በአዲስ አበባ በህንጻ ግንባታ ሰራተኞች ላይ በደረሰ አደጋ ጉዳት ደረሰ

በአዲስ አበባ ወሎ ሰፈር አካባቢ እየተገነባ ባለ ህንጻ ላይ ዛሬ ቅዳሜ ሐምሌ 18፤ 2012 ጠዋት ላይ በደረሰ አደጋ አንድ ሰው ሲሞት በ9 ሰዎች ላይ ከባድ ጉዳት መድረሱን የአዲስ አበባ ከተማ የእሳትና የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ገለጸ። በህንጻው ግንባታ ላይ የተሰማሩ 55 ሰራተኞችንም ጉዳት ሳይደረስባቸው በህይወት መትረፋቸውንም አስታውቋል።        

በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 የሚገኘው ይህ ህንጻ በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (INSA) መገንባት የጀመረ ሲሆን ግንባታው ሲገባደድ ኤጀንሲውን ጨምሮ የሰላም ሚኒስቴር እና ሌሎች ተቋማትን በውስጡ ይይዛል ተብሎ የሚጠበቅ ነው። ባለ 15 ወለል የሆነው እና ወደ መጠናቀቁ እንደተቃረበ የተነገረለት ይህ ህንጻ የውጭ መስታወቶች ተገጥመውለታል። 

ዛሬ ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት ተኩል ገደማ በህንጻው ላይ የደረሰው አደጋ መንስኤ በውጭ ግድግዳ ላይ የተለጠፉ የሴራሚክ ልባሶች መንሸራተት ያስከተለው እንደሆነ አንድ የነፍስ አድን ሰራተኛ ተናግረዋል። የሴራሚክ ልባሶቹ፤ በግንባታ ሰራተኛ መወጣጫዎች (ስካፎሊዲንግ) ላይ በማረፋቸው የመደርመስ አደጋ መከሰቱን እና ጉዳት መድረሱን አክለዋል። 

በመወጣጫ መደርመስ አደጋው ጽኑ ጉዳት ከደረሰባቸው ሰራተኞች መካከል አንድ ግለሰብ ሆስፒታል ሲደርስ ህይወቱ ማለፉን የአዲስ አበባ ከተማ የእሳትና የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አንድ ባለሙያ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። ከባድ የመቁሰል አደጋ የደረሰባቸው ዘጠኝ የግንባታ ሰራተኞች በሆስፒታል በህክምና ላይ እንደሚገኙም አስረድተዋል። 

ሰራተኞቹን በህይወት ለማትረፍ 22 የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች እና አራት ተሽከርካሪዎች መሰማራታቸውን ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። በስፍራው የነበረው የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢም አምቡላንሶች አደጋ የደረሰባቸውን ሰራተኞች ወደ ሆስፒታል ሲያመላልሱ ተመልክቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)