ጅቡቲያዊው የጦር አውሮፕላን አብራሪ – ከኢትዮጵያ እስከ ጋቦዴ ወህኒ ቤት

ከኢትዮጵያ ተላልፎ የተሰጠው ጂቡቲያዊው የአየር ኃይል አብራሪ ፉአድ ዩሱፍ አሊ፤ ለሁለተኛ ጊዜ በረሃብ አድማ ላይ መሆኑን ጠበቃው ዛሬ  ሐሙስ ሐምሌ 16፤ 2012 ለፈረንሳይ ዓለም አቀፍ ሬድዮ (RFI) ተናግረዋል። አብራሪው ጤንነቱ ቢቃወስም ምግብ ለመመገብ አሻፈረኝ ማለቱን ገልጸዋል። በሆስፒታል የሚደረግለትን ህክምናም “ልመረዝ እችላለሁ” በሚል ስጋት አለመቀበሉንም ለሬድዮ ጣቢያው አስረድተዋል። 

የቀድሞው የጅቡቲ አየር ሃይል ባልደረባ ጉዳይ ከሶስት ወራት በፊት በጅቡቲ በከፍተኛ ሁኔታ ሲያነጋግር የሰነበተ ሲሆን በሀገሪቱ እምብዛም ለማይታዩት የተቃውሞ ሰልፎች መቀስቀስም መንስኤ ሆኖ ነበር። አብራሪው በአንድ ወህኒ ቤት ውስጥ ሆኖ የቀረጸው የ12 ደቂቃ ተኩል ተንቀሳቃሽ ምስል በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ከተለቀቀ በኋላ ጅቡቲ በወቅቱ ተደጋጋሚ የተቃውሞ ሰልፎችን አስተናግዳለች። 

ፉአድ ለእስር የተዳረገው በተለይም በአየር ሃይሉ አዛዥ ደረሰብኝ ያለውን የስነ ልቦና ጫና እና ትንኮሳ ይፋ በማድረጉ ነበር። አብራሪው ወደ ወህኒ ከመውረዱ በፊት ወደ ኢትዮጵያ ኮብልሎ ጥገኝነት ለመጠየቅ ሙከራ ማድረጉን የቅርብ ሰዎቹ ይናገራሉ። የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደሯ” ሐይማኖት አሸናፊ ባለፈው መጋቢት ወር የጀመረውን የአብራሪውን የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች፣ በኢትዮጵያ የነበረውን ቆይታ እና ለጅቡቲ ተላልፎ የተሰጠበትን ሂደት ፈትሻለች።  

በጅቡቲ አየር ሃይል አብራሪ የሆነው ፉአድ ዩሱፍ አሊ በሀገሬው ሰዎች ዘንድ ተዘውታሪ የሆነውን መልዕክት ማስተላለፊያ ዘዴ ተጠቅሞ ከአንድም ሁለቴ ያሰራጫቸው ቪዲዮዎች ዝምታ ያረበበትን የጀቡቲ ፖለቲካ የናጡ ነበሩ። መጋቢት 18፤ 2012 በማህበራዊ መገናኛ አውታሮች የተሰራጨው የመጀመሪያው ቪዲዮ የስድስት ደቂቃ ተኩል ርዝመት ብቻ ቢኖረውም፤ በውስጡ የተነሱ ሀሳቦች ግን ፉአድን በመላው ጅቡቲ ታድኖ እንዲታሰር ትዕዛዝ እንዲወጣበት ምክንያት ሆኗል።  

ፉአድ ይህን ቪዲዮ የቀረጸው የጅቡቲ አየር ሃይል ንብረት በሆነ አውሮፕላን ኮክፒት ውስጥ ተቀምጦ፣ ሙሉ የደንብ ልብሱን ከእነማዕረጉ አድርጎ ነው። አብራሪው በዚህ ቪዲዮው ላይ በጀቡቲ አይነኬ ከሚባሉ ሰዎች አንዱ የሆኑትን፤ የፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኦማር ጉሌህ የወንድም ልጅ፤ ዋሲብ ሙሳን በሶማሊኛ ቋንቋ ሲያወግዝ ይደመጣል። ጀቡቲያውያንም የሀገሪቱ የአየር ሃይል አዛዥ የሆኑትን ዋሲብ ሙሳን እንዲቃወሙ ይጠይቃል። 

የፉአድ ጥሪ በጅቡቲያውያን የማህበራዊ መገናኛ አውታር ተጠቃሚዎች ዘንድ በፍጥነት ነበር የተዛመተው። አብራሪው ቪዲዮውን ለዕይታ ባበቃ በሰዓታት ውስጥ፣ የጭነት መኪናን በመጠቀም ድንበር ተሻግሮ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን በጅቡቲ የሚገኙ ቤተሰቦቹ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ይህንን እውነታ ያላወቁት የጅቡቲ ባለስልጣናት ፉአድን በመላው ጅቡቲ እንዲታሰስ ቢያደርጉም ሊያገኙት አለመቻላቸውን ቤተሰቦቹ ይገልጻሉ። በዚህም ምክንያት ባለስልጣናቱ ባለቤቱን፣ የፉአድን ልጆች እንዲሁም ወንድም እና እህቱን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን ባለቤቱ ሰሚራ አብዲ ጀማፉር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድታለች።  

የአብራሪው ተቃውሞ መነሻ 

የሰላሳ አራት ዓመቱ ፉአድ የጅቡቲ አየር ሃይልን የተቀላቀለው የልጅነት የአብራሪነት ምኞቱን እውን ለማድረግ ነበር። በተወለደበት የጅቡቲ ዋና ከተማ ጅቡቲ እስከ ዩኒቨርስቲ ድረስ ያለውን ትምህርት ቢያጠናቅቅም የጅቡቲ አየር ሃይል አብራሪዎችን ለመመልመል ማስታወቂያ ሲያወጣ የሀገሪቱን ሰራዊት ለመቀላቀል አይኑን አላሸም።

የአየር ሃይሉን መግቢያ ፈተና ከወሰዱ ተወዳዳሪዎች፤ ምርጥ አራት ውስጥ በመግባቱ በሞሮኮ ለሚካሄደው የአብራሪነት ስልጠና ተመረጠ። ወደ ሞሮኮ  ሮያል የአየር ሃይል ማሰልጠኛ የተጓዘው እንደውም ከጅቡቲው ፕሬዘዳንት ኢስማኤል ኦማር ጉሌህ ጋር እንደነበር ቤተሰቦቹ በኩራት ያስታውሳሉ። ስልጠናውን በ24 ዓመቱ በከፍተኛ ማዕረግ ተመራቂነት የጨረሰው ፉአድ ወደ ጅቡቲ ከተመለሰ በኋላ ነገሮች እንዳሰበው አልሆኑለትም። 

በጅቡቲ አየር ሃይል በተለማማጅ አብራሪነት ስራውን የጀመረው ፉአድ በቀጣዩቹ አስር አመታት ወደ ሙሉ ካፒቴንነትም ሆነ ወደ ረዳት አብራሪነት ሳይሸጋገር መቆየቱ ክፉኛ እንደጎዳው የቅርብ ሰዎቹ ያስረዳሉ።

“ለ10 ዓመታት ያለ መታከት እና ራሱን ጥሎ ቢሰራም፤ ከእርሱ ያነሰ ልምድ ያላቸው ባልደረቦቹ እድገት ሲያገኙ እርሱ ግን ምንም አይነት እድገት ያለማግኘቱ ከፍተኛ ጭንቀት እና ብስጭት ውስጥ ከቶት ነበር” ሲሉ ታላቅ ወንድሙ ኦማር አሊ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። “ፉአድ በአየር ሃይሉ ውስጥ በአጠቃላይ ከ400 ሰዓታት በላይ በማብረር ቢያገለግልም፤ በአየር ሃይሉ አዛዥ ዋሲብ ሙሳ ካሊኔሊህዊል ይገለል ነበር” ሲሉ መለስ ብለው ያስታውሳሉ። 

በጅቡቲ አየር ሃይል ያለው እውነታ በሞሮኮ ከወሰደው ትምህርት እና ከሰለጠነባቸው የሰራዊቱ መርሆዎች የራቀ መሆኑን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተረዳ የመጣው ፉአድ በመጨረሻ ለወሰደው እርምጃ መንሳኤ መሆኑን ወንድሙ ይገልጻሉ። “ያሰበው አይነት የስራ ህይወት እንደማይኖረው መረዳቱ ለተስፋ መቁረጥ ዳርጎታል” ይላሉ የነበረበትን የስነ ልቦና ሁኔታ ሲያስረዱ።  

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው ሶስት የፉአድ የቅርብ ሰዎች እንደሚሉት፤ አብራሪው እንደሌሎች ባልደረቦቹ ነገሩን ትቶ ከማለፍ ይልቅ ፊት ለፊት መጋፈጥን ይመርጥ ነበር። መብቶቹን በተደጋጋሚ ለመጠየቅም የመከላከያ ሰራዊቱ ጠቅላይ አዛዥ ወደሆኑት ፕሬዘዳንት ጉሌህ ዘንድ ጭምር አቤቱታውን ያሰማ እንደነበር ይገልጻሉ።

“ይህ እርምጃው ጎዳው እንጂ አልጠቀመውም። በፍጥነት በሰራዊቱ ውስጥ መገለል ይደርስበት ጀመረ። በተጨማሪም በተደጋጋሚ ያጠቁት እና የተለያየ ቅጣቶችንም ይጥሉበት ጀመሩ። የፉአድ አካሄድ አድሎአዊ ለሆነው የአየር ሃይሉ አመራር አደጋ በመደቀኑ ሊወገድ የሚገባው ሰው አደረገው” ሲሉ ኑሯቸውን በካናዳ ያደረጉት ታላቅ ወንድሙ ያስረዳሉ።

በኢትዮጵያ ቆይታው ምን ተከሰተ?

በጅቡቲ አየር ሃይል ደረሰብኝ ባለው በደል እና መገለል የተማረረው ፉአድ ወደ ኢትዮጵያ ከተሰደደ በኋላ በዚያም የሻተውን ሰላም አላገኘም። በኢትዮጵያ በነበረው አጭር ቆይታ እንዳሰበው የፖለቲካ ጥገኝነት ማግኘት አልቻለም። ይልቁንም ከአገሩ ከወጣ ከሁለት ሳምንት በኋላ ረቡዕ መጋቢት 30፣ 2012 ያልጠበቀው ነገር ተከሰተ። 

በዕለቱ ወደ አዲስ አበባ ከገባ ጥቂት ቀናት የሆኑት ፉአድ ከውጪ አገር በሃዋላ የተላከለትን ገንዘብ ለመቀበል ወደ ባንክ ቤት አምርቷል። ከቦታ ቦታ ለመጓጓዝ በተጠቀመበት ታክሲ ውስጥ ሁለት ተጨማሪ ሰዎች አሉ። አንደኛው እንደ እርሱ ሁሉ ከጅቡቲ ኮብልለው አዲስ አበባ የመጡ ባርካት አብዱል-ዋሂብ የተባሉ ግለሰብ ናቸው። ከእርሳቸው ጋርም አንዲት ሴት ነበረች። 

ፉአድ ጉዳዩን ፈጻጽሞ ወደጫነችው ታክሲ ሲመለስም ሁሉ ነገር ሰላም ነበር። ታክሲዋ በጉዞ ላይ ሳለች ግን የኢትዮጵያ የጸጥታ ኃይሎች አስቁመው እርሱን እና ሁለቱን ተሳፋሪዎች በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን አብረውት የነበሩት ባርካት ይናገራሉ። ባርካት እና አብራቸው የነበረች ሴት ከቆይታ በኋላ ሲለቀቁ ፉአድ ግን ለሁለት ቀናት በጸጥታ ኃይሎቹ ተይዞ መቆየቱን ቤተሰቦቹ ይገልጻሉ።

ኦማር ወንድማቸው በማቆያ ውስጥ ሁለት ምሽቶችን ማሳለፉን እና የያዙት የጸጥታ ኃይሎችም ወደ ፍርድ ቤት እንዳላቀረቡት ያስረዳሉ። ረቡዕ የተያዘው ፉአድ “አርብ ዕለት ወደ አየር ማረፊያ ተወስዶ፤ ለጅቡቲ ብሔራዊ የደህንነት አገልግሎት ተላልፎ ተሰጥቷል” ይላሉ። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ከአንድ አለማቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ያገኘችው መረጃ ይህንኑ የኦማርን ገለጻ አረጋግጧል። ፉአድ ለሁለት ቀናት በኢትዮጵያ የቆየው “አስፈላጊ የጉዞ ሰነዶች እስኪሰናዱ እንደነበር” መረጃው አመልክቷል።  

የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት አያያዝ ምን ይመስል ነበር?

ጅቡቲያዊው አብራሪ በቁጥጥር ስር ከዋለበት ዕለት ጀምሮ የደረሰበትን ለማወቅ የጥገኝነት ጉዳዩን ለመከታተል የተቀጠሩት ጠበቃው ኢዘዲን ሲያፈላልጉት ቆይተዋል። እንደ እርሳቸው ገለጻ ደንበኛቸውን በፌደራል ፖሊስም ሆነ በአዲስ አበባ ፖሊስ ማረፊያ ቤቶች ውስጥ ቢያፈላልጉትም አላገኙትም። 

ከዚህ በተጨማሪም ፉአድ ተያዘ በተባለበት ቀንም ሆነ ከዚያ በኋላ ባሉት ሶስት ሳምንታት ውስጥ በቁጥጥር ስር መዋሉንም ሆነ ወደ ጅቡቲ መተላለፉን የሚያሳይ ምንም አይነት የሰነድ ማስረጃ በኢትዮጵያ ውስጥ አላገኙም። ከዚህ ባሻገር በአዲስ አበባ በሚገኘው “ኢንተርፖል” በኩልም ጉዳያቸው አልፎ ከሆነ በሚል ማጣራት ያደረጉት ጠበቃው “ፉአድን አየሁ” የሚል ተቋም አለማግኘታቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።

ጠበቃው በሰነድ የተደገፈ መረጃ ባያገኙም በቃል ግን ደንበኛቸው የኮሮና ቫይረስ ተጠርጣሪዎች ወደሚቆዩበት ለይቶ ማቆያ መግባታቸውን መስማታቸውን እና ያንንም ተከትሎ ለ14 ቀን ያህል መጠበቃቸውን አስረድተዋል። ሆኖም ፍለጋቸው ውጤት ባለማፍራቱ ምክንያት ውላቸውን ማቋረጣቸውንም ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

የፉአድ ወንድምም የጠበቃውን ገለጻ የሚያጠናክር መረጃ ሰጥተዋል። ወንድማቸው ፉአድ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ካምፓስ ማቆያ ውስጥ የመጀመሪያውን ምሽት አንዳሳለፈ ገልፀዋል።

የጠበቃውን እና የኦማርን መረጃ ተከትሎ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ፉአድ ምናልባት “ወደ ለይቶ ማቆያ ውስጥ የገቡት ከውጪ አገር ስለገቡ ከሆነ” በሚል ለጤና ሚኒስቴር ጥያቄ አቅርባለች። ነገር ግን በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የመረጃ ቋት ውስጥ ለሁለት ቀናት ያህል ቢፈለግም በዚህ ስም የተመዘገበ ሰው አለመገኘቱን የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

ጀቡቲያዊው አብራሪ “የኢትዮጵያ የጸጥታ ኃይሎች በአክብሮት እና ያለ ምንም ጥቃት አንደያዙት” መግለጹን ከወንድማቸው እንደሰሙ ኦማር ገልጸዋል። ፉአድ እንዴት እና በየትኛው የኢትዮጵያ ተቋም በኩል ለጅቡቲ ተላልፎ እንደተሰጠ ለማወቅ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ሳምንታትን የፈጀ ማጣራት ብታደርግም እስካሁን ግልጽ መረጃ ማግኘት አልቻለችም። 

የፌደራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ምክትል አቃቤ ህግ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ ወንጀለኞቹን አሳልፎ የመስጠት ስምምነት በሁለት አገራት መካከል በማይኖርበት ጊዜ፤ ተላልፎ እንዲሰጠው የሚጠይቀው አገር ተመሳሳይ ትብብር ወደ ፊት ከተጠየቀ ለመስጠት በመስማማት፤ አለም አቀፍ ህጎችን ባከበረ አካሄድ ተላልፎ የሚሰጥበት አሰራር መኖሩን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል።

ወደ መንግስት የስራ ሃላፊነት ከመምጣታቸው በፊት በሰብአዊ መብት ማስተማር እና ምርምር ሰፊ ልምድ ያካበቱት ዶ/ር ጌዲዮን እንደሚሉት “በመደበኛው አሰራር በዚህ አሳልፎ የመስጠት ትብብር (Reciprocity) ወቅትም ከግምት ውስጥ የሚገቡ ጉዳዮች በርከት ያሉ ናቸው”። “ተላልፎ እንዲሰጥ የተፈለገው ሰው የተከሰሰው በምን ወንጀል ነው? የተከሰሰበት ነገር ኢትዮጵያም ወንጀል ነው ወይ? ከበድ ያለ ወንጀል ነው? የሚለውን ጨምሮ እንደዚህ ነገሮች ተመዝነው ነው ተላልፎ የሚሰጠው” ሲሉ ህጋዊ ሂደቱን ያብራራሉ።

“የፉአድ ጉዳይ በእኛ በኩል ቢመጣ፤ ከአቻ ተቋም በህጋዊ ወይም በዲፕሎማሲ መስመሩ በኩል ይመጣ ነበር። ነገር ግን ይህንን ጉዳይ አላስተናገድንም”

ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ- የፌደራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ምክትል አቃቤ ህግ

“አለ የተባለውን ወንጀል፤ ተፈላጊው ግለሰብ መፈፀሙን ተከትሎ መደበኛ ክስ በአገሩ መጀመሩን የሚያሳይ ማስረጃ ከሌለም፤ እንደዚህ ያለ ጥያቄ አይስተናገድም” ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል፡፡ የፉአድ ጉዳይም በተቋማቸው በኩል አልፎ እንደሆነ የሚያሳይ ምንም አይነት ማስረጃ እንደሌም ገልጸዋል። “የፉአድ ጉዳይ በእኛ በኩል ቢመጣ፤ ከአቻ ተቋም በህጋዊ ወይም በዲፕሎማሲ መስመሩ በኩል ይመጣ ነበር። ነገር ግን ይህንን ጉዳይ አላስተናገድንም” ሲሉ ተቋማቸው በነገሩ እጁ እንደሌለበት ጠቁመዋል። 

የጅቡቲውን አብራሪ ሁኔታ የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ያውቀው እንደው በ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተጠየቁት የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ መስሪያ ቤታቸው “ጉዳዩን እንዳልተከታተለ” ገልጸዋል። ተመሳሳይ ጥያቄ የቀረበለት የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት (UNHCR) ጉዳዩን በመገናኛ ብዙሃን ከመከታታል ባሻገር፤ ተቋሙ ጉዳዩን የተመለከተ ዝርዝር መረጃ እንደሌሌው ገልጿል።

“ፉአድ በኢትዮጵያ ቆይታው የጥገኝት ጥያቄ አቅርቦ እንደሆነም የማውቀው መረጃ የለም። በዚህ ጉዳይም የሚመለከተው አካል የኢትዮጵያ መንግስት በመሆኑ እሱን እንድታነጋገሩ እንመክራለን” ሲሉ የተቋሙ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ክሱት ገብረ እግዚአብሄር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በኢሜይል በሰጡት ምላሽ ላይ ጠቅሰዋል። 

የጅቡቲ መንግስት ምን አለ? 

ፉአድ ከኢትዮጵያ ወደ ሀገሩ የተወሰደው በአንድ የጅቡቲ አየር ሃይል አውሮፕላን ሲሆን ከተወሰደ ቀን ጀምሮ ለ11 ቀናት በጅቡቲ የብሔራዊ ደህንንት እስር ቤት መቆየቱን በጅቡቲ የኦማር ጠበቃ አስረድተዋል። ከዚያም በሚያዚያ 13፤ 2012 ወደ ጋቦዴ ወህኒ ቤት መሸጋገሩን እና በማግስቱ ምሽት ፍርድ ቤት መቅረቡን የፉአድ ቤተሰቦች ያብራራሉ። ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን የተመለከተው የፉአድ ጠበቃ በሌለበት እንደነበር ጠቁመዋል።

በጁቡቲ ከተማ የሚገኘው የጋቦዴ ወህኒ ቤት

የጅቡቲ ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ግንቦት 29፤ 2012 በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ፉአድ በአገር ክህደት ተጠርጥሮ ክስ እንደተመሰረተበት ተናግረዋል። “በያዝነው አመት መጋቢት ወር ውስጥ ወደ ጠላት አገር ኤርትራ አውሮፕላን ይዞ ለመጥፋት ሞክሯል” ሲሉ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ጃማ ሱሌይማን መግለጻቸውን የጅቡቲ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ በዚሁ መግለጫቸው ፉአድ ወደ ኢትዮጵያ በመሸሽ የጥገኝነት ጥያቄ ማቅረቡን አምነው፤ ኢትዮጵያ ግን ጥገኝነቱን እንዳልሰጠች አክለዋል። የኢትዮጵያ መንግስትም ፉአድን ለጅቡቲ አሳልፎ መስጠቱን አረጋግጠዋል።

ጀቡቲ እና ኢትዮጵያ በወንጀል የሚፈልጓቸውን ሰዎች አንዳቸው ለሌላቸው አሳልፎ የመስጠት የቀደመ ታሪክ አላቸው። በ1997 ዓ.ም ወደ ጅቡቲ የጠፉ ሁለት የኢትዮጵያ አየር ሃይል አብራሪዎች ለኢትዮጵያ ተላልፈው መሰጠታቸው ይታወሳል። አብራሪዎቹ ወደ ጅቡቲ የሸሹት ከአንድ ቴክኒሺያን ጋር በመሆን ነበር። በወቅቱ የጅቡቲ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ኢልሚ ቡሁ “ሁለቱ አብራሪዎቹ በገዛ ፈቃዳቸው ለኢትዮጵያ ተላልፈው ተሰጥተዋል፤ የአውሮፕላን ቴክኒሺያኑ ግን ለመመለስ ስላልፈቀደ በጅቡቲ ቆይቷል” ሲሉ ለቢቢሲ ገልፀው ነበር። 

የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት እና የአብራሪዎቹ ቤተሰቦች ግን ጥገኝነት ጠያቂዎቹ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ የተደረጉት “ያለፍቃዳቸው” መሆኑን ሞግተው ነበር። አብራሪዎቹ ወደ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ “ከአዲስ አበባ ውጪ ባለ የአየር ሃይል ጣቢያ ውስጥ በእስር እንዲቆዩ መደረጉን” የአብራሪዎቹ ቤተሰቦች በወቅቱ ለቢቢሲ አጋልጠዋል። 

ጅቡቲ እና ኢትዮጵያ እንዲህ አይነት እርምጃዎችን ሲወስዱ ቢቆዩም በወንጀል የሚፈለጉ ሰዎችን አሳልፎ ለመስጠት ሁለቱ አገራት ያደረጉት ስምምነት በኢትዮጵያ በኩል የጸደቀው ፉአድ ወደ ጅቡቲ ተላልፎ ከተሰጠ ከወር በኋላ ነው። የተወካዮች ምክር ቤት ሰኔ 18፣ 2012 ባደረገው ስብሰባ በኢትዮጵያ እና ጅቡቲ መንግስታት መካከል የተደረገውን በወንጀል ጉዳዮች የጋራ የፍትህ ትብብር እና በወንጀል የሚፈለጉ ሰዎችን አሳልፎ መስጠት ስምምነት ረቂቅ አዋጅን ያጸደቀው በሙሉ ድምጽ ነው።

ኢትዮጵያ ሕጉን ተከትላ ይሆን?

አሳልፎ መስጠትን የተመለከቱ ሕጎች የሚፈፀሙበት እና የሚተገበሩበት መንገድ በሁለት እንደሚከፈል ከ20 ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮችን የተከታተሉ፤ የዘገቡ እና በዘርፉ ሶስተኛ ዲግሪያቸውን የያዙ አንድ ባለሙያ ይናገራሉ። የመጀመሪያው መንገድ የአገር ውስጥም ሆነ አለም አቀፍ ሕጎችን ወደ ጎን በማለት ሰዎችን አሳልፎ መስጠትም ሆነ ከጎረቤት ሃገር ማምጣት መሆኑን ይገልጻሉ። “ኢትዮጵያ በጎረቤት አገር ከሚገኙ የስደተኛ ካምፖች የፖለቲካ ተቃዋሚዎችን ማምጣቷ በተግባር ያለውን ሂደት መልካም እንዳልሆነ በደንብ ያሳያል” ሲሉ ባለሙያው ያስረዳሉ። 

ሁለተኛው መንገድ መሰረታዊ የሕግ ሂደቶችን በመከተል የሚካሄድ መሆኑን የሚጠቁሙት ባለሙያው፤ መደበኛው ስነ ስርአት “አንድ ወንጀለኛ ተላልፎ ይሰጠኝ የሚል አገር የዲፕሎማሲ ሰንሰለቱን በመከተል የተላልፎ ይሰጠኝ ጥያቄ ለጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ጽህፈት ቤት በማቅረብ የሚፈፀም” እንደሆነ ያመለክታሉ። “ተላልፎ እንዲሰጥ ከተወሰነም መፈጸም ያለበት በፖሊስ ነው” ይላሉ።

“የፉአድ ጉዳይ በሁለተኛው አካሄድ የተከወነ ነው ብለን እንውሰድ። ፉአድ ቶርቸር እንደሚደርስበት ከገለጸ ተላልፎ ያለመሰጠት መብት አለው። ተላልፎ የመሰጠቱ ጥያቄ ቶርቸር እንደሚደርስበት በገለጸበት ቅፅበት መቆም ነበረበት” ሲሉ ባለሙያው ይሞግታሉ። በኢትዮጵያ ተይዞ ተላልፎ ለመሰጠት የሚፈቅዱት፤ የሽብር ወንጀልን ለመከላከል የወጣው አይነት አዋጆች እንኳን፤ የስቅይት ስጋት ካለ ተላልፎ እንዳይሰጥ እንደሚከለክሉ ያትታሉ።

“የፉአድ ተላልፎ የመሰጠት ሂደት በሕገ መንግስት እና በአለም አቀፍ ህጎች መነፅር ስንመለከተው ከእገታ አይለይም። ፖሊስን ጨምሮ ማንኛውም አካል ከሕግ ውጪ አንድን ሰው መያዝ ሕገ ወጥ እና ያልተገባ ድርጊት ነው”

የሰብአዊ መብቶች ባለሙያ

“የፉአድ ተላልፎ የመሰጠት ሂደት በሕገ መንግስት እና በአለም አቀፍ ህጎች መነፅር ስንመለከተው ከእገታ አይለይም። ፖሊስን ጨምሮ ማንኛውም አካል ከሕግ ውጪ አንድን ሰው መያዝ ሕገ ወጥ እና ያልተገባ ድርጊት ነው” ሲሉ የሰብአዊ መብቶች ባለሙያው ይቃወሙታል።

በአጠቃላይ ውሳኔው ሁለት ሕገ መንግስታዊ መብቶችን የጣሰ ሆኖ እንዳገኙት ለ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተናገሩት ባለሙያው “የመዘዋወር ነጻነትን እንዲሁም በሕግ የመዳኘት መብትን አላከበረም” ይላሉ። በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 17 እና 19 መሰረት ያለ ሕጋዊ ምክንያት ሰዎች እንዲያዙ መፈቀድ አልነበረበትም ሲሉም አጽንኦት ይሰጣሉ።

“ያለ ሕጋዊ ማብራሪያ እና ስነ ስርአቱ ከግምት ውስጥ ሳይገባ፤ ፉአድን በቁጥጥር ስር ያዋለ ፖሊስ፣ የመንግስት የሕግ ባለሙያ ወይም ማንኛውም ሰው መመርመር፤ ከስራው መባረር እና በወንጀል መጠየቅ አለበት” ሲሉ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል መወሰድ ያለበትን እርምጃ ይጠቁማሉ። “በፉአድ ላይ እየደረሰ ላለው ስቅይት ኢትዮጵያ ተጠያቂ ናት። ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ የሕግ ማዕቀፎች ሰብአዊ መብቶችን ማክበር ብቻ ሳይሆን እንድትጠብቅ ይጠበቅባታል። የስቅይት አደጋ የተጋረጠበትን ሰው አሳልፋ ስትሰጥ ይሀንን ሰብአዊ መብት የመከላከል ግዴታዋን ጥሳለች” ሲሉም ያጠቃልላሉ።

ቪዲዮ የቀሰቀሰው ተቃውሞ 

የፉአድ ለጂቡቲ ተላልፎ የመሰጠት ጉዳይ በጁቡቲያውያን ዘንድ በቀላሉ አልታየም። የአብራሪው መታሰር ከተሰማ ጀምሮ ጁቡቲያውያን በማህበራዊ መገናኛ አውታሮች ቁጣቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል። ፉአድ በጋቦዴ ወህኒ ቤት ውስጥ እንዳለ የቀረጸው ቪዲዮ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ከተሰራጨ በኋላ የጂቡቲያውያን ቁጣ ገንፍሎ ለተቃውሞ አደባባይ እንዲወጡ አድርጓቸዋል።

የ12 ደቂቃ ተኩል ርዝመት ባለው በዚህ ተንቀሳቃሽ ምስል ላይ ፉአድ በቆሸሸ መፀዳጃ ቤት ውስጥ መታሰሩን ያሳያል። በዚሁ ቪዲዮ ላይ በብረት ፍርግርግ እና በሽቦ ወንፊት በተሸፈነው የሽንት ቤቱ አንደኛው ጥግ ላይ ሆኖ፤ በእስር ላይ የደረሰበትን በደል በሶማሊኛ ቋንቋ ሲናገር የሚደመጠው ፉአድ፤ የደረሰበትን ስቅይት (ቶርቸር) ልብሱን በመግለጥ ጭምር ያሳያል። 

ፉአድ ከወህኒ ቤቱ ቪዲዮውን ከለቀቀ በኋላ የመጀመሪያው ሰልፍ ግንቦት 27 የተደረገ ሲሆን ሰልፉን ፖሊስ በሃይል እንደበተነ የአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገባ ያመለክታል። የተቃውሞ ሰልፉ በጅቡቲ ሁለተኛ ከተማ በሆነችው አሊ ሳቤህ ግንቦት 28ም የቀጠለ ሲሆን፤ ፖሊስ በሰልፈኞች ላይ በተኮሰው ጥይት ብዙሃን መጎዳታቸውን እና ሌሎች መታሰራቸውን የዜና ወኪሉ ዘግቧል።

በእነዚህ ተቃውሞ ሰልፎች በርካታ ሰዎች ታስረዋል። ከታሰሩት መካከልም ጋዜጠኞች ይገኙበታል። “ሪፖርተርስ ዊዝ አውት ቦርደርስ” እንዲሁም የዳያስፖራ ራዲዮ ጣቢያ የሆነው የ “ላ ቮክስ ዴ ጅቡቲ (ኤል ቪ ዲ)”  ዘጋቢ በመሆን የተቃውሞ ሰልፎቹን በመዘገብ ላይ የነበረው ሞሃመድ አብራሂም ዋሪስ በቁጥጥር ስር ከዋሉት ጋዜጠኞች መካከል ነበር።

በተመሳሳይ ለኤል ቪዲ የሚሰራው ቃሲም ኑር አባህ ተቃውሞዎቹን በመዘገብ ላይ እያለ ተይዞ እንደነበር ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች ተቋም “ሪፖርተርስ ዊዝ አውት ቦርደርስ” ይፋ አድርጎ ነበር። የታሰሩት ጋዜጠኞቹ ከአምስት ቀን በኋላ ግንቦት 30 መለቀቃቸውም ታውቋል። ጅቡቲ በአለም አቀፉ የፕሬስ ነጻነት ኢንዴክስ ከ180 አገራት፤ አራት አገራትን ብቻ በመቅደም 176ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

ላለፉት 35 አመታት የአሜሪካን አለማቀፍ የደህንነነት ስጋቶችን የሚተነትነው እና የሚሰንደው የውጭ ደህንነት አማካሪ ምክር ቤት (OSAC) በጅቡቲ ከተማ ሰኔ 5፤ 2012 የተጠራውን የተቃውሞ ሰልፍ ተከትሎ ማስጠንቀቂያ አውጥቶ ነበር። በአሜሪካ መንግስት እና በግሉ ዘርፍ ትብብር የደህንነት ስጋቶቹን የሚያጠናው ኦሳክ የተቃውሞ ሰልፎቹ በስድስት ዋና ዋና ቦታዎች ላይ ቢያተኩሩም በሌሎች አካባቢዎችም እንደሚካሄዱ በማስጠንቀቂያው ላይ ገልጾ ነበር። 

“ፒ ኬ 12፣ ሃያብሌ፣ ባልባላ አዲ፣ ሼኪ ሙሳ፣ ስታዴ አል ሃጂ ጉሌድ አፕቲዶን” ዋና ዋና መሰባሰቢያዎቹ እንደሚሆኑም አሳስቦ ነበር። ሰልፉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጅቡቲ መንግስትን ለመቃወም የጠሩት እንደሆነ የኦሳክ የጅቡቲ ቅርንጫፍ አረጋግጧል። “የጅቡቲ የፀጥታ ሃይሎች የሃይል እርምጃዎችን ባልተፈቀዱ ሰልፍ ላይ በመውሰድ የሚታወቁ ናቸው” በማለት ከሰልፉ ቀደም ብሎ ባወጣው ማስጠንቀቂያው ላይ ተቋሙ አስፍሮ ነበር።

መጋል የጀመረው የጅቡቲ ፖለቲካ   

ፉአድ ወደ ጂቡቲ ተላልፎ ከተሰጠበት በኋላ ከ 12 ቀናት  ቆይታ በኋላ ነበር በመደበኛ ፍርድ ቤት ቀርቦ ጉዳዩ የታየው። መደበኛ የፍርድ ሂደት መጀመሩ ሳይረጋገጥ፣ የሰብአዊ መብቶቹ በአግባቡ እንደሚያዙ ማረጋገጫ ሳይታይ እና ጥገኝነት የመጠየቅ መብቱን አሟጦ ሳይጠቀም ተላልፎ የመሰጠቱ ጉዳይ በሰብአዊ መብት ባለሞያዎች ዘንድ ጥያቄን አጭሯል።

አለማፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ሂውማን ራይትስ ዋችም ጉዳዩን በመመርመር በ ሰኔ 25፤ 2012 ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ ላይ የፉአድ ጤንነት አስጊ ሁኔታ ላይ መድረሱን ከቤተሰቦቹ መረዳቱን ጠቅሷል። ከዚህ ቀድሞ በጋቦዴ ወህኒ ቤት ታስረው ከቆዩ በኋላ ህይወታቸው ያለፈ ፖለቲከኞችን በማንሳት የእርሱም ህይወት እንዳያልፍ ስጋት እንዳለውም ጨምሮ ገልጿል። 

የፉአድ ጠበቃም የደንበኛቸው ጤና አስጊ ሁኔታ ላይ በመድረሱ ምክንያት በሆስፒታል ውስጥ እንዲቆይ ወይም በጊዜያዊነት እንዲለቀቅ ጠይቀው ነበር። ነገር ግን የጅቡቲ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት በሰኔ 4፤ 2012 ውሎው ይህን ጥያቄ ውድቅ አድርጎታል።

ከ43 ዐመታት በፊት ከቅኝ ገዢዋ ፈንሳይ ነጻ ለመውጣት ባካሄደችው ህዝበ ውሳኔ ነጻነቷን የተጎናጸፈችው ትንሿ አፍሪካዊት አገር ጅቡቲ፤ ከነፃነት በኋላ የመጀመሪያ መሪዋ የነበሩት ሃሰን ጉሌድ ኦፕቲዶን ለ22 ዓመታት መርተዋታል። ኦፕቲዶን በ1991 ዓ. ም ስልጣናቸውን ሲለቁ መንበሩን ያስረከቡት ለወንድማቸው ልጅ ኢስማኤል ጉሌህ ነበር። ለ20 ዓመታት የኦፕቲዶን የቀኝ እጅ የነበሩት ጉሌህ የጸጥታ ሹም፣ የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት  ኃላፊ እና አማካሪያቸው ሆነው አገልግለዋል፡፡

ለ20 ዓመታ ያህል ጅቡቲን በፕሬዝዳትነት የመሩት ጉሌህ ላይ አራት አገር አቀፍ ምርጫዎችን ማሸነፋቸው ታውጆላቸዋል። ከሶስተኛው የምርጫ ድላቸው በኋላ ግን ጠንከር ያሉ ተቃውሞዎች እየገጠሟቸው ይገኛል። ከ2007 በኋላ ጠንካራ የተባለለት ተቃውሞ በሀገሪቱ የተቀሰቀሰው ደግሞ ከኢትዮጵያ ለጅቡቲ ተላልፎ የተሰጠው ፉአድ በእስር ላይ የደረሰበትን ስቅይት የሚያሳየው ቪዲዮ ከተሰራጨ በኋላ ነው። 

ፉአድ “እንደ ጋቦዴ ካለ ጠንካራ ወህኒ ቤት ውስጥ እንዴት ቪዲዮውን ቀርጾ ለመልቀቅ ቻለ?” የሚለው ጉዳይም ራሱን ችሎ ሲያነጋግር ሰንብቷል። የቀጠናው የፖለቲካ ተንታኞች በበኩላቸው ሁነቱ “በጅቡቲ መንግስት የጸጥታ መዋቅር ውስጥ ያለውን ልዩነት ያሳየ ነው” ባይ ናቸው። የቪዲዮውን ለዕይታ መብቃት ተከትሎ በጅቡቲ የተቀሰቀሱት ተቃውሞዎችም “በሀገሪቱ ለአመታት የተጠራቀሙ ዘርፈ ብዙ ችግሮች የወለዷቸው ናቸው” ሲሉ ጉዳዩ በአብራሪው ላይ ደረሰ ከተባለው ኢ-ሰብዓዊ አያያዝ በላይም የሚሻገር መሆኑን ያስገንዝባሉ። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)