የOMN ጋዜጠኞች የፍርድ ቤት ውሎ

በተስፋለም ወልደየስ

ፖሊስ በኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ (OMN) የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋዜጠኞች እና ሰራተኞች ላይ ያቀረበው ተጨማሪ የምርምራ ጊዜ በፍርድ ቤት ተፈቀደለት። የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች ያቀረቡት የዋስትና መብት ጥያቄም ውድቅ ተደርጓል።   

የምርምራ ጊዜውን የፈቀደው እና የዋስትና መብቱን የከለከለው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ነው። ፍርድ ቤቱ ባለፈው ቅዳሜ ሐምሌ 11፤ 2012 በዋለው ችሎት ከOMN ጋዜጠኛ መለሰ ድሪብሳ ጋር ለሁለተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት የቀረቡ አራት ተጠርጣሪዎችን ጉዳይ እና ባለፈው ሳምንት በቁጥጥር ስር የዋለው ሌላኛው የጋዜጠኛ ጉዮ ዋሪዮ ጉዳዩን መመልከቱን ከጠበቆቻቸው አንዱ የሆኑት አቶ ሚልኪያስ ቡልቻ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

ከጋዜጠኛ መለሰ ጋር በአንድ መዝገብ ከቀረቡት ውስጥ ሁለቱ በOMN የቴሌቪዥን ጣቢያ በሹፍርና እና ጥበቃ የሚያገለግሉ ግለሰቦች መሆናቸውን ጠበቃው ገልጸዋል። በፖስፖርት ስሙ ኮሊንስ ኦሴሞ ተብሎ የሚጠራው ኬንያዊ ጋዜጠኛ ያሲን ጂማ እና በ“አቶ ጃዋር መሐመድ ቤት የሚኖሩ ናቸው” የተባሉት አቶ ሀሰን ጅማ የተባሉ ግለሰብም በተመሳሳይ መዝገብ መካተታቸውንም አክለዋል። 

ፖሊስ እነ መለሰ ድሪብሳን “ጠርጥሬያችኋለሁ” በሚል ለችሎት ያሰማው የወንጀል ዝርዝር በእነ ጃዋር መሐመድ ላይ ከቀረበው ጋር ተመሳሳይ መሆኑን ጠበቃው አስረድተዋል። ግለሰቦቹ የተጠረጠሩት “የድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን አስክሬን በጉልበት ቀምቶ ወደ አዲስ አበባ በማስመለስ፣ በባለስልጣናት ላይ የመግደል ሙከራ በማድረግ፣ ግጭት በማስነሳት እና በብሔሮች መካከል ጥል እንዲነሳ በማድረግ” መሆኑን ጠበቃው አብራርተዋል። 

ተጠርጣሪዎቹ ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት በቀረቡ ወቅት ችሎቱ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ፈቅዶ የነበረ ሲሆን፤ መርማሪ ቡድኑ በዚህ ጊዜ ያከናወናቸውን ተግባራት በቅዳሜው የችሎት ውሎ አቅርቧል። መርማሪ ቡድኑ በእነዚህ ጊዜያት “የተጠርጣሪዎቹን ቃል መቀበሉን እና የ34 ምስክሮችን ቃል መስማቱን” ለችሎት ማሳወቁን ገልጾ 14 ተጨማሪ የምርመራ ቀናት መጠየቁን አቶ ሚልኪያስ ጠቁመዋል።    

ፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ የጠየቀው የተጠርጣሪዎቹ “የሞባይል ስልኮች ላይ እያደረገ ለሚገኘው ምርመራ፣ ሌሎች ግብረ አበሮቻቸውን ለመያዝ፣ የደረሰውን ጉዳት መጠን ለማጣራት” በሚል እንደሆነ ጠበቃው ዘርዝረዋል። የመርማሪ ቡድኑን ጥያቄ የተመለከተው ፍርድ ቤቱ የተጠየቀውን 14 ቀናት ወደ 10 ቀንሶ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ መፍቀዱን አክለው ገልጸዋል። በዚህ መሰረት ተጠርጣሪዎቹ በቀጣይ ችሎት የሚቀርቡት ሐምሌ 21፤ 2012 ይሆናል። 

“ባለው የወንጀል ህግ መሰረት ‘አንድ ሰው ወንጀል ሰርቷል ተብሎ ከተጠረጠረ የፈጸመው ወንጀል በግሉ ተሳትፎ መገለጽ አለበት እንጂ በደፈናው መጠርጠር የለበትም’ ብለን ስናነሳ ፍርድ ቤቱም በዚህ ላይ አቅጣጫ ሰጥቷል”

ጠበቃ ሚልኪያስ ቡልቻ

ፍርድ ቤቱ ከዚህም ባሻገር በተጠርጣሪ ጠበቆች የቀረበውን አቤቱታ ተቀብሎ ትእዛዝ መስጠቱን ጠበቃው ተናግረዋል። በቅዳሜው ችሎት የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች በፖሊስ የቀረበው የወንጀል ዝርዝር “እከሌ ይህን አደረገ፣ የእከሌ ወንጀል ተሳትፎ ይሄ ነው” በሚል “ተነጣጥሎ” አለመቅረቡን በማንሳት ተከራክረዋል። 

“ባለው የወንጀል ህግ መሰረት ‘አንድ ሰው ወንጀል ሰርቷል ተብሎ ከተጠረጠረ የፈጸመው ወንጀል በግሉ ተሳትፎ መገለጽ አለበት እንጂ በደፈናው መጠርጠር የለበትም’ ብለን ስናነሳ ፍርድ ቤቱም በዚህ ላይ አቅጣጫ ሰጥቷል። የእያንዳንዱ ተጠርጣሪ የተሳትፎ ደረጃው በህግ አግባብ እንድታቀርቡ ብሎ ለመርማሪዎቹ አሳውቋል” ሲሉ ጠበቃ ሚልኪያስ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

ፍርድ ቤቱ በዚያው የችሎት ውሎ የተመለከተው ሌላው ጉዳይ፤ ድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ከመገደሉ ከአንድ ሳምንት በፊት ከOMN የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ያደረገውን ቃለ መጠየቅ ያካሄደው፤ ጋዜጠኛ ጉዮ ዋሪዮ ላይ የተጠየቀውን የምርምራ ጊዜን ነው።  በጉዮ ላይ ፖሊስ ያቀረባቸው የወንጀል ዝርዝሮች “በOMN ላይ ሀሰተኛ መረጃን በማሰራጨት፣ ብሔርን ከብሔር ጋር የሚያጋጭ ዘገባ በማዘጋጀት እና በማሰራጨት እና በዚያ ምክንያት ሁከት እና ግርግር እንዲፈጠር፣ ያንን ተከትሎም ህይወት እንዲጠፋ እና ንብረት እንዲወድም አስተዋጽኦ አድርጓል” የሚል እንደሆነ ጠበቃ ሚልኪያስ ገልጸዋል። 

ባለፈው ቅዳሜ ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት በቀረበው ጉዮ ላይ ፖሊስ ምርመራ ለማድረግ 14 ቀናት የጠየቀ ሲሆን ፍርድ ቤቱም ጥያቄው ተቀብሎ ለሐምሌ 24 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። ጉዮ “ሁለት ቀን ምግብ እንዳልበላ እና በረሃብ እንደተጎዳ” ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ ማቅረቡን ጠበቃው አስረድተዋል። 

ጋዜጠኛው “በተያዘበት ቀን ምግብ አለመብላቱን እና ምንም ነገር ሳይቀምስ ውሎ ማደሩን፤ በቀጣይ ቀንም የቀረበለትን ደረቅ ዳቦ እና ሻይ መመገብ እንዳልቻለ” ለችሎቱ መናገሩን ገልጸዋል። ቤተሰብ እንዲጎበኘው ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥለትም መጠየቁንም አክለዋል። አቤቱታውን ያደመጠው ፍርድ ቤቱ “በቂ ምግብ እንዲሰጠው እና ከቤተሰብ ጋርም እንዲገናኝ ትዕዛዝ ሰጥቷል” ብለዋል ጠበቃው። 

በእነ ጋዜጠኛ መለሰ በኩል ደግሞ ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ያለባቸውን ስጋት ለፍርድ ቤቱ ማሰማታቸውን አቶ ሚልኪያስ ተናግረዋል። በሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ በእስር ላይ የሚገኙት ተጠርጣሪዎቹ “ያልተመረመሩ አዳዲስ ተጠርጣሪዎች በየጊዜው ተይዘው እንደሚገቡ” በማንሳት “በበሽታው እንያዛለን” የሚል ስጋት እንደገባቸው ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል። ከዚህም በተጨማሪ ሳኒታይዘር እና ሳሙና እንደሌላቸው በመጥቀስ “ለአደጋ ተጋልጠናል” ሲሉ አቤቱታቸውን ማቅረባቸውን ጠበቃቸው ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)