይደለንም፤ የህዝብ ጥያቄ ነው’ እያለ ህዝቡን ወደከፋ ችግር የሚወስድበት ሁኔታ ታይቷል” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተችተዋል። የአመራሮቹን አካሄድ “ራስ ለማንገስ የሚደረግ ሩጫ” በማለትም ጠርተውታል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ስብሰባ ከማካሄዳቸው ቀናት አስቀድሞ በተወካዮች ምክር ቤት በነበራቸው የጥያቄ እና መልስ ቆይታም “ከሁለት ቤት መብላት የሚፈልጉ” ያሏቸውን የክልሉን አመራሮች ወርፈዋል። 

“እዚህም እዚያም መርገጥ አይቻልም። የለውጥ አደናቃፊ መሳሪያ መሆን አይፈቀድም። ለለውጥ አደናቃፊ ኃይል መጋለቢያ መሆን አይቻልም”

አቶ ጥላሁን ከበደ- የደቡብ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ

በዛሬው ኮንፍረንስ መክፈቻ ላይ የደቡብ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ አባባል ጋር ተመሳሳይ ይዘት ያለው አገላለጽ ተጠቅመዋል። “እዚህም እዚያም መርገጥ አይቻልም። የለውጥ አደናቃፊ መሳሪያ መሆን አይፈቀድም። ለለውጥ አደናቃፊ ኃይል መጋለቢያ መሆን አይቻልም” ሲሉ አቶ ጥላሁን የኮንፍረንሱን ተሳታፊዎች አስጠንቅቀዋል።

በደቡብ ክልል ያሉ የተወሰኑ አመራሮች “አውቀውም ሆነ ሳያውቁ፤ ለውጡን የመቀልበስ አጀንዳ ያነገቡ ሃይሎችን እያስተናገዱ ይገኛሉ” ያሉት የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ይህ አካሄድ “መቆም ያለበት ነው” ሲሉ ለተሳታፊዎቹ  ተናግረዋል። አቶ ጥላሁን “ስርዓቱን ለመቀልበስ እያሴሩ ነው” ካሏቸው ኃይሎች ውስጥ በግልጽ ማንነቱን ጠቅሰው የወነጀሉት የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ድርጅትን ነው። ኃላፊው ህወሓትን “የሴራ ፖለቲካ፤ የብጥብጥ እና የሁከት ፖለቲካ ባለቤት እና ዋና ጠንሳሽ” ሲሉ ጠርተውታል።

ህወሓት በደቡብ ክልል ውስጥ የሚያከናውናቸው “የሴራ ተግባራት አሉ” ያሉት የክልሉ የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ለዚህ ማሳያ ያሉትን ጠቅሰዋል። ድርጅቱ በክልሉ “ኢ-መደበኛ አደረጃጀትን” በመጠቀም ስራዎችን እንደሚሰራ የተናገሩት አቶ ጥላሁን “የተለያዩ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን በፌደራሊስት ሃይሎች ስም እየጠሩ፣ እየጠበቁ፣ አቅም እያስታጠቁ፣ ከፍተኛ የህቡዕ ስራ ያከናውናሉ” ሲሉም ወንጅለዋል። 

“የሕወሓትን ሴራ ሀሰታቸውን፣ ባህሪያቸውን፣ አቅማቸውን፣ ገብተው የሚሰሩበት ስልታቸውን፣ በየአካባቢያቸው ያለውን እንቅስቃሴያቸውን በደንብ አውቀን መታገል፣ ህዝቡ እንዲያውቅ ማድረግ የሚያስችል ስራ መስራት አለብን”

አቶ ጥላሁን ከበደ- የደቡብ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ

ዛሬ የተጀመረው ኮንፍረንስ አንደኛው ግብ አመራሩ “የህወሓትን ሴራ በደንብ እንዲረዳ ማድረግ” መሆኑን ኃላፊው ገልጸዋል። “የሕወሓትን ሴራ ሀሰታቸውን፣ ባህሪያቸውን፣ አቅማቸውን፣ ገብተው የሚሰሩበት ስልታቸውን፣ በየአካባቢያቸው ያለውን እንቅስቃሴያቸውን በደንብ አውቀን መታገል፣ ህዝቡ እንዲያውቅ ማድረግ የሚያስችል ስራ መስራት አለብን” ሲሉ ለተሰብሳቢው አስገንዝበዋል።  

“ከፊት ለፊት ባለው ጊዜያት እጅግ በጣም በርካታ ፈተናዎች አሉ፤ ስኬቶችም አሉ፤ ፈተናዎችም ይገጥሙናል። እነኚህን ፈተናዎች መቋቋም የምንችለው ከፍተኛ የሆነ ህዝባዊ ንቅናቄ ስንፈጥር ነው፤ ህዝባችንን ከጎናችን ስናሰልፍ ነው” ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።

የደቡብ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት እስከ መጪው መስከረም ወር ድረስ ባለው ጊዜ ሊሰሩ የሚገቡ ጉዳዮችን ለይቶ በሰነድ ያዘጋጀ ሲሆን ይህንን ሰነድም ለስብሰባው ተሳታፊዎች አሰራጭቷል። ሰነዱ “የቀሪ ጊዜያት የፓርቲ እና የመንግስት እቅዶች የሰፈሩበት ነው” ተብሏል። በዚህ ሰነድ ላይ የተመሰረተ “የስራ ክፍፍል” ማድረግ የኮንፍረሱ ሶስተኛ ግብ መሆኑም በዛሬው ስብሰባ ላይ ተጠቁሟል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)