በቤይሩት ፍንዳታ በኢትዮጵያውያን ላይ የደረሰው ጉዳት እየተጣራ ነው – ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

በተስፋለም ወልደየስ

በሊባኖስ መዲና ቤይሩት፤ ትላንት ማክሰኞ በደረሰው ከፍተኛ ፍንዳታ ምን ያህል ኢትዮጵያውያን እንደተጎዱ በመጣራት ላይ እንደሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቃባይ ዲና ሙፍቲ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። ፍንዳታው በደረሰበት አቅራቢያ ባለው የመኖሪያ ሰፈር፤ በርካታ ኢትዮጵያውያን እንደሚኖሩ ያመለከቱት በቤይሩት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን፤ ምን ያህሉ በአደጋው እንደተጎዱ ለማወቅ መቸገራቸውን ገልጸዋል። 

ቤይሩትን ባናወጠው ከፍተኛ ፍንዳታ የሞቱ ሰዎች ቁጥር መቶ መድረሱን የሊባኖስ ቀይ መስቀል ማህበር አስታውቋል። በአደጋው የተጎዱ ሰዎች ቁጥር ወደ አራት ሺህ ማሻቀቡንም የማህበሩ ሃላፊ ዛሬ ጠዋት ይፋ አድርገዋል።

በርካታ ኢትዮጵያውያን በቤት ሰራተኝነት እና በሌሎችም ስራዎች በተሰማሩባት የቤይሩት ከተማ፤ በኢትዮጵያውያን ላይ ምን ያህል ጉዳት እንደደረሰ እስካሁን በቁጥር የተጠናቀረ መረጃ አልወጣም። ጉዳቱን በተመለከተ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቃባይ ዲና ሙፍቲ “ከፍንዳታው ጋር ምን ያህል ኢትዮጵያውያን ተጎዱ የሚለው እየተጣራ ነው ያለው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። 

መስሪያ ቤታቸው “የዳያስፖራ ኢትዮጵያውያንን ጉዳይ በትኩረት እየተከታተለ” መሆኑን የገለጹት ቃል አቃባዩ፤ ሚኒስቴሩ ችግር ላለባቸውም ሆነ ለሌሎች ኢትዮጵያውያን መርዳቱን እንደሚቀጥል ገልጸዋል። እርሳቸው ይህን ቢሉም ከሊባኖስ ወደ ሀገራቸው መመለስ የሚፈለጉ በሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን፤ “መሄጃ አጥተው ችግር ላይ መውደቃቸውን” በተደጋጋሚ ሲገልጹ ቆይተዋል። በቤይሩት ያለው ቆንስላ ጽህፈት ቤትም ሆነ የኢትዮጵያ መንግስት እንዳልደረሰላቸውም 

ይንን ኢትዮጵያውያኑን እሮሮ በተመለከተ የተጠየቁት ዲና ከሀገሪቱ አቅም በላይ የሆኑ በርካታ ነገሮች ቢኖሩም የተወሰኑ ኢትዮጵያውያን እንዲመለሱ መደረጉን ተናግረዋል። “ከእኛ አቅም ውጪ የሆኑ፣ ከዚህ ኮቪድ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች አሉ። የሎጀስቲክ ጉዳይ፣ የመንገድ መከፈት ጉዳይ አለ። እንደዚያም ሆኖ እኮ በርካቶችን በነጻ አስመጥተናል” ብለዋል።  

የሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው እርምጃ “በቂ አይደለም” በሚል የሚቀርበው ትችትም “ባለው ነባራዊ ሁኔታ” መታየት እንዳለበት ገልጸዋል። “በዚህ በኩል እጥረቶች ይኖራሉ። ለማንኛውም መያዝ ያለበት፤ ይሄንን ነገር በትኩረት እየተከታተልነው መሆኑን ነው” ሲሉ የሚኒስቴሩ ቃል አቃባይ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል።  

“ከእኛ አቅም ውጪ የሆኑ፣ ከዚህ ኮቪድ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች አሉ። የሎጀስቲክ ጉዳይ፣ የመንገድ መከፈት ጉዳይ አለ። እንደዚያም ሆኖ በርካቶችን በነጻ አስመጥተናል

ዲና ሙፍቲ- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቃባይ

በሊባኖስ በቤት ሰራተኝነት ተቀጥረው ከሚሰሩ 250,000 ስደተኞች መካከል አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያንን መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። ዝቅተኛ ክፍያ የሚያገኙ ኢትዮጵያውያን በመዲናይቱ ቤይሩት በአንድ አካባቢ ተሰባስበው እንደሚኖሩ በዚያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ይናገራሉ። የትላንትናው ፍንዳታ በደረሰበት አቅራቢያ የሚገኘው እና “አሽረፍዬ” ተብሎ በሚጠራው በዚህ አካባቢ እንደ ኢትዮጵያውያን ሁሉ፣ ሶሪያውያን፣ ግብጻውያን እና የአርሜኒያ ዝርያ ያላቸው የሊባኖስ ዜጎች በብዛት የሚገኙበት መሆኑን ነዋሪዎቹ ያብራራሉ። 

በቤይሩት የምትገኝ አንዲት ኢትዮጵያዊት በ“አሽረፍዬ” አካባቢ ያሉ ኢትዮጵያውያን ምን ያህል ጉዳት እንደደረሰባቸው ማረጋገጥ ባትችልም በሌሎች አካባቢዎች ያሉ ቢያንስ አራት ኢትዮጵያውያን በመስታወት ስብርባሪ ተጎድተው ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውን እንደሰማች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግራለች። 

የትላንቱ ፍንዳታን ተከትሎ የሀዘን መግለጫቸውን በማህበራዊ ትስስር ገጾቻቸው የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በሊባኖስ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቤይሩት ከሚገኘው ቆንስላ ጋር ግንኙነት እንዲፈጥሩ አሳስበዋል። በቤይሩት የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት ትላንት ማምሻውን በፌስ ቡክ ገጹ ባሰራጨው መልዕክት “ሁኔታዎች እስኪረጋጉ” ኢትዮጵያውያን ዜጎች በተቻለ መጠን በቤት ውስጥ እንዲቆዩ መክሯል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)