በተስፋለም ወልደየስ
የፌዴሬሽን ምክር ቤት በትግራይ ክልል ስለሚካሄደው ምርጫ የጻፈው ደብዳቤ “ህጋዊ ውጤት ሊያስከትል አይችልም” ሲል የክልሉ ምክር ቤት ምላሽ ሰጠ። የትግራይ ክልል ምክር ቤት ዛሬ ሰኞ ሐምሌ 27፤ 2012 በጻፈው የምላሽ ደብዳቤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የፈጸሙት ድርጊትም “ሕገ መንግስቱን የሚጥስ ነው” ብሏል።
የክልሉ ምክር ቤት በደብዳቤው “የክልሉ ምክር ቤት እና ህዝብ ያሳዩትን ህገ መንግስታዊና ህብረ ብሄራዊ ስርዓቱን የማስቀጠል ፍላጎት፣ ተነሳሽነት እና እንቅስቃሴ መደገፍ አሊያም አለማደናቀፍ ለሀገሪቱ ይበጃል የሚል ጽኑ እምነት አለን” ብሏል። ሆኖም “ይህ ሳይሆን ቀርቶ ሌላ ችግር ቢፈጠር ኃላፊነቱን መውሰድ ያለባቸው በኢ-ህገ መንግስታዊ ድርጊት የሚሳተፉ አካላት [ናቸው]” ሲል ምክር ቤቱ አሳስቧል።
የትግራይ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ሩፋኤል ሽፋረ ፊርማ የሰፈረበት ባለ አምስት ገጽ ደብዳቤ፤ “በኢ-ህገ መንግስታዊ ድርጊት የሚሳተፉ” ያላቸውን አካላት ባይዘረዝርም የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤን ግን በግልጽ በመጥቀስ ትችቶች አቅርቧል። አፈ ጉባኤው “ስልጣናቸውን አላግባብ ተጠቅመዋል” ሲል የክልሉ ምክር ቤት ወንጅሏል።
በክልሉ ምክር ቤት ትችት የቀረበባቸው አፈ ጉባኤ አደም ፋራህ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የመምራት ስልጣን ባለፈው ሰኔ ወር የተረከቡት፤ የህወሓት ስራ አስፈጻሚ አባል የሆኑትን ኬሪያ ኢብራሂም፤ ስልጣናቸውን በገጻ ፍቃዳቸው መልቀቃቸውን ተከትሎ ነው። በፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤነት ለሁለት ዓመታት ያገለገሉት ኬሪያ ስልጣናቸውን የለቀቁት፤ “ሕገ- መንግስት ከሚጥስ እና አምባገነናዊ አካሄድን ከሚያራምድ ቡድን ጋር አብረው ለመስራት ፈቃደኛ አይደለሁም” በሚል ምክንያት ነበር።
እርሳቸውን የተኳቸው አቶ አደም፤ ባለፈው ሳምንት ለትግራይ ክልል ምክር ቤት በፊርማቸው በላኩት ደብዳቤ፤ የክልሉ መንግስት ምርጫ ለማካሄድ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ “በአፋጣኝ እንዲያቆም” አሳስበዋል። የትግራይ ክልል “ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ በሚጥል” ድርጊቱ የሚቀጥል ከሆነ፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ መንግስቱ እና ሌሎች ሕጎች የተሰጠውን ስልጣን ለመተግበር የሚገደድ መሆኑንም በደብዳቤያቸው አስጠንቅቀዋል።
የትግራይ ክልል ምክር ቤት በዛሬው ምላሹ “የክልሉ ህዝቦች ሉዓላዊ ስልጣናቸውን ተጠቅመው የሚወስኑት ውሳኔ በባለ ስልጣንም ሆነ በማናቸውም አካል የሚዛትበት ወይም ደብዳቤ ሊጻፍበት የሚቻልበት ህጋዊ እና ህገ መንግስታዊ ምክንያት የለም” ብሏል። “የአፈ ጉባኤው ድርጊት ሕገ መንግስቱ ከሰጣቸው ስልጣን ውጪ የተፈጸመና ሕገ መንግስቱን የሚጥስ በመሆኑ የተጻፈው ደብዳቤ ህጋዊ ውጤት ሊያስከትል አይችልም” ሲል አቋሙን ግልጽ አድርጓል። ድርጊቱ “በአስቸኳይ ሊታረም” እንደሚገባም ምክር ቤቱ አሳስቧል።
ምክር ቤቱ በትግራይ ክልል ምርጫ ማካሄድ “ለሕገ መንግስታዊ ስርዓት አደጋ ሊሆን አይችልም” ሲልም በደብዳቤው ሞግቷል። የትግራይ ክልል መንግስት ምርጫ ለማካሄድ የወሰነው “ሕገ መንግስታዊ ኃላፊነቱን” ለመወጣት መሆኑን የጠቀሰው ደብዳቤው፤ የክልሉ ሕገ መንግስትም በየአምስት አመቱ ምርጫ እንዲካሄድ እንደሚያስገድድ አንቀጾችን ጠቅሶ አስረድቷል።
“ምርጫ ማካሄድ ለሕገ መንግስታዊ ስርዓቱ ዋስትና መስጠትና ኃላፊነትን መወጣት ያመለክታል እንጂ ለሕገመንግስታዊ ስርዓቱ አደጋ ሊሆን አይችልም” ሲል የክልሉ ምክር ቤት ደብዳቤ አስገንዝቧል። የፌዴሬሽን ምክር ቤትም ሆነ ሌላ አካል በትግራይ ምርጫ ላይ የማዘዝ ስልጣን እንደሌለው አጽንኦት የሰጠው ደብዳቤው የምርጫው ባለቤት “የትግራይ ህዝብ ብቻ ነው” ብሏል።
“የትግራይ ክልል ምክር ቤት ሕገ መንግስቱን ተከትሎ ክልላዊ ምርጫ ለማካሄድ ያስተላለፈው ውሳኔ፤ ሕገ መንግስቱን ለማክበርና የትግራይ ህዝብ በመረጠው መንግስት እንዲመራና እንዲተዳደር ለማድረግ ካለው ፅኑ እምነት የተነሳ መሆኑን ሁሉም የሚያውቀውና ጸሀይ የሞቀው ጉዳይ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል” ሲልም አክሏል።
ምክር ቤቱ ይህን ቢልም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት በጻፈው ደብዳቤ፤ የትግራይ ክልል መንግስት የራሱን የምርጫ ኮሚሽን በማቋቋም ጭምር እያካሄደው ያለው እንቅስቃሴ ሕገ መንግስቱን እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅን በመጣስ እንደሆነ አስታውቆ ነበር። የምርጫ እንቅስቃሴው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባለፈው ሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ ያሳለፈውን የምርጫ ማራዘም ውሳኔ “ያላከበረ ነው” ሲልም ተችቷል።
የትግራይ ክልል ምክር ቤቱ ለዚህ በሰጠው ምላሽ “የትግራይ ብሄራዊ ክላልዊ መንግስት ምርጫ እንዲደረግ በምክር ቤቱ መወሰኑ፣ የምርጫና የስነ ምግባር ህግ ማውጣቱ፣ የምርጫ ኮሚሽን ማቋቋሙና የምርጫ ሂደት መጀመሩ በኢፌዲሪ ሕገ መንግስት አንቀጽ 39፣ 52 እና 13 ለሕገ መንግስታዊ ስርዓቱ ያለው ታማኝነትና ተገዥነት ያሳያል” ሲል ተከራክሯል።
“የፌዴሬሽን ምክር ቤት በህገ መንግስት ትርጉም ሰበብ ምርጫ ለማራዘም ያስተላለፈው ውሳኔ ኢ-ሕገ መንግስታዊ ከመሆኑ ባለፈ የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት አባላት ምርጫ ለማራዘም ምንም አይነት ህገ መንግስታዊ ስልጣን የለውም። በመሆኑም የትግራይ ክልል የጣሰው ውሳኔ የለም” ሲል አብራርቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)