የቢሾፍቱ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት ዛሬ ረፋዱን በነበረው የችሎት ውሎው፤ የኦሮሚያ ፖሊስ በአቶ ልደቱ አያሌው ላይ ምርመራ ለማካሄድ የጠየቀውን የ14 ቀናት ጊዜን ፈቀደ። ፖሊስ “ሰኔ 23 እና 24 በቢሾፍቱ ከተማ የተቀሰቀሰውን ሁከት በማስተባበር እና በገንዘብ በመደገፍ አቶ ልደቱን ጠርጥሬያችኋለሁ” ሲል ለፍርድ ቤቱ ገልጿል።
ባለፈው አርብ ሐምሌ 17፤ 2012 በአዲስ አበባ በፌደራል ፖሊስ አባላት በቁጥጥር ስር የዋሉት አቶ ልደቱ በዚያኑ ቀን መኖሪያቸው ወደሚገኝበት ቢሾፍቱ ከተማ ተወስደዋል። ፍርድ ቤት ከመቅረባቸው አስቀድሞ ያሉትን ሁለት ቀናት በእስር ያሳለፉት በከተማይቱ በሚገኝ ሶስተኛ ተብሎ በሚታወቀው የፖሊስ ጣቢያ ውስጥ መሆኑን፤ መስራች እና የብሔራዊ ምክር ቤት አባል የሆኑበት የኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ፕሬዝዳንት አቶ አዳነ ታደሰ ለ”ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
በዛሬው የችሎት ውሎ የፓርቲው ጠበቃ አቶ ልደቱ የተጠረጠሩበትን “ወንጀል አልፈጸሙም” ሲሉ ለፍርድ ቤቱ መቃወሚያ ማቅረባቸውን አቶ አዳነ ገልጸዋል። የድምጻዊ ሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች ሁከት ከተቀሰቀሰ በኋላ ፖሊስ “ለደህንነታቸው” በሚል አቶ ልደቱን ከቢሾፍቱ አጅቦ ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ ማድረጉን ጠበቃው ጠቅሰዋል ብለዋል።
የኢዴፓ ጠበቃ “አቶ ልደቱ ከወንጀሉ ጋር ምንም ግንኙነት የላቸውም። የዋስትና መብታቸው ተከብሮ ይለቀቁ” ሲሉ ለፍርድ ቤቱ ጥያቄ ማቅረባቸውንም የፓርቲው ፕሬዝዳንት አመልክተዋል። “የዋስትና ጥያቄው ተቀባይነት የማያገኝ ከሆነ እንደ ሀገር አቀፍ ፓርቲ አመራርነታችው እና ብጥብጡ የተከሰተውም እንደ ሀገር በመሆኑ ጉዳያቸው በፌደራል ደረጃ በአዲስ አበባ ሊታይ ይገባል” በማለት ጠበቃው አማራጭ ሀሳብ ማቅረባቸው ተገልጿል።
ፖሊስ በጠበቃው የቀረቡትንም ሁለቱንም መከራከሪያዎች በመቃወም ለችሎቱ ምላሽ ሰጥቷል። በሰኔ 23 እና 24፤ 2012 በቢሾፍቱ ከተማ ሁከት እንደነበር የጠቀሰው ፖሊስ “ጉዳዩ መታየት ያለበት ወንጀሉ በተፈጸመት ቦታ እንጂ በአዲስ አበባ አይደለም” ብሏል። ዋስትናን በተመለከተ ለቀረበው ጥያቄም ፖሊስ “ተጠርጣሪው በዋስ ቢለቀቁ ማስረጃዎችን ሊያጠፉብኝ ይችላሉ” በሚል መቃወሙን አቶ አዳነ ተናግረዋል።
የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው የቢሾፍቱ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት በአቶ ልደቱ ጠበቃ የቀረቡትን ጥያቄዎች ውድቅ አድርጓል። ፍርድ ቤቱ ፖሊስ የጠየቀውን የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ በመፍቀድ ለነሐሴ 4፤ 2012 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። (በተስፋለም ወልደየስ- ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)