በተስፋለም ወልደየስ
ዛሬ ከሰዓት የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ፊት የቀረቡት እስክንድር ነጋ እና ሁለት ተጠርጣሪዎች የፍርድ ቤት ሂደቱ በግልጽ ችሎት የማይካሄድ ከሆነ “የሂደቱ አካል መሆንም ሆነ መከራከር አንፈልግም” በማለት ጠበቆቻቸውን አሰናበቱ። ፍርድ ቤቱ የአቃቤ ህግ ምስክሮችን በዝግ ችሎት ለመስማት ለነሐሴ 8፤ 2012 ቀጥሯል።
እስክንድር ነጋ ዛሬ ለችሎት ሲናገር “ይህ ጉዳይ በሀገራችን ላይ ያንዣበበው የgenocide አደጋ የሚስተናገድበት እንደሆነ ይታወቃል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ተሞክሮ የሚያመለክተው እንዲህ አይነቱ ጉዳይ በግልጽ ችሎት እንዲታይ ነው” ብሏል። ፍርድ ቤቱ በዛሬው ውሎው ያቀረቡትን መከራከሪያ ውድቅ አድርጎ፤ “ችሎቱ በግልጽ አይታይም” በሚል ብይን በመስጠቱ “የሂደቱ አካል ላለመሆን” ከውሳኔ ላይ መድረሳቸውን ለፍርድ ቤቱ አመልክቷል።
አቃቤ ህግ የምስክሮችን አቀራረብ፣ ምስክሮች ጉዳት ሊደርስባቸው ስለሚችል ጥበቃ እንዲደረግላቸው እና የጥበቃውን አይነት በተመለከተ ለችሎት ትላንት ያቀረበውን አቤቱታ በመንተራስ እነ እስክንድር ነጋ በጠበቆቻቸው አማካኝነት ዛሬ ለፍርድ ቤቱ ሁለት ገጽ ምላሽ አስገብተዋል። ምላሻቸውን የመረመረው ፍርድ ቤቱ ያቀረቡትን መከራከሪያ ውድቅ አድርጓል።
የእነ እስክንድር ጠበቆች በመጀመሪያ ያቀረቡት አስተያየት አቃቤ ህግ በቀዳሚ ምርመራ፤ ፍርድ ቤት ያቀረባቸው የምስክሮች ዝርዝርም ሆነ የምስክሮችን አቀራረብ በተመለከተ በጹሁፍ ያቀረበው አቤቱታ ኮፒ “ለተከሳሾች ደርሶን መልስ እንድንሰጥ አልተደረገም” የሚል ነው። አቃቤ ህግ ያቀረባቸው ምስክሮች ግማሹ ከመጋረጃ ጀርባ (ማንነታቸው ሳይታወቅ)፣ ግማሹ ደግሞ በዝግ ችሎት እንዲሰሙ እንዳመለከተ ችሎቱ በቃል እንደነገራቸው ተጠርጣሪዎቹ በሁለተኛነት ባነሱት መከራከሪያቸው ጠቅሰዋል።
የቀዳሚ ምርመራ ችሎት ስልጣን፣ ወደፊት ለሚመሰረት ክስ ማስረጃ ማቆየት ብቻ እንደሆነና ምስክሮቹ እንዴት ይሰሙ በሚለው ላይ የወንጀል ስነ ስርዓት ህጉ ምንም ስላላስቀመጠ ክርክር ሊቀርብበት እንደማይችል ፍርድ ቤቱ ከዚህ ቀደም ለተጠርጣሪዎቹ መግለጹን የእነ እስክንድር ምላሽ አስታውሷል። የወንጀል ስነ ስርዓት ህጉ ቀዳሚ ምርመራን በሚመለከት ባላስቀመጠው ጉዳይ ላይ፤ አቃቤ ህግ አቤቱታ ማቅረቡ “ስነ ስርዓታዊ አይደለም” ተብሎ ውድቅ እንዲደረግ ጠይቀዋል።
አቃቤ ህግ የጠቀሰው አዋጅ ቁጥር 699/03፤ ስለ ቀዳሚ ምርመራ ስርዓት ምንም የሚጠቅሰው ነገር ስለሌለ፤ አዋጁን መሰረት አድርጎ የቀረበው ጥያቄ “የህግ ድጋፍ የለውም” ተብሎ ውድቅ እንዲደረግም ተጠርጣሪዎቹ አመልክተዋል። በዚሁ አዋጅ መሰረት ምስክሮች ጥበቃ የሚደረግላቸው፤ ሁለት መስፈርቶችን በአንድ ላይ ሲያሟሉ እንደሆነ መቀመጡን የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች አንስተዋል።
አንደኛው መስፈርት “የወንጀል ድርጊቱ ያለምስክሩ በሌላ መንገድ ሊረጋገጥ ወይም ሊደረስበት የማይችል ሲሆን” እንደሆነ የጠቀሱት ጠበቆች ሆኖም አቃቤ ህግ ይህንን በአቤቱታው ላይ ባለመግለጹ “የአዋጁን መጠየቅ አላሟላም” ሲሉ ሞግተዋል። ሁለተኛው መስፈርት “በምስክሮች ላይ ከባድ አደጋ ይደርሳል ተብሎ ሲታመን” እንደሆነ ያስታወሱት ጠበቆች አቃቤ ህግ ምስክሮቹ “ከባድ አደጋ ሊደርስባቸው ይችላል ከሚል ባለፈ ይህን ድምዳሜውን የሚደግፍ ማስረጃ በአቤቱታው ላይ አላቀረበም” ሲሉ ተከራክረዋል።
አቃቤ ህግ የምስክሮች ጥበቃ ላይ አስመልክቶ ያቀረበው ምርጫም፤ የተከሳሾችን መስቀለኛ ጥያቄ የማቅረብ መብት ብቻ ሳይሆን የሚጎዳው የሕዝቡ ሂደቱን በሙሉ ተመልክቶ፣ እውነቱን የማወቅ መብትም ጭምር ነው ሲሉ ተጠርጣሪዎቹ በምላሻቸው አመልክተዋል። ተጠርጣሪዎች አቃቤ ህግ እንደሚፈልገው የምስክሮች ማንነት ከሚዲያ እና ከተጎጂ ቤተሰቦች ተደብቆ ሳይሆን በግልጽ እንዲደረግ እንደሚሹም ገልጸዋል።
የተጠርጣሪዎችን ዝርዝር ምላሽ በንባብ ያሰሙት ዳኛ፤ አቃቤ ህግ አስተያየት እንዲሰጥበት ዕድል ሰጥተዋል። ምስክሮች ስጋት ካለባቸው ጥበቃ እንደሚደረግላቸው በአዋጅ ቁጥር 699 በግልጽ መቀመጡን አቃቤ ህግ ጠቅሷል። የአቃቤ ህግ ምስክሮች የሚያስረዱት ፍሬ ነገርም በሌላ ምስክር የማይረጋግጡ መሆናቸውን ገልጿል። የምስክሮች ማንነት ቢገለጽ እና አድራሻቸው በግልጽ ቢነገር፤ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ቢሆኑም፤ አደረጃጀቱ ታች ድረስ ያለ ስለሆነ ጉዳት ሊደርስባቸው እንደሚችል አስረድቷል።
“ለምስክሮች በሌላ መልኩ ጥበቃ ሊደርግ ይችል ነበር” በሚል በጠበቆች በኩል የቀረበው መከራከሪያ ተቀባይነት የማያገኝባቸውን ምክንያቶች አቃቤ ህግ ለችሎቱ ዘርዝሯል። ለምስክሮች መሳሪያ ማስታጠቅ የመሳሪያ አጠቃቀምን ማስተማር እንደሚጠይቅ የገለጸው አቃቤ ህግ ይታጠቁ ቢባል እንኳ “ከተደራጀ ጥቃት” እንደማያድናቸው ጠቁሟል። አድራሻ መደበቅም ከጥቃት እንደማያድን አክሏል። ምስክሮቻቸው ከባድ ጥቃት የሚደርስባቸው በመሆኑ ጥበቃ እንደሚያስፈልጋቸውም ለችሎት ገልጿል።
በተጠርጣሪዎች ላይ የቀረበው ተራ የደንብ መተላለፍ አሊያም ተራ የሰው መግደል እና ንብረት ማውደም ሳይሆን ከፍተኛ አደጋ የሚያስከትል ብሔርን ከብሔር፣ ሃይማኖትን ከሃይማኖት የሚያጋጭ ወንጀል መሆኑን ያመለከተው አቃቤ ህግ በዚህም ምክንያት ምስክሮቹ ጥበቃ እንደሚያስፈልጋቸው አትቷል። አቃቤ ህግ፤ ተጠርጣሪዎቹ ይህንን ለመፈጸማቸው በቂ ማስረጃ አለንም ብሏል።
“የምስክሮቹን ማንነት አለማወቅ የተጠርጣሪዎቹን የመከላከል መብት ያጣብባል” በሚል የተነሳውን ሀሳብም አቃቤ ህግ አስተባብሏል። ተጠርጣሪዎቹ መከራከር ያለባቸው ሀሳቡን እንጂ የሰውየውን ማንነት አይለም ብሏል። የምስክሮቹን መልክ አለመለየት የመከላከል መብትን ያጣብባል ብለን አንገምትም ሲልም ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል። ይህንን የአቃቤ ህግ ማብራሪያ የተጠርጣሪ ጠበቆች ተቃውመዋል። የምስክሩ ማንነት አለመታወቅ የመከላከል መብታችንን ይጎዳል ሲሉም አቤት ብለዋል።
የግራ ቀኙን ክርክር፤ አግባብነት ካላቸው የህግ ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ የመረመረው ፍርድ ቤቱ የእነ እስክንድርን መከራከሪያ ውድቅ በማድረግ አቃቤ ህግ ምስክሮችን ማሰማት እንዲቀጥል አዝዟል። ፍርድ ቤቱ በምስክሮች ዝርዝር ከአንድ እስከ ሶስት የተዘረዘሩት ግለሰቦች ማንነታቸው ሳይታይ ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው እንዲመሰክሩ ብይን ሰጥቷል። በዝርዝሩ ከአራተኛ እስከ ሰባተኛ የተጠቀሱ ምስክሮች ደግሞ በዝግ ችሎት እንዲመሰክሩ በይኗል።
አቃቤ ህግ ለዛሬ ሁለት ምስክሮችን ማቅረቡን ቢገልጽም፤ ከምስክር መሰማት በፊት እስክንድር ለመናገር እድል እንዲሰጠው ጠይቆ ተፈቅዶለታል። ፍርድ ቤቱ ዛሬ የሰጠው ብይን፤ ከአለም አቀፍ ተሞክሮ “በተቃራኒ ነው” በሚልም ተቃውሞውን አሰምቷል። ከዚህ በኋላ “በዚህ ችሎት መገኘት አንፈልግም” ያለው እስክንድር “የክስ ሂደቱ የሚቀጥል ከሆነ እኛ በሌለንበት እንዲቀጥል ነው የምንጠይቀው” ሲል ለችሎት አመልክቷል።
አቃቤ ህግ “ይህ አቋም የሌሎቹም ተጠርጣሪዎች መሆኑ” እንዲረጋገጥ በጠየቀው መሰረት የዕለቱን ችሎት የመሩት ዳኛ፤ ይህንኑ ከተጠርጣሪዎቹ አንደበት አረጋግጠዋል። “የአቃቤ ህግ አካሄድ እኛን በከፍተኛ ደረጃ ሊጎዳ የሚችል ነው” ያሉት ሁለተኛው ተጠርጣሪ ስንታየሁ ቸኮል “አቃቤ ህግ ማስረጃ አለኝ ብሏል። አሁን ግን ከመጋረጃ ጀርባ ካልሆነ ምስክሮችን አላሰማም እያለ ነው። ይህ ደግሞ ህዝብ ውስጥ ብዥታ ይፈጥራል” ሲሉ ተነጋግረው እንደወሰኑበት ገልጸዋል።
ሶስተኛዋ ተጠርጣሪም “አቶ እስክንድር ነጋ የተናገሩት የእኛም ሀሳብ ስለሆነ በዚሁ ነው የሚቀጥለው” ሲሉ ለዳኛው የማረጋገጫ ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል። ፍርድ ቤቱ በጉዳዩ ላይ እነ እስክንድርን ወክለው ችሎት የቆሙ ጠበቆቻቸውን አስተያየትም ጠይቋል።
ጠበቃ ኑሩ ሰይድ “የጥብቅና አገልግሎት በውል ላይ የተመሰረተ ነው። ደንበኛው ‘አሰናብቻለሁ’ ሲል ካንተ ጋር ያለኝን ውል አፍርሻለሁ ማለቱ ነው። አገልግሎቱ በውል ላይ ተመስርቶ ከሆነ እና ያ ውል ከሌለ አገልግሎቱን መስጠት አይችልም። ከዚህ በኋላ ለመናገር ስልጣን የለውም ማለት ነው” ሲሉ መልሰዋል።
ጠበቃ ሄኖክ አክሊሉ በበኩላቸው “የተጠረጠረ ወይም የተከሰሰ ሰው በፈለገው ጠበቃ መወከል አለበት። አሁን የህግ ድጋፍ ስለሌለን እንድሰናበት ነው” ሲሉ ለፍርድ ቤቱ ጥያቄ አቅርበዋል። ፍርድ ቤቱም ጉዳዩን መርምሮ በሰጠው ውሳኔ ሁለቱን ጠበቆች አሰናብቶ የፍርድ ቤቱ ሬጅስትራር ለተጠርጣሪዎቹ የተከላካይ ጠበቃ እንዲያቆም ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ፍርድ ቤቱ ዛሬ ምስክርነታቸውን ለመስጠት ቀርበው የነበሩ ሁለት የአቃቤ ህግ ምስክሮች ለአርብ ነሐሴ 8፤ 2012 ቀጠሮ ሰጥቶ የእለቱን ችሎት አጠናቅቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[ይህ ዘገባ ዘግየት ብሎ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]