ኢትዮ ቴሌኮም በዓመት 47.7 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ

ኢትዮ ቴሌኮም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 47.7 ቢሊዮን ብር ገቢ ማስገባቱን የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ አስታወቁ። ተቋሙ ገቢውን በ25 በመቶ ለማሳደግ አቅዶ የነበረ ቢሆንም ከእቅዱ 105 በመቶ ማሳካቱን ገልጸዋል።

ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ይህን የገለጹት የተቋሙን የበጀት አመት አፈጻጸም በተመለከተ ዛሬ ሐሙስ ሐምሌ 23፤ 2012 በአዲስ አበባው ሃያት ሪጀንሲ ሆቴል በሰጡት መግለጫ ነው። ኢትዮ ቴሌኮም የሞባይል ድምጽ አገልግሎት ተጠቃሚ ደንበኞቹን በበጀት ዓመቱ ማጠናቀቂያ ወደ 44.5 ሚሊዮን ማሳደጉን ፍሬህይወት ተናግረዋል።  የተቋሙ የኢንተርኔት እና ዳታ ደንበኞችም 23.8 ሚሊዮን መድረሳቸው ተነግሯል።

በኢትዮጵያ ብቸኛ የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ የሆነው ኢትዮ ቴሌኮም፤ ባለፈው በጀት ዓመት 11.3 ቢሊዮን ብር ታክስ ለመንግስት መክፈሉን እና 147.7 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማስገኘቱን የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ ገልጸዋል። ተቋሙ የማህበራዊ ኃላፊነትን ለመወጣት 1.1 ቢሊዮን ብር ወጪ ማድረጉንም ጠቁመዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)