በሐይማኖት አሸናፊ
የቀድሞው የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት እና የአሁኑ የመከላከያ ሚኒስትር አቶ ለማ መገርሳ ከትላንት ረቡዕ ነሐሴ 6፤ 2012 ጀምሮ በቤት እንዲቆዩ ትዕዛዝ መሰጠቱን የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ታማኝ ምንጮች ተናገሩ። አቶ ለማ በዚህ ሳምንት በስራ ቦታቸው ላይ የታዩ ቢሆንም፤ ከትላንት ጀምሮ ግን ወደ ስራ ቦታ ጭምር እንዳይመጡ እንደተነገራቸው ምንጮች ገልጸዋል።
የኢፌዲሪ የመከላከያ ሚኒስትር በመሆን ከሚያዝያ 2011 ጀምሮ እያገለገሉ ከሚገኙት ከአቶ ለማ በተጨማሪም ለጸሃፊያቸውም ተመሳሳይ ትዕዛዝ እንደተላለፈ ምንጮች አስረድተዋል። በትላንትናው ዕለት በአቶ ለማ ጽህፈት ቤት ላይ ብርበራ ስለመካሄዱ መረጃዎች ቢወጡም፤ የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጮች ግን ይህንን አስተባብለዋል።
የመከላከያ ሚኒስትሩ የስራ አስፈፃሚው እንጂ የሰራዊቱ አባል እንዳለመሆናቸው “ወደ ስራ ቦታ እንዳይመጡ” የሚለው ትዕዛዝ ከአስፈፃሚው አካል የመጣ መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የደረሰው መረጃ ያሳያል። ነገር ግን ለአቶ ለማ ይህንን መልክት ያደረሷቸው የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ ጄነራል አደም መሃመድ እንደሆኑ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጫችን ገልጸዋል።
ጄነራል አደም ትዕዛዙን ለአቶ ለማ የነገሯቸው ትላንት ሊደረግ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረን አንድ ስብሰባ ለመሰረዝ በተነጋገሩበት ወቅት እንደሆነም እኚሁ ምንጭ ጠቁመዋል። “ሁለቱም ተጠሪነታቸው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው፤ ስልጣናቸውም የጎንዮሽ እንጂ የበላይ እና የበታች አይደለም” ሲሉም አክለዋል።
ባለፈው ዓመት ተሻሽሎ በወጣው የመከላከያ ሰራዊት አዋጅ ቁጥር 1100/2011፤ አንቀፅ 23 መሰረት የመከላከያ ሚኒስትሩ ዘጠኝ ዋና ዋና የስራ ተግባሮች አሉት። ተግባራቱ ከሰራዊቱ የእለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች ይልቅ የአስተዳደር ስራዎች ላይ ያተኩሩ ናቸው።
በአዋጁ መሰረት ሚኒስትሩ መከላከያን በተመለከተ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ለመከርባቸው እና ሊወሰኑ የሚገባቸውን ጉዳዮች እያቀረበ ያስወስናል። የመከላከያ ሚኒስትሩ የተለያዩ ህጎች እና ፖሊሲዎችን በተመለከተ ሃሳብ የማመንጨት ስልጣን ያለው ሲሆን ሲጸድቁም ስራ ላይ መዋላቸውን ያረጋግጣል።
እንደ መከላከያ ፋውንዴሽን ያሉ የሰራዊቱን የልማት ተቋማት የመምራት ኃላፊነት ያለው ሚኒስትሩ፤ የመከላከያ ሚኒስቴርን በጀት የማዘጋጀት እና በስራ ላይ መዋሉን በመጠየቅ የማረጋገጥ ስልጣን በአዋጅ ተሰጥቶታል። ይህ አካሄድ የአለም አቀፍ የሲቪሎች ክትትል (civilian supervision) መርህን የተከተለ፤ በህዝብ የተመረጠ አካልን ከዩኒፎርም ለባሹ ሰራዊት ጋር የሚያስተሳስር ነው።
መከላከያ ሚኒስትሩ እነዚህን ኃላፊነቶቻቸውን መወጣት ይጠበቅባቸው የነበረ ቢሆንም፤ ባለፈው አንድ አመት ወደ ስራ ገበታቸው የሚመጡት አልፎ አልፎ ብቻ መሆኑን አንድ ከፍተኛ የስራ ኃላፊ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቀዋል። የአቶ ለማ ከስራ ገበታ መቅረት እንግዳ ነገር አይደለም የሚሉት እኚሁ ኃላፊ “በቤት ይቆዩ” የሚለው ትዕዛዝ መሰጠቱም አይስገርምም ባይ ናቸው። ለዚህ አባባላቸውም በማስረጃነት የሚጠቅሱት፤ አቶ ለማ ቀድሞውንም በአብዛኛው በቤታቸው የሚያሳልፉ መሆናቸውን ነው።
አቶ ለማ “በቤት እንዲቆዩ” ትዕዛዝ ቢተላለፍላቸውም በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን እንደተናኘው ጉዳዩ “የቁም እስር” አለመሆኑን በጸጥታው ዘርፍ ያሉ የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጭ ተናግረዋል። “በዚህ ሰዓት ማን፣ ምን አደጋ እንደሚያደርሰባቸው አይታወቅም። ስለዚህም በቤት እንዲቆዩ መታዘዙ ከእስር ጋር የሚገናኝ ሳይሆን ጥበቃ ይመስለኛል” ሲሉም አስረድተዋል።
ትዕዛዙ መተላለፉን ተከትሎ በአቶ ለማ መኖሪያ ቤት ዙሪያ “የተለየ እንቅስቃሴ ታይቷል” በሚል የተሰራጨውን መረጃ ለማጣራት በትላንትናው ዕለት ወደ ስፍራው የሄደው የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ “ከወትሮው የተለየ ጥበቃም ሆነ እንቅስቃሴ” ያለመኖሩን ተመልክቷል፡፡ የአቶ ለማ ቤት በሚገኝበት ሰፈር የሚገኙ ሶስት ጥበቃዎችን ያነጋገረው ዘጋቢያችን በአካባቢያቸው ለየት ያለ ነገር ያለመመልከታቸውን ገልጸውለታል።
“ነገሮችን ማባባስ ሳይሆን ማረጋጋት መርጧል። በጠረጴዛ ዙሪያ በሚደረጉ ውይይቶችም ነገሮች ምላሽ ያገኛሉ ብሎ ያምናል። ለዚያም ነው ወደ መገናኛ ብዙሃን መቅረብ ያልፈለገው”
ከሚኒስትሩ ግቢ የወጡ ሁለት የጥበቃ ሰዎች ተመሳሳይ ጥያቄ ሲቀርብላቸው ግራ ሲጋቡ ተስተውለዋል። ጥያቄው ለምን እንደቀረበም ዘጋቢውን ማብራሪያ የጠየቁት የጥበቃ ሰዎች ከተወሰኑ ምልልሶች በኋላ “ሁሉም ነገር ሰላም እንደሆነ” ለዘጋቢው ምላሽ ሰጥተዋል። አቶ ለማም ትናንት ረቡዕ በቤታቸው ማሳለፋቸውን ምንጮች አረጋግጠዋል።
“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጉዳዩን በተመለከተ የአቶ ለማን አስተያየት ለማግኘት ብትሞክርም፤ የእጅ ስልካቸው ጥሪ የማያስተናግድ በመሆኑ ሙከራው ሳይሳካ ቀርቷል። ሆኖም የአቶ ለማ የቅርብ ጓደኛ፤ ሚኒስትሩ ለመገናኛ ብዙሃን ምንም አይነት አስተያየት መስጠት እንደማይፈልጉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
“ነገሮችን ማባባስ ሳይሆን ማረጋጋት መርጧል። በጠረጴዛ ዙሪያ በሚደረጉ ውይይቶችም ነገሮች ምላሽ ያገኛሉ ብሎ ያምናል። ለዚያም ነው ወደ መገናኛ ብዙሃን መቅረብ ያልፈለገው” ሲሉም የቅርብ ጓደኛቸው አስታውቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[የኢትዮጵያ ኢንሳይደሩ ተስፋለም ወልደየስ ለዚህ ዘገባ አስተዋጽኦ አድርጓል]