በኮንሶ እና አሌ ማህበረሰቦች ግጭት የተጠረጠሩ 7 አመራሮች በቁጥጥር ስር ውለዋል ተባለ

የፎቶ ዘገባ፦ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ርስቱ ይርዳው ከሰሞኑ በኮንሶ እና አሌ ማህበረሰቦች መካከል በተፈጠረው ግጭት የደረሰውን ጉዳት በዛሬው ዕለት፤ ቅዳሜ ሐምሌ 25፤ 2012 ፤ በአካባቢው በመገኘት ተመልክተዋል። ርዕሰ መስተዳደሩ ክክልሉ መንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን በግጭቱ የወደሙ ቤቶች እና የእህል ጎተራዎችን ተዘዋውረው አይተዋል። 

የ21 ሰዎች ህይወት የተቀጠፈበት ይህ ግጭት የተቀሰቀሰው በአንድ አካባቢ በሚኖሩ ሁለት ጎረቤታሞች መካከል በተፈጠረ የመሬት ይገባኛል ጥያቄ እንደነበር የአካባቢው አስተዳዳሪዎች በዛሬው መርሃ ግብር ላይ ተናግረዋል። አስተዳዳሪዎቹ ችግሩን በሽምግልና መፍታት እየተቻለ ግጭት በመቀስቀስ ወደ ሌሎች ቀበሌዎች እንዲዛመት ያደረጉ ኃይሎችንም ወንጅለዋል። 

እስካሁን ድረስ ለግጭቱ መባባስ ምክንያት ናቸው ተብለው የተጠረጠሩ የኮንሶ ዞን እና የአሌ ልዩ ወረዳ ሰባት አመራሮች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል። ሌሎች ተጠርጣሪዎችንም በቁጥጥር ስር የማዋሉ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም በመርሃ ግብሩ ለተገኙ የአካባቢው ነዋሪዎች ቃል ተገብቷል። የዛሬው መርሃ ግብር የተጠናቀቀው ከሁለቱም ከሁለቱም ማህብረሰብ የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች የያዘ የእርቀ ሰላም ቡድን በማቋቋም ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)