በወላይታ የዞኑን ከፍተኛ አመራሮች ጨምሮ 26 ግለሰቦች ታሰሩ

በተስፋለም ወልደየስ 

የወላይታ ዞን ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ ቁጥራቸው 26 የሚሆኑ ግለሰቦች ዛሬ እሁድ ነሐሴ 3፤ 2012 በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የደቡብ ክልል አስታወቀ። የግለሰቦቹን በቁጥጥር ስር መዋል ተከትሎ የዞኑ አስተዳደር መቀመጫ በሆነችው ሶዶ ከተማ ወጣቶች  ተቃውማቸውን ሲያሰሙ ማምሸታቸውን እና የጥይት ተኩስም ይሰማ እንደነበር ነዋሪዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

የደቡብ ክልል ቴሌቪዥን ጣቢያ የክልሉን ፖሊስ ኮሚሽን እና ጸጥታ ቢሮን ጠቅሶ ምሽቱን ባቀረበው የዜና እወጃ፤ የዞኑ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ 26 ግለሰቦች ዛሬ ከሰዓት መያዛቸንው ዘግቧል። ጣቢያው የአመራሮቹን ማንነት ግን በዝርዝር አላሳወቀም።  

በወላይታ በተቃዋሚ ፓርቲነት የሚንቀሳቀሰው የዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ (ዎብን) የፓርቲው የአደረጃጀት ጉዳይ ኃላፊ እና የወላይታ ዞን ከፍተኛ አመራሮች መታሰራቸውን ምሽቱን ባወጣው መግለጫ አረጋግጧል። ዛሬ ከታሰሩት ውስጥ የሌላኛው ተቃዋሚ ፓርቲ የዎላይታ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ዎሕዴግ) ምክትል ሊቀመንበር፣ የሀገር ሽማግሌዎች ተወካዮች፣ የተለያዩ አክቲቪስቶች እና ሌሎች ግለሰቦች እንደሚገኙበትም ይፋ አድርጓል።

ዎብን፤ የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች እና ሌሎች ግለሰቦች በቁጥጥር ስር የዋሉት በሶዶ ከተማ ካለው ጉተራ አዳራሽ በስብሰባ ላይ ባሉበት ወቅት እንደሆነ በመግለጫው ጠቁሟል። ከአመራሮቹ ጋር ተሰብስበው የነበሩት ከተለያየ አደረጃጀት የተወጣጡ የወላይታ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምስረታ አስተባባሪ ካውንስል አማካሪ ቦርድ አባላት እንደነበሩም አመልክቷል።   

ግለሰቦቹ ከጉተራ አዳራሽ ተይዘው ሲወሰዱ የተመለከቱ አንድ የአይን እማኝ የአዳራሹ ቅጥር ግቢ ቢያንስ ለአንድ ሰዓት ያህል ቀይ ኮፍያ ባጠለቁ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ሲጠበቅ እንደነበር መመልከታቸውን አስረድተዋል። ከቀኑ አስር ሰዓት ገደማ ከአዳራሹ ግቢ የተወሰኑ ሰዎች በመከላከያ ሰራዊት አባላት ታጅበው ወደ ውጭ ከወጡ በኋላ የዞኑ ምክትል የዞን አስተዳዳሪ በሚጠቀሙበት የላንድክሩዘር መኪና እና የፌደራል ፖሊስ አባል በጫነ ሌላ ተሽከርካሪ እንዲገቡ ተደርጎ ወዳልታወቀ ቦታ መወሰዳቸውን አብራርተዋል። 

ሁለቱ ተሽከርካሪዎች ከፊታቸው እና ከኋላቸው የመከላከያ ሰራዊት አባላትን በጫኑ ፒክ አፕ መኪናዎች ታጅበው እንደነበር እማኙ ተናግረዋል። የተወሰዱትን ሰዎች ማስክ አጥልቀው ስለነበር ማንነታቸውን ከርቀት ለመለየት እንዳልቻሉም አክለዋል። ሆኖም በጉተራ አዳራሽ የነበሩ ሰራተኞች ከተወሰዱት ሰዎች መካከል “የዞኑ አስተዳዳሪ ዳጋቶ ኩምቤ እና አክቲቪስት አሸናፊ ከበደ እንደሚገኙበት ነግረውኛል” ብለዋል።   

ከቀኑ አስር ሰዓት ገደማ የነበረውን ይህን ክስተት፤ የተለመደ የባለስልጣን እንግዳ አጀብ እንደሆነ በማሰብ የአካባቢው ሰዎች ለሁኔታው እምብዛም ትኩረት አለመስጠታቸውን እማኙ ጠቁመዋል። ከደቂቃዎች በኋላ ግን በርካታ ወጣቶች ወደ አዳራሹ በመምጣት ተቃውሞ ማሰማት መጀመራቸውን አመልክተዋል። 

የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ መምህር እና አክቲቪስት አሸናፊ ከበደ

ወጣቶቹ ወደ አዳራሹ የሚወስደውን ጨምሮ በከተማይቱ ያሉ ሌሎች መንገዶችን ድንጋይ በመደርደርና ጎማ በማቃጠል መዝጋታቸውን የሶዶ ከተማ ነዋሪዎች ተናግረዋል። የተዘጉ መንገዶች ለማስከፈት እና ተቃዋሚ ወጣቶችን ለመበተን ጥይት በተደጋጋሚ ይተኮስ እንደነበርም ገልጸዋል። በጸጥታ ኃይሎች እና በወጣቶች መካከል የነበረው ፍጥጫ በተለይ በርትቶ የተስተዋለው “አንደኛ መስመር” ተብሎ በሚታወቀው የአስፋልት መንገድ እንደነበርም አስታውቀዋል። 

የጥይት ተኩሱ እስከ ምሽቱ አንድ ሰዓት ተኩል ድረስ ቀጥሎ እንደነበር የሚናገሩት ነዋሪዎች ከዚያ በኋላ በከተማው ያለው ሁኔታ ረገብ ማለቱን አመልክተዋል። በከተማይቱ የነበረው የትራንስፖርት አገልግሎት በመቋረጡም ሰዎች ወደ መኖሪያ ቤታቸው ለመሄድ ተቸግረው እንደነበር ገልጸዋል። 

ተቃዋሚው የዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ፤ የወላይታ ህዝብ የክልልነት ጥያቄውን ሲያቀርብ የነበረው በሰላማዊ መንገድ እንደነበር አስታውሶ ሆኖም የፌዴራል እና የደቡብ ክልል መንግስታት ሰላማዊ ጥያቄን “ወደ ሁከት ለመቀየር” ሞክረዋል ሲል ከስሷል። ሁለቱም አካላት የጀመሩትን “ሕገ ወጥ ድርጊት እንዲያቆሙ አጥብቀን እንጠይቃለን” ሲል አሳስቧል። 

“ፍትሐዊ፣ ሕገ-መንግሥታዊና ፍፁም ሠላማዊ የሆነ መንገድ በመጠቀም የዎላይታ ሕዝብ ለሚጠይቀው ጥያቄ በሠላም ተገቢ ምላሽ  ከመስጠት ይልቅ  አመራሮችንና  ታጋዮችን  የማሠር እርምጃ  ፈፅሞ ሕገ-ወጥና  የመብት ጥሰት ተግባር ነው” ሲል ፓርቲው የዛሬውን እስር ኮንኗል። ዎብን የታሠሩ ሰዎች በአስቸኳይ እንዲፈቱ እና የዎላይታ ሕዝብ  በክልል የመደራጀት  ሕገ-መንግስታዊ ጥያቄ  በአስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጠው በመግለጫው ላይ ጥያቄውን አቅርቧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)