የብርጋዴየር ጄነራል ውበቱ ፀጋዬ መጽሐፍ በኢትዮጵያ ታትሞ ለንባብ በቃ

በተስፋለም ወልደየስ

በኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት ውስጥ ለ32 ዓመታት ያገለገሉት ብርጋዴየር ጄነራል ውበቱ ፀጋዬ የጻፉት መጽሐፍ በኢትዮጵያ ታትሞ ለንባብ በቃ። መጽሐፉ የዛሬ ሰባት ዓመት ግድም በአሜሪካ ታትሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲሰራጭ ቢቆይም ለኢትዮጵያ ገበያ ሲቀርብ የመጀመሪያው ነው። 

“ሁሉም ነገር ወደ ሰሜን ጦር ግንባር” በሚል ርዕስ የተዘጋጀው የጄነራሉ መጽሐፍ በኢትዮጵያ ታትሞ መሰራጨት የጀመረው ካለፈው ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ መሆኑን ጃፋር የመጽሐፍት አከፋፋይ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቋል። መጽሐፉ በኢትዮጵያ እንዲታተም ያደረጉት የጄነራሉ ልጅ አቶ እስክንድር ውበቱ መሆናቸውም ተገልጿል። 

በሰባት መቶ ስምንት ገጾች የተዘጋጀው ይሄው መጽሐፍ ይበልጥ ትኩረቱን ያደረገው ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል በነበረችበት ወቅት በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሄደው ጦርነት ላይ ነው። መጽሐፉ ከ1967 ዓ.ም. እስከ 1981 ዓ.ም የተደረጉ ታሪካዊ የወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን እና ዘመቻዎችን በፎቶዎች፣ በካርታዎች እና ደብዳቤዎች አስደግፎ ለንባብ አቅርቧል። 

ነዋሪነታቸው በአሜሪካን ሀገረ የሆነው ብርጋዴየር ጄነራል ውበቱ መጽሐፉን ለማዘጋጀት 21 ዓመት እንደፈጀባቸው በመጽሀፉ መግቢያ ላይ ገልጸዋል። “ይህን መጽሐፍ ወይም ማስታወሻ በጻፍኩበት ወቅት ለቅንብሩ የረዱኝ ጭብጥ ነገሮች ቢኖሩ፤ በጦር ሜዳ በተሳተፍንባቸው ልዩ ልዩ አውደ ውጊያዎች ጊዜ በተገኘው አጋጣሚ፤ ዘወትር ከኪሴ በማትለየው የጦር ሜዳ ማስታወሻ ደብተሬ ላይ ዘግቤ ባስቀመጥኩት ማስረጃ በመመርኮዝ ነው” ሲሉም የመጽሐፉ መረጃዎች የመነጩት ከየት እንደሆነ ጠቁመዋል።

በደርግ ጊዜ ከነበረው የኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት ጋር በአዛዥነት እና በዘመቻ መኮንነት ለረጅም ዓመታት አብረው የቆዩት ብርጋዴየር ጄነራል ውበቱ የሰራዊቱ ታሪክ “በሚገባ አልተነገረም” የሚል እምነታቸውን በመጽሐፋቸው አንጸባርቀዋል። የጦር ሰራዊቱ ተጋድሎ በተብራራ ሁኔታ ባለመቅረቡም “ሰራዊቱ እንዳልተዋጋ እና አገር እንዳልጠበቀ ሆኖ በአንዳንድ ወገኖች ግንዛቤ መወሰዱም ይታያል” በማለት ቁጭታቸውን በመጽሐፉ መግቢያ ላይ ገልጸዋል።   

“ይህን መጽሐፍ ለማዘጋጀት የተገደድኩበት ዐብይ ምክንያት በአንደኛ ደረጃ ሰራዊቱ የተሰጠውን ግዳጅ ከነበረው አስቸጋሪ ማለትም ከሰው ሰራሽም ሆነ የተፈጥሮ መሰናክልን እየተቋቋመ እንዴት አድርጎ በሚችለው አቅሙ ሁሉ ተተኪ የሌላትን ሕይወቱን በመክፈል የአንድነቱን ተልዕኮ እንደፈጸመ ለማስረዳት እንጂ በስራ ላይ ለተሰሩት ስህተቶች ወይም ለተሰነዘሩት ትችቶች እና አመለካከቶች ሁሉ ለመከላከልና ለማስተባበል አይደለም” ሲሉም የመጽሐፉን አላማ አብራርተዋል።        

“ሰራዊቱ የተሰጠውን ግዳጅ ከነበረው አስቸጋሪ ማለትም ከሰው ሰራሽም ሆነ የተፈጥሮ መሰናክልን እየተቋቋመ እንዴት አድርጎ በሚችለው አቅሙ ሁሉ ተተኪ የሌላትን ሕይወቱን በመክፈል የአንድነቱን ተልዕኮ እንደፈጸመ ለማስረዳት ነው”

ብርጋዴየር ጄነራል ውበቱ ፀጋዬ

ብርጋዴየር ጄነራል ውበቱ በደርግ ዘመነ መንግስት በኤርትራ ክፍለ ሀገር ተሰማርቶ የነበረውን የሁለተኛ አብዮታዊ ሰራዊት በአዛዥነት የመሩ ነበሩ። ወደ ሰራዊት አዛዥነታቸው ከመምጣታቸው በፊት በኤርትራ ጦርነት ስመ ገናና የነበረው የናደው ዕዝ አዛዥ ሆነው ለአምስት ዓመት አገልግለዋል። ደርግ ከመውደቁ በፊት በነበሩ ጥቂት ዓመታት በፕሬዝዳንት መንግስቱ ኃይለማርያም ቢሮ በወታደራዊ አማካሪነት እና በብሔራዊ ውትድርና የሲቪል መከላከያ መምሪያ ኃላፊነትም ሰርተዋል።

በግንቦት 1981 ዓ. ም. ተሞክሮ በነበረው መፈንቅለ መንግስት ተሳትፎ ተጠርጥረው ለሁለት ዓመት በታላቁ ቤተ መንግስት የታሰሩት ብርጋዴየር ጄነራል ውበቱ ኢህአዴግ አዲስ አበባን ከመቆጣጠሩ አስቀድሞ ከእስር ተለቅቀዋል። ጄነራሉ በኢህአዴግ የስልጣን ዘመን እንደ ጓዶቻቸው በእስር ከማሳለፍም ተርፈዋል። 

ላለፉት 16 ዓመታት ኑሯቸውን በአሜሪካ ያደረጉት የጦር አዛዡ በ79 ዓመታቸውም ከውትድርና ሙያቸው ጋር ተቀራራቢነት ባለው ዘርፍ በስራ ላይ እንደሚገኙ ልጃቸው አቶ እስክንድር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ለአጭር ጊዜ ጉብኝት ባለፈው ዓመት ወደ ኢትዮጵያ ጎራ ብለው የነበሩት ጄነራሉ ወደ ሀገራቸው ጠቅለልው የመመለስ ሀሳብ እንዳላቸውም ልጃቸው ጨምረው ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)