በተስፋለም ወልደየስ
ከኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) መስራቾች አንዱ የነበረው የብርሃነመስቀል ረዳ የትግል ታሪክ በባለቤቱ ታደለች ኃይለሚካኤል ተጽፎ ለንባብ በቃ። “ዳኛው ማነው?” የሚል ርዕስ የተሰጠው ይሄው መጽሐፍ የኢህአፓ ታጋይ የነበሩት የመጽሐፉ ደራሲ ታሪክንም በጥምር ያካተተ ነው።
ከጥንስሱ እስከ ህትመቱ አርባ ዓመታት ገደማ የወሰደው ይህ መጽሐፍ ታትሞ ገበያ ላይ የዋለው ከትላንት በስቲያ ሐሙስ፤ ሐምሌ 30፤ 2012 ዓ.ም ነው። በደራሲዋ እና ቤተሰቦቻቸው አማካኝነት በአዲስ አበባ የታተመው የዚህ መጽሐፍ የመጀመሪያ ረቂቆች የተጻፉት ደራሲዋ በደርግ ዘመነ መንግስት ለ12 ዓመታት ከአምስት ወር በታሰሩበት ወቅት እንደነበር ተገልጿል።
በአራት ክፍሎች እና በሃያ አንድ ምዕራፎች የተከፋፈለው መጽሐፍ ታሪኩን የሚጀምረው ወጣቷ ታደለች የከፍተኛ ትምህርታቸውን ወደ ተከታተሉባት ስዊዘርላንድ ለመጓዝ ከአዲስ አበባ ሲነሱ ነው። ደራሲዋ በዚህች የማዕከላዊ አውሮፓ ተራራማ ሀገር የነበራቸው ቆይታ የህይወታቸውን ጉዞ አቅጣጫ ያስቀየረ ነበር።
በስዊዘርላንድ የመጀመሪያ ዓመት ቆይታቸው ሙሉ ትኩረታቸውን ለትምህርታቸው ሰጥተው እንደነበር በመጽሐፉ የሚጠቅሱት ታደለች በአውሮፓ የነበረውን የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ለመቀላቀል ብዙ ጊዜ እንደወሰደባቸው ይተርካሉ። በተማሪዎች እንቅስቃሴው ለመሳባቸው ዋነኛ ምክንያቶች የነበሩት ደግሞ በአጋጣሚ መንገድ ላይ የተዋወቋቸው የንቅናቄው ተሳታፊዎች ተስፋዬ ደበሳይ እና አክሊሉ ኅሩይ ናቸው።
ኢህአፓ ሲቋቋም ከመስራቾቹ አንዱ ለመሆን የበቃው ተስፋዬ ደበሳይ፤ በታደለች ህይወት ጉልህ ስፍራ ለሚይዝ ሌላ ክስተት መንስኤም ሆኗል። ተስፋዬ በስተኋላ የደራሲዋ የትዳር እና የትግል አጋር የሆነውን ብርሃነመስቀል ረዳን ከታደለች ጋር በማስተዋወቅ፤ ሶስት ልጆችን ያፈራው ጥምረት እንዲወለድ ምክንያት ሆኗል።
ብርሃነመስቀል በስደት ከሚኖርበት አልጄሪያ ወደ ስዊዘርላንድ በመጣበት ወቅት፤ ምስጢር ለመጠበቅ ታስቦ በታደለች ቤት እንዲያርፍ መደረጉ ነበር ትውውቁን የወለደው። በአጋጣሚ የተጀመረው ግንኙነት ወደ ፍቅር አድጎ እስከ ትዳር ብሎም በመርሃ ቤቴ እና መንዝ የትጥግ ትግል አብሮ እስከ መመስረት ተጉዟል።
በ“ዳኛው ማነው?” መጽሐፍ ከዚህ ቀደም ከብርሃነመስቀል ወገን ያልተሰማው የእርሱ እና የባለቤቱ የመርሃ ቤቴ እና መንዝ የትጥቅ ትግል ቆይታ በዝርዝር ቀርቦበታል። ብርሃነመስቀል መርሃ ቤቴን ለትጥቅ ትግል የመረጠው በአጋጣሚ እንደሆነ ደራሲዋ አጽንኦት ሰጥተው በመጽሐፉ ያነሳሉ።
“ ‘ብርሃነመስቀል ወደ ሰሜን ሸዋ የሔደው ፓርቲው ቀደም ብሎ ያስጠናውን ቦታ በማወቁ ነው’ በማለት ክፍሉ ታደሰ የሚገልጸው ፍጹም ከእውነት የራቀ ነው። ባላሰበውና ባልተዘጋጀበት ሁኔታ ከፓርቲው እንዲገድለው የተላከው ደምሴ፤ የጓዱን አስተሳሰብ ሲረዳ አቋሙን ለውጦ በወንድሙ አማካይነት ይዞት ስለጠፋ ነው”
“ ‘ብርሃነመስቀል ወደ ሰሜን ሸዋ የሔደው ፓርቲው ቀደም ብሎ ያስጠናውን ቦታ በማወቁ ነው’ በማለት ክፍሉ ታደሰ [በ ያ ትውልድ መጽሐፍ] የሚገልጸው ፍጹም ከእውነት የራቀ ነው። ባላሰበውና ባልተዘጋጀበት ሁኔታ ከፓርቲው እንዲገድለው የተላከው ደምሴ፤ የጓዱን አስተሳሰብ ሲረዳ አቋሙን ለውጦ በወንድሙ አማካይነት ይዞት ስለጠፋ ነው” ሲሉ ታደለች በመጽሐፋቸው ይሟገታሉ።
የመርሃቤቴ ተወላጅ የሆነው የሰሜን ሸዋ ዞን አገናኝና በፓርቲው ውስጥ እንደአገናኝ ብቻ ሳይሆን የአዲስ አበባ ከተማ ታጣቂ (ስኳድ) አባል እንደነበር በመጽሐፉ ተጠቅሷል። ደምሴ እነ ብርሃነመስቀል “ክሊኩ” ብለው በሚጠሩት የኢህአፓ አመራሮች ስብስብ የተሰጠውን የግድያ ተልዕኮ እንዲፈጽም በአንጃነት ወደ ተፈረጀው ቡድን ሰርጎ የገባ እንደነበር ደራሲዋ ያብራራሉ። “እምነታችሁ እምነቴ፤ ጥያቄያችሁ ጥያቄዬ ነው” በሚል ከቡድኑ ጋር መገናኘት የጀመረው ደምሴ ሊገድለው የነበረውን ብርሃነመስቀልን ከከተማ እንዲሰወር በመርዳት የተጫወተው ሚናንም ዘርዝረዋል።
ታደለች ባለቤታቸውን በመርሃ ቤቴ ከተቀላቀሉ በኋላ የነበረውን ሂደትም ምስል ከሳች በሆነ መልኩ ጽፈዋል። በኢህአፓ ውስጥ እርማት እንዲደረግ የተፈጠረው ንቅናቄን በተለያዩ ጊዜ የተቀላቀሉ አባላት 20 ደርሰው እንደነበር የሚጠቁሙት ደራሲዋ በእነዚህ አባላት አማካኝነት፤ ከአላማው ጋር የሚሄድ፤ ታጥቆ አንቂና አደራጅ ቡድን (ታአአቡ) የተሰኘ ስብስብ መቋቋሙን ይገልጻሉ።
ቡድኑ በመርሃ ቤቴ እና በመንዝ የነበረው እንቅስቃሴ በመጽሐፉ በስፋት ተወስቷል። መጽሀፉ ካሉት አራት ክፍሎች አንደኛው የዋለውም ለዚሁ ቡድን ነው። የመጽሐፉ ማጠቃለያ ክፍል ደራሲዋ በእስርና በምርመራ ያሳለፉትን ጊዜ የሚተርክ ነው። በመጋቢት 1969 ወደ መርሃ ቤቴ የወረዱት ታደለች በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር የዋሉት፤ ከሁለት ዓመት የትጥቅ ትግል ቆይታ በኋላ በጥር 1971 ወደ አዲስ አበባ ለመመለስ በጉዞ ላይ ሳሉ ነበር።
ደራሲዋ ታደለች ከ12 ዓመታት የእስር ቆይታ በኋላ፤ በኢህአዴግ ዘመነ መንግስት የመጀመሪያዋ የሴቶች ጉዳይ ሚኒስትር በመሆን ለ11 ዓመታት ሀገራቸውን አገልግለዋል። በስተኋላም በፈረንሳይ እና ኮትዲቯር ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር በመሆን ለስምንት ዓመታት ሰርተዋል።
በ“ዳኛው ማነው?” የራሳቸው ታሪክ መካተትን በተመለከተ ደራሲዋ፤ “ዋነኛ ዓላማው ብርሃነመስቀልን መዘከር አድርጎ የተጠነሰሰው ትውስታ፣ የእኔን የትግልና የግል ሕይወት፣ በዚሁ ሳቢያም ቤተሰቦቼ ያለፉበትን ውጣ ውረድ በተጓዳኝ መዳሰሱ አልቀረም። በዚህም መጽሐፉ፣ የኛ ልጆችም ሆኑ ወላጆቻቸው በተመሳሳይ ትግል ያለፉ ልጆች፣ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ በግልጽ እንዲረዱ፣ ትልቁን ስዕል ለማሳየት ያግዛል ብዬ አስባለሁ” ሲሉ በመጽሐፉ “መቅድም” መልዕክታቸውን አስፍረዋል።
መጽሐፉ ለታሪክ ተመራማሪዎች እና ተንታኞች ግብዓት የሚሆን መረጃና ዕውቀት እንደሚያስተላልፍ ጠንካራ እምነታቸውን የገለጹት ታደለች “ከዚህ መጽሐፍ ያገኙትንም ግብዓት፤ ለመጪው ትውልድ ለእውነት ያደላ፣ ሚዛናዊ የአገር ታሪክ ለማዘጋጀት እንዲጠቀሙበት እመኛለሁ” ብለዋል። የመጽሐፉን “ቀዳሚ ቃል” የጻፉት የታሪክ ፕሮፌሰሩ ባሕሩ ዘውዴ መጽሐፉ በበርካታ ምክንያቶች “ትልቅ እርባና” ያለው መሆኑን ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
“የመጽሐፉ [አንድ] ትልቅ እርባና በኢሕአፓ ውስጥ የተከሰተውንና ውድቀቱን ያፋጠነውን ክፍፍል በዝርዝር ለመረዳት ማስቻሉ ነው” ብለዋል ባሕሩ በመጽሐፉ መግቢያ ጽሁፋቸው። “የዚህ መጽሐፍ አንዱ ፋይዳ የብርሃነመስቀልን ሁለንተናዊ ስብዕና አጉልቶ ማውጣት መቻሉ ነው። እስካሁን በአብዛኛው ከታወቀበት ታጋይነቱም ባሻገር፣ ወግ አዋቂነቱ፣ የሥነ ጽሑፍና የተውኔት ክህሎቱ፣ የክላሲካል ሙዚቃ አፍቃሪነቱ፣ ከዩኒቨርስቲው በታገደባቸው ዓመታት በናይሮቢ የነበረው የቢቢሲ ጋዜጠኝነትና የፍቅርም ሕይወት” በማለት የመጻፉ መታተም ጠቀሜታን አስቀምጠዋል።
በ442 የተዘጋጀው “ዳኛው ማነው?” መጽሐፍ በሀገር ውስጥ በ295 ብር እንዲሁም በውጭ ሀገራት ላሉ አንባቢያን በ24.50 ዶላር ለገበያ ውሏል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)