በድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ማግስት፤ ማክሰኞ ሰኔ 23፤ 2012፤ በርካታ ወጣቶች ሀዘናቸውን እና ተቃውሟቸውን ለመግለጽ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ተምመው ነበር። ወጣቶቹ በቡድን ቡድን ሆነው፣ መፈክር እያሰሙ ወደ መስቀል አደባባይ አቅጣጫ ሲጓዙ ታይተዋል።

በሰኔ 23ቱ የአዲስ አበባ ሁነት የተሳተፉ አብዛኞቹ ወጣቶች ዱላ እና አጣና ይዘው ነበር። የወጣቶቹ ጉዞ በመጀመሪያ ሰላማዊ የነበረ ቢሆንም ረፋድ ላይ ግን፤ በበቅሎ ቤት አካባቢ፤ በድንጋይ መንገድ ወደ መዝጋት እና የህንጻ መስታወቶችን ወደ መሰባበር ተሸጋግሯል።
ወጣቶቹን፤ የአዲስ አበባም ሆነ የፌደራል ፖሊስ አባላት ለሰዓታት በዝምታ ሲመለከቷቸው ተስተውሏል። ሆኖም የድንጋይ ውርወራ እና የንብረት ውድመት ከተከሰተ በኋላ፤ የጸጥታ ኃይሎቹ ሁከቱን ለመቆጣጠር መጠነኛ እርምጃዎች ለመውሰድ ሲሞክሩ ታይተዋል።

ሁከቱን ተከትሎ የበቅሎ ቤት አካባቢ ነዋሪዎች አካባቢውን ለማረጋጋት በተሽከርካሪዎች ሲዘዋወሩ ለነበሩ የፖሊስ አባላት አቤቱታቸውን አቅርበዋል። ነዋሪዎቹ ፖሊስ በአካባቢው ከመድረሱ አስቀድሞ ድንጋይ ሲወረውሩ ከነበሩ ወጣቶች ጋር ተጋጭተው ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)