የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት እነ ጃዋር መሐመድን ያቀረቡትን የ“ዳኛ ይነሳልን” ጥያቄ ውድቅ አደረገ። ፍርድ ቤቱ ብይኑን የሰጠው ልደታ በሚገኘው አዳራሽ ዛሬ ረቡዕ ነሐሴ 6፤ 2012 ባስቻለው ችሎት ነው።
ጃዋር መሐመድ እና በቀለ ገርባን ጨምሮ 14 ተጠርጣሪዎች የ“ዳኛ ይቀየርልን” ጥያቄ ያቀረቡት ከትላንት በስቲያ ሰኞ ነሐሴ 4፤ 2012 በነበረው ችሎት ነው። ተጠርጣሪዎቹ በጠበቆቻቸው በኩል ለፍርድ ቤቱ ያስገቡት ባለ ሰባት ገጽ አቤቱታ፤ ቀደም ሲል የተጠርጣሪዎቹን የጊዜ ቀጠሮ ይመለከቱ የነበሩት እና በስተኋላም በቀዳሚ ምርመራ መዝገቡን ለማየት በተሰየሙት ዳኛ “የችሎት አመራር ሁኔታ ላይ” የቀረበ ነው።
ዳኛው በችሎት አመራራቸው “ትክክለኛ ፍትህ ለመስጠት የሚያስችል ነጻ፣ ገለልተኛ እና ሚዛናዊ ስለመሆናቸው እምነት የማይጣልባቸው ናቸው” የሚለው አቤቱታው፤ ለዚህ ማሳያ የሚሆኑ ስድስት ምክንያቶች ዘርዝሯል። ምክንያቶቹን አንድ በአንድ የተመለከተው የዛሬው ችሎት የቀረበው አቤቱታ “በማስረጃ የተደገፈ ስላልሆነ ዳኛው ከችሎቱ ሊነሱ አይገቡም” ሲል ብይን ሰጥቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)