ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን አሳልፎ በሚሰጡ ጉዳዮች ላይ ለመደራደር ፍቃደኛ አለመሆኗን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ

በተስፋለም ወልደየስ 

በኢትዮጵያ አሁን በስልጣን ላይ ያለው አመራር በአባይ ግድብ ድርድርም ሆነ በሌሎች ላይ ጉዳዮች ላይ የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም አሳልፎ በሚሰጡ ነገሮች ላይ “ለመደራደር ፍቃደኛ አይደለም” ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቃባይ ዲና ሙፍቲ ገለጹ። ቃል አቃባዩ ይህን ያሉት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የአባይ ግድብ ሙሌት እና አስተዳደርን አስመልክቶ እየተደረገ ስላለው ድርድር ከሰሞኑ ላቀረበው አስተያየት በሰጡት ምላሽ ነው።  

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ኢትዮጵያ በአባይ ግድብ ድርድር ላይ ከስምምነት ላይ ለመድረስ የቀራት ጊዜ እየተሟጠጠ መሆኑን ሰሞኑን “ብሎምበርግ” ለተባለው መገናኛ ብዙሃን አስታውቆ ነበር። ይህንን የአሜሪካን አቋም በተመለከተ ዛሬ አርብ ነሐሴ 1፤ 2012 በሰጡት ጋዜጣዊ መደበኛ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተጠየቁት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቃባይ “ብሔራዊ ጥቅማችንን በጫና አሳልፈን [አንሰጥም]” ብለዋል። 

“አሁን ያለው አመራርም ሆነ ህዝባችን፤ በድርድሩ ዙሪያም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ላይ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም አሳልፎ የሚሰጥ ነገር ላይ ለመደራደር ፍቃደኛ አይደለም። ወደዚያ የሚገፋንን ማንኛውም ነገር [እንጸየፋለን]” ሲሉ ቃል አቃባዩ የሀገራቸውን አቋም ግልጽ አድርገዋል። “ከአሜሪካ ጋር ያለን ግንኙነት እንዲበላሽ አንፈልግም” ያሉት ቃል አቃባዩ “ከአሜሪካ ጋር ያለን ግንኙነት ከተበላሸ የምንጎዳው እኛ ብቻ ሳንሆን አሜሪካኖችም ጭምር ናቸው” ብለዋል።  

በአፍሪካ ህብረት አመቻችነት እየተካሄደ ባለው የአባይ ግድብ ድርድር ላይ በታዛቢነት ከሚሳተፉት ውስጥ አሜሪካ አንዷ መሆኗን የገለጹት ዲና “በታዛቢነት ሚናቸው እንዲቀጥሉ እንፈልጋለን” ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። አሜሪካ በኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን መካከል የሚደረገው የሶስትዮሽ ድርድር እንዲሳካ የምታደርገውን ጥረት እና ድጋፍ ሀገራቸው እንደምታደንቅም አስታውቀዋል።

ሶስቱ የአባይ ተፋሰስ ሀገራት በአባይ ግድብ ላይ የጀመሩትን ድርድር የፊታችን ሰኞ ነሐሴ 4፤ 2012 ይቀጥላሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተጠቁሟል። ድርድሩ በዚህ ሳምንት ከመቋረጡ በፊት ኢትዮጵያ የአባይ ግድብ የውሃ ሙሌት ደንብን የያዘ ምክረ ሃሳብ አቅርባ ነበር። 

በምክረ ሃሳቡ የቀረበው አዲስ ነገር እንዳልሆነ ያመለከቱት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቃባዩ፤ ኢትዮጵያ በሙሌቱ ላይ በመጀመሪያ ስምምነት ከተደረሰ በኋላ ዘላቂ የሆነ የውሃ አጠቃቀምን በተመለከተ “በሌላ ማዕቀፍ፤ ሌላ ጊዜ እንነጋገር” የሚል አቋም እንዳላት አብራርተዋል። በታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ድርቅ በሚኖርበት ወቅት፤ ኢትዮጵያ ሁኔታውን ከግምት እንደምታስገባ፤ ሆኖም ስለ ውሃ አለቃቁ ከወዲሁ እንደማትወሰን መገለጿንም ተናግረዋል።   

“ከአሁኑ ‘ይህን ያህል ውሃ ልቀቁ፣ ይህን ውሃ አትልቀቁ፣ ይህን ያህል ውሃ መያዝ አትችሉም’ የሚለው አይነት ስምምነት ውስጥ አንገባም ነው። ምክንያቱም ይሄ የተፈጥሮ ውሃውን መቆጣጠር አንችልም። እንኳንና ይሄንን፤ ጣና ውስጥ ምን ያህል ውሃ እንዳለ ለማወቅ በጣም አስቸጋሪ ነው። ይቀያየራል፤ ይሄ የተፈጥሮ ጉዳይ ነው” ብለዋል። 

ግብጽ የኢትዮጵያን ምከረ ሃሳብ አጥንታ ለመምጣት የተጀመረውን ድርድር ብታቋርጥም፤ ቀጣይ ዙር ድርድር በመጪው ሰኞ እንዲካሄድ ሃሳቡ የቀረበው ከእርሷው መሆኑ ቃል አቃባዩ ጠቁመዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)