የፌዴሬሽን ምክር ቤት የትግራይ ክልል መንግስትን አስጠነቀቀ

በተስፋለም ወልደየስ 

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የትግራይ ክልል መንግስት ምርጫ ለማካሄድ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ “በአፋጣኝ እንዲያቆም” አሳሰበ። ክልሉ “ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ በሚጥል” ድርጊቱ የሚቀጥል ከሆነ፤ ምክር ቤቱ “በሕገ መንግስቱ እና ሌሎች ሕጎች የተሰጠውን ስልጣን ለመተግበር እንደሚገደድ” አስጠንቅቋል።  

ምክር ቤቱ ማስጠንቀቂያውን የሰጠው ለትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት ከቀናት በፊት በላከው ደብዳቤ ነው። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው ባለ ሶስት ገጽ ደብዳቤ “የኢ.ፌ.ዲ.ሪ  ሕገ መንግስትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ እንዲከበር ስለማሳሰብ” የሚል ርዕስ ይዟል። 

ባለፈው ሰኔ ወር የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤነትን የተረከቡት አቶ አደም ፋራህ ፊርማ የሰፈረበት ደብዳቤው፤ ምክር ቤቱ “የሕገ መንግስቱ ጠባቂ” መሆኑን አስታውሷል። የትግራይ ክልል መንግስት የራሱን የምርጫ ኮሚሽን በማቋቋም ጭምር እያካሄደው ያለው እንቅስቃሴም “ግልጽ የሆነ የሕገ መንግስት ጥሰት ነው” ሲል ወንጅሏል።

ፎቶ፦ የፌዴሬሽን ምክር ቤት

ምክር ቤቱ ተጣሱ ያላቸውን የሕገ መንግስት አንቀጾች በደብዳቤው ዘርዝሯል። የፖለቲካ መብቶችን ለማስፈጸም አስፈላጊ የሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶችን እንዲሁም ምርጫን በሚመለከት ህጎችን የማውጣት ስልጣን ያለው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሆኑን ያነሳው ደብዳቤው ይህም በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 51 (15) እና 55 (2) (መ) መደንገጉን ጠቅሷል።

በፌደራል እና በክልል የምርጫ ክልሎች የሚደረጉ፤ ነጻ እና ትክክለኛ ምርጫዎችን በገለልተኝነት ማካሄድ የሚችለው፤ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ብቻ መሆኑ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 102 መደንገጉንም ደብዳቤው ጠቁሟል። በዚሁ የሕገ መንግስት አንቀጽ፤ የምርጫ ቦርድ አባላት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚሾሙ ያመላከተው ደብዳቤው ይህም “በክልል ደረጃ የሚቋቋም የምርጫ ቦርድ ያለመኖሩ” ማሳያ እንደሆነ አብራርቷል። 

የትግራይ ክልል ስድስተኛውን ዙር ምርጫ በክልሉ እንዲካሂድ ወስኖ እየተንቀሳቀሰ ያለው፤ እነዚህን የሕገ መንግስት አንቀጾች እና ባለፈው ዓመት የጸደቀውን የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅ በጣሰ መልኩ መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት በደብዳቤው አትቷል። ክልሉ ስልጣን በራሱ ምርጫ ለማካሄድ የወሰነው ውሳኔ እና ይህንኑ ለማስፈጸም እያደረገው ያለው እንቅስቃሴ፤ ከሕገ መንግስቱ እና ከምርጫ ህጉ ጋር ከመቃረኑ ባሻገር፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሰኔ 3፤ 2012 የሰጠውን ውሳኔ “ያላከበረ ነው” ሲል ተችቷል።   

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባለፈው ሰኔ ወር ባካሄደው ስብሰባ፤ ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ እንዲራዘም ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል። ምክር ቤቱ ከውሳኔው ላይ የደረሰው፤ ምርጫ ማራዘምን በተመለከተ የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ የሕገ መንግስት ትርጉም እንዲሰጥበት የውሳኔ ሀሳብ ካቀረበለት በኋላ ነበር። ምክር ቤቱ ከምርጫ ማራዘም ውሳኔ ላይ የደረሰው እንዴት እንደነበር ለትግራይ ክልል በጻፈው ደብዳቤ መግቢያ ላይ ዘርዘር አድርጎ አስቀምጧል። 

የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት “ምርጫን በወቅቱ ለማካሄድ ከአቅም በላይ የሆነ እክል ሲያጋጥም ምን መደረግ እንዳለበት በግልጽ አለመደንገጉን” ያነሳው ደብዳቤው፤ ምክር ቤቱ “ክፍተቱን በሕገ መንግስት ትርጉም መሙላት ተገቢ መሆኑን በማመን” በጉዳዩ ላይ ሰፊ ውይይት ማድረጉን ገልጿል። በስራ ላይ ያሉት ምክር ቤቶች እና የአስፈጻሚው አካል ስልጣንና የስራ ዘመን፤ ከሕገ መንግስቱ አላማዎች እና ግቦች እንዲሁም መሰረታዊ መርሆዎች ጋር በማስተሳሰር እና በማገናዘብ ከተደረገ ውይይት በኋላ ከውሳኔ ላይ መድረሱንም አስታውቋል። 

የትግራይ ክልል መንግስት ይህን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ “ወደ ጎን በመተው” ምርጫን ለማካሄድ የጀመረው እንቅስቃሴ፤ “ሕገ መንግስቱን የሚቃረን፣ ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል እና የኢትዮጵያን የፌደራል ስርዓት የሚጎዳ አካሄድ [ነው]” ነው ብሏል ደብዳቤው። የፌደራል መንግስት በክልል ጣልቃ የሚገባበትን ስርዓት ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ በመጥቀስም፤ የክልሉ ድርጊት ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ ለመጣሉ ማሳያ አቅርቧል።     

“በአንድ የክልል መንግስት ተሳትፎ ወይም እውቅና ሕገ መንግስቱን ወይም ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን ባለማክበር የሚደረግ እንቅስቃሴ ወይም ድርጊት፤ ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ እንቅስቃሴ ወይም ድርጊት እንደሆነ በግልጽ ተደንጓል” ብሏል ደብዳቤው። 

“የፌደራል መንግስት የተሰጠው ስልጣን በክልሎች መከበር ያለበት በመሆኑ፤ ማንኛውም ሕግ ወይም የመንግስት አካል ውሳኔ ከሕገ መንግስቱ ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚነት እንደማይኖረው ታውቆ የክልሉ መንግስት ሕገ መንግስቱን እና የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ውሳኔ እንዲያከብር እና የጀመረውን ኢ-ሕገ መንግስታዊ እንቅስቅሴ በአፋጣኝ እንዲያቆም እናሳስባለን” ሲል የፌዴሬሽን ምክር ቤት በደብዳቤው ማጠቃለያ ላይ አስታውቋል።   

“ክልሉ ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ በሚጥለው ድርጊቱ የሚቀጥል ከሆነ፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ መንግስቱ እና አግባብነት ባላቸው ሌሎች ህጎች የተሰጠውን ስልጣን ለመተግበር የሚገደድ መሆኑን እንገልጻለን”

የፌዴሬሽን ምክር ቤት

“ይህ ሳይሆን ቀርቶ ክልሉ ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ በሚጥለው ድርጊቱ የሚቀጥል ከሆነ፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ መንግስቱ እና አግባብነት ባላቸው ሌሎች ህጎች የተሰጠውን ስልጣን ለመተግበር የሚገደድ መሆኑን እንገልጻለን” በማለት ምክር ቤቱ ለትግራይ ክልል የላከውን ደብዳቤ በማስጠንቀቂያ ቋጭቷል። 

ደብዳቤው የተላከለት የትግራይ ክልል ምክር ቤት፤ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ላልተወሰነ ጊዜ እንዲራዘም የተደረገው የ2012 ምርጫ በክልሉ እንዲካሄድ የወሰነው ሰኔ 5፤ 2012 ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ ነበር። በሙሉ ድምጽ የጸደቀው የክልሉ ምክር ቤት ውሳኔ ምርጫው “ህግን ተከትሎ እንዲካሄድ በወቅቱ እንዲካሄድ” አቅጣጫ ማስቀመጡ አይዘነጋም።

ምክር ቤቱ ሰኔ 30 ባካሄደው መደበኛ ጉባኤው የክልሉን የምርጫ ኮሚሽን ማቋቋሚያ እንደዚሁም የምርጫ እና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጆችን አጽድቋል። ከሁለት ሳምንት በፊት፤ ሐምሌ 9፤ 2012 አስቸኳይ ስብሰባውን ያካሄደው የክልሉ ምክር ቤት፤ በክልሉ ለስድስተኛ ጊዜ የሚካሄደውን ምርጫ የሚያስፈጽሙ አምስት አመራሮችን ሾሟል።

የክልሉን የምርጫ ኮሚሽን በኮሚሽነርት እንዲመሩ የተሾሙት መምህር ሙሉ ወርቅ ኪዳነ ማርያም ናቸው። ወይዘሮ ጽጌረዳ ዲበኩሉ ደግሞ የምርጫ ኮሚሽኑን ምክትል ኮሚሽነር ሆነዋል። ኮሚሽኑ በዚህ ዓመት መጨረሻ በትግራይ ይካሄዳል በተባለው ምርጫ የሚሳተፉ የግል እና የፖለቲካ ፓርቲ ዕጩዎች ምዝገባን በማካሄድ ላይ ይገኛል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)