የኢዜማ ስራ አስፈጻሚ አባል በዋስ እንዲለቀቁ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰጠ

የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ የብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት ሂሩት ክፍሌ በስድስት ሺህ ብር ዋስትና ከእስር እንዲፈቱ ትዕዛዝ አስተላለፈ። ፍርድ ቤቱ ትዕዛዙን የሰጠው ዛሬ ማክሰኞ ሐምሌ 28፤ 2012 በዋለው ችሎት ነው። 

ሐምሌ 7 ቀን 2012 በቁጥጥር ስር የዋሉት ሂሩት ዛሬ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ለሶስተኛ ጊዜ ነው። የምርምራ የጊዜ ቀጠሮ ጉዳይን የሚመለከተው የአራዳ ምድብ ችሎት ለዛሬ ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረው፤ ፖሊስ የምርመራ መዝገቡን አጠናቅቆ እንዲቀርብ ነበር። 

በዛሬውም ችሎት ፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ቢጠየቅም ፍርድ ቤቱ ሳይቀበለው መቅረቱን የተጠርጣሪዋ ጠበቃ አቶ በእሱፍቃድ ፋንታዬ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ፖሊስ ቀሩኝ ያላቸውን የምርመራ ስራዎች ለፍርድ ቤቱ መዘርዘሩንም ገልጸዋል:: 

ለኢንፎርሜሽን እና መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (INSA) የተላከው የተጠርጣሪዋ ኮምፒውተር እና ስልክ የፍተሻ ውጤት እንዳልመጣለት ለፍርድ ቤቱ የገለጸው ፖሊስ ውጤቱን ለመቀበል ተጨማሪ ጊዜ መጠየቁን ጠበቃው አስረድተዋል። ፖሊስ ከዚህ በተጨማሪም በአዲስ አበባ ከተማ በተፈጠረው ሁከት የደረሰውን ውድመት ግምት ለመቀበል ለሚመለከተው ደብዳቤ መጻፉን እና የዚህንም ውጤት ገና አለመቀበሉን ለችሎት ተናግሯል ብለዋል። 

ፖሊስ ሂሩትን በቁጥጥር ስር ያዋላቸው “በአዲስ አበባ ከተማ ከቅድስተ ማሪያም እስከ ግንፍሌ አካባቢ ያሉ ወጣቶችን በማስተባበር፤ ሁከት በማስነሳት ተሳትፈዋል” በሚል ጠርጥሮ መሆኑን ከዚህ ቀደም በነበሩ የችሎት ውሎዎች መግለጹ ይታወሳል። በእነዚህ የችሎት ውሎዎች ይህንኑ የሚያስረዱለት የሰዎች ማስረጃዎች እያሰባሰበ መሆኑንም ለፍርድ ቤቱ አስታውቆ ነበር። 

በተጠርጣሪዋ ላይ ምርመራ እያከናወነ የሚገኘው የምርመራ ቡድን፤ ተጨማሪ የሰዎች ማስረጃ ለማሰባሰብ አድራሻቸውን እያፈላለገ በመሆኑ፤ ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጠው ለፍርድ ቤቱ ማመልከቱን የተጠርጣሪዋ ጠበቃ ተናግረዋል። ፖሊስ ደንበኛቸውን ከአንድ ወር በላይ በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ ሲያደርግ መቆየቱን ለፍርድ ቤቱ ያስረዱት ጠበቃ በእሱፍቃድ ጊዜው ለምርመራ “ከበቂ በላይ ነው” ሲሉ ተከራክረዋል። 

ደንበኛቸው የተጠረጠሩበት “ሁከት የመፍጠር ወንጀል” የዋስትና መብት የማያስከልክል መሆኑን ለፍርድ ቤቱ የጠቀሱት ጠበቃው የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው በድጋሚ ጠይቀዋል። “ፖሊስ ቀረኝ የሚለውን ምርመራ እርሳቸው በውጭ ሆነው ማድረግ ይችላል” ሲሉ አስረድተዋል።

የተጠርጣሪዋ ጠበቃ ተመሳሳይ የዋስትና ጥያቄ ሐምሌ 20፤ 2012 በዋለው ችሎት ቢያቀርቡም፤ ፍርድ ቤቱ ጥያቄያቸውን ውድቅ አድርጎ ስምንት ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ፈቅዶ ነበር። በዛሬው ችሎት የቀረበውን የግራ ቀኙን አስተያየት ያደመጠው ፍርድ ቤቱ የተጠርጣሪዋ ጠበቃ ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ መቀበሉን አቶ በእሱፍቃድ ገልጸዋል። የኢዜማ የሙያ ማኅበራት ተጠሪ የሆኑት ሂሩት የተጠየቀባቸው የስድስት ሺህ ብር ዋስትና መሆኑንም አክለዋል።    

ፍርድ ቤቱ ፖሊስ እስካሁን የተሰጠው የምርመራ ጊዜ “በቂ” መሆኑን ጠቅሶ፤ መርማሪ ቡድኑ ቀሪ ምርመራውን ተጠርጣሪዋ በውጭ ሆነው ማድረግ እንደሚችል ማስገንዘቡን አቶ በእሱፍቃድ ጠቁመዋል። ዋስትናውን የፈቀደው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት የጊዜ ቀጠሮ መዝገቡን መዝጋቱን የተጠርጣሪዋ ጠበቃ አብራርተዋል። (በተስፋለም ወልደየስ- ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)